የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከገጽታ ግንባታ ዘገባ ባሻገር ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረጉ ዘገባዎችን ከማቅረብ አኳያ ክፍተት እንዳለባቸው ይነገራል። ለመሆኑ በግድቡ ዙሪያ የሚሰሩ ዘገባዎች ምን ያህል ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረጉ ናቸው?
ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን፤ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ በተለያዩ ቀውሶች እየተናጠች ባለበት ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ተቀርጾ ሥራ የተጀመረበት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በደረሰባቸው አካባቢዎች የነበረው ግጭት የቆሞበት ወቅት መሆኑን ያስታውሳል።
እንደ ጋዜጠኛ ዳዊት ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከገጽታ ግንባታ ባሻገር ብሔራዊ ጥቅምን ሊያስከበር በሚችል ደረጃ ዘገባዎችን እያቀረቡ አይደለም። አሁን ላይ የመገናኛ ብዙኃኑ ዝምታ ስለበዛ ህዝቡም አብሮ ዝም ብሏል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በአንድ ወቅት የመንግሥትን የትኩረት ሞቅታ ተቀብለው ሲሰሩ ነበር የሚለው ጋዜጠኛ ዳዊት፤ “የትኛውም መንግሥት ቢኖር ግድቡ የሚኖርና የሚዘልቅ፤ የህዝብንና የአገርን ብሄራዊ ጥቅም ማረጋገጫ መሆኑን አይዘግቡትም ነበር” ይላል።
በግብጽ በኩል ያለው አቋም ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝቦች ፊታቸውን አዙረውበታል ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ተነስተው ግድቡን ግዑዝ ነገር አድርገው እስከማስቀረት ድረስ በርካታ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆናቸውን፤ የግብጽ መንግሥት ከሚያደርገው በተጨማሪ መገናኛ ብዙኃኑ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ላይ ምን አይነት ጫና ማድረግ እንዳለባቸውም አጀንዳ ቀርጸው እየሠሩ መሆናቸውን ጋዜጠኛ ዳዊት ይናገራል።
“በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያሉ መገናኛ ብዙኃን የድርድሩን ውጤትና የተስማሙበትንና ያልተስማሙ በ ትን ጉዳይ እንኳን ዋና ርዕሰ ጉዳይ አድርገው በብዛት አይዘግቡም። መግለጫ ይጠብቃሉ፤ አሊያም ሰው ጠርቶ መረጃ እስኪሰጣቸው ድረስ ይጠብቃሉ” ብሏል።”
አሁን ላይ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በግድቡ ዙሪያ የተለያየ አቋም እየያዙ መሆናቸውን፤ አንዳንዶቹ ግድቡን ያስጀመረው መሪ ከሌለ በስተቀር ሌላው ሊያስቀጥለው አይገባም” በማለትና ብሄራዊ ጥቅምን በመቃረን የግድቡን ጉዳይ ለማራከስ ጥረት ሲያደርጉ እንደሚስተዋሉና ለውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ መረጃ እስከመስጠት እንደሚደርሱ ጋዜጠኛ ዳዊት አስታውቋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት መምህር በረከት ሀሰን እንደሚሉት፤ በመገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረ ዘገባ ሲባል፤ የአገሪቷን ሉዓላዊነት በሚያከብር መንገድ የተፈጥሮ ጸጋዎችን የመጠቀም፣ የሰብዓዊ መብትን ማስጠበቅ፣ የህዝቦችን አንድነት የማስጠበቅና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚቀርብበት መንገድ ነው።
እንደእርሳቸው ገለጻ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የብሔራዊ ጥቅምን አስተሳሰብ እየሰሩ ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም። ከዚህ ይልቅ ብሔራዊ አንድነትንና ጥቅምን ሊበክሉ በሚያስችል መንገድ ነው የግለሰብና የቡድን ፍላጎቶችን በማራመድ የሚዘግቡት። ብሔራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አጀንዳዎችን መፍጠርና ወደማህበረሰቡ ማድረስ ሳይሆን የብሄራዊ አንድነትን ሊበትን የሚችል ሥራም ነው እየተሰራ ያለው። ግልጽ ያልሆኑ መረጃዎች በግድቡ ላይ የነበረውን አንድነት ሸርሽሯል። መገናኛ ብዙኃንም በግድቡ ዙሪያ ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ አኳያ ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም።
“የግብጽ ሚዲያዎች ባለፉት 20 ዓመታት ናይልን በተመለከተ ከመንግሥት የሚሰጣቸውን አጀንዳ በመውሰድ የራሳቸውንም አጀንዳ በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ጫና ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ እየተከተሉ ነው። ብዙ ገንዘብ ፈሰስ በማድረግና ተቋማትን በመገንባት በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲጻፉ በማድረግ ዓለም ስለአባይ ያለው አመለካከት ወደነርሱ እንዲያዘነብል አድርገዋል።
በአባይ ጉዳይ የግብጽ መንግሥትና መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ አንጻር የሰሩትን ያህል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አልሰሩም። የታላቁን ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ጫና ማሳደር ቀርቶ ብሔራዊ አንድነትን የማስጠበቅ ሥራ እንኳን አልተሰራም” ይላሉ አቶ በረከት፤ “የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም ያለው ቢሆንም በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ብዙ ትኩረት አልተደረገበትም” የሚሉት ደግሞ በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ብርሀኑ በላቸው ናቸው።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ከአገር ውስጥ አልፎ ከጎረቤት አገሮች ጋር እስከሚደረገው የኤሌክትሪክ ሽያጭ ግድቡ ይዞ የሚመጣውን እድል እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጠንከር ያለ አገራዊን ጥቅም የሚያጎሉ መረጃዎች አይወጡም። ለአብነት ከሦስት ዓመት በፊት አልጀዚራ የግብጽ ህልውና በአባይ ግድብ ላይ መመስረቱንና ችግር ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ “ስትራግል ኦቨር ዘ ናይል” የሚል ዶክመንተሪ ፊልም ሰርቶ ነበር። እንዲህ አይነቱን ተጻራሪ ዘገባዎች የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሊመክቱ ይገባ ነበር።
ዓለም አቀፍ የውሃ ህጉ ምን ይላል ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ በጉዳዩ ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ አለማግኘትና የግብጽ ፖለቲካ መሪዎችን ሀሳብ በሚገባ አለማስተዋል ክፍተቱን እንዳጎላው አቶ ብርሀኑ አስረድተዋል። በግድቡ ላይ ያሉትን እውነታዎች መገንዘቡ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገሮች ያለውን ፋይዳም ማሳየት እንደሚቻል ገልጸዋል። ተደራዳሪ ሆነው የሚሰሩ ባለሙያዎች የሚሰጡት ምክረ ሃሳብ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ማሳየት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙኃኑ በግድቡ ዙሪያ ያለውን መነቃቃት ጭምር እያዳከሙት መሆናቸውንና ይህም ከግብጽ መገናኛ ብዙኃን ፍላጎት ጋር ተመጋጋቢ አስመስሎታል የሚለው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በበኩሉ፣ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በግድቡ ዙሪያ አገራዊ ጥቅምን አስልተው አለመስራታቸውን፤ ከዚህ ይልቅ በየዘመኑ የነበሩ የመንግሥት ባለስልጣናት የሚሰጡትን ከፖለቲካ የመነጨ ሃሳባቸውን ይዘው መሮጡ ላይ ሲያተኩሩ እንደነበር ይናገራል።
ግድቡ ጥራቱንም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ደኅንነቱን ጠብቆ እየተገነባ መሆኑን፤ ከሌሎች አገሮች ጋር በምናደርገው ድርድርም የጥራቱን ጉዳይ ከመግለጽ ይልቅ ግብጽ ይዛ ለምትነሳው የመደራደሪያ ሀሳብ ሌላ ግብዓት እየሆኑ መሆኑንም ጋዜጠኛ ያየሰው ጠቁሟል።
ጋዜጠኛ ዳዊት በበኩሉ፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ብቻ ሳይሆን ማሳጣትም ጭምር እየታየባቸው መምጣታቸውን ገልጾ፤ ይህም የሆነው መገናኛ ብዙኃን በግድቡ ዙሪያ የራሳቸውን አጀንዳ ቀርጸው የማይሰሩና ብሔራዊ ጥቅምን የማያውቁ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳል።
ይህ እንደተቋምም እንደጋዜጠኛም በተናጠል ችግሮች መታየታቸውን፤ በሌላ መልኩ መንግሥት ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ከአሁን ቀደም በነበረው ልክ መንቀሳቀስና አጀንዳ መስጠት አለመቻሉ ችግሩን እንዳጎለው ጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም፤ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ስለግብጽ ፍላጎትና አካሄድ በቂ እውቀትና መረጃ አለመኖር ብሄራዊ ጥቅምን ያስከበረ ዘገባ እንዳይሰሩ ምክንያት መሆኑንም ተናግሯል።
የአገር ውስጥ የፖለቲካው ሁኔታ በአሸናፊነትና ተሸናፊነት ላይ ያተኮረ ሆነና የህዳሴ ግድብም የአንድ ወገን ብቻ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ መወሰዱን ለብሄራዊ ጥቅም ዘገባዎች ትኩረት እንዳይደረግ ሆኗል የሚለው ጋዜጠኛ ያየሰው፤ ግድቡ የመጀመሪያው ትልቅ ፕሮጀክት እንደመሆኑ ብዙ ችግሮች ሊገጥሙት እንደሚችሉ አስቀድሞ መገመት እንደሚቻል፤ ሆኖም ችግሮችን ለአገር ጥቅም ሲባል ከማዳን ይልቅ የበለጠ በማጉላት ከግድቡ በተቃራኒ ለቆሙ ኃይሎች ግብዓት የሆኑበት አጋጣሚም መፈጠሩን ያብራራል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረ ስላሴ በበኩላቸው፤ “መገናኛ ብዙኃን በዚህ ዙሪያ እየሰሩ ነበር አሁንም በመስራት ላይ ናቸው።
ነገር ግን የሚጎድለው ነገር መታየት አለበት። የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት ሆነን በመገናኛ ብዙኃን ረገድ የግብጾችን ያክል አልሰራንም። እኛ ድሆች ብንሆንም ተካፍለን እንጠቀምበት እያልን ባለንበት ወቅት እነርሱ ግን የድሮ ታሪክ ይዘው ባለቤት እኛ ነን እንደሚሉት ሁሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም ከእነርሱ በላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው። ትክክለኝነትና ሀቀኝነት ላይ በመመርኮዝ የህዝብን ጥቅም ሊያስከብር በሚችል መልኩ መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል።
ችግሩ የመገናኛ ብዙኃን ብቻ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ በረከት፤ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት መረጃ የሚሰጡበት መንገድ፣ በግድቡ ዙሪያ ከፍተኛ ጥናት ያደረጉ የኢትዮጵያ ምሁራንና መንግሥት በጋራ በመስራት ረገድ ግልጽነት አለመኖርም የችግሩ መነሻ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ መገናኛ ብዙኃኑ በግድቡ ዙሪያ ብሄራዊ አንድነትና ጥቅምን በሚያስከብር መልኩ ዘገባዎችን አለመስራታቸው ደግሞ የግብጽ መንግሥት በየጊዜው አቋሙን እየቀየረ ጫና እንዲያሳድር አስችሎታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ውሃና መሰል ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ጥናቶችን በመዳሰስ ከምሁራን ጋር በትብብር መስራት አለባቸው። በኢትዮጵያ ምሁራን የሚሰሩ ጥናቶች በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንዲቀርቡና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እውነታውን እንዲያውቁ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ሚና አላቸው። በአገር ውስጥ የሚገኙት ዲፕሎማቶች በግድቡ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙም ማድረግ አለባቸው።
እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፤ ጋዜጠኞች ከፖለቲካ ግፊት ነጻ ሆነው የአገራቸውን ጥቅምና ጉዳት መለየት አለባቸው። የፖለቲካው ማዕበል የሚንጣቸው ሳይሆኑ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ምንነት መረዳት ይኖርባቸዋል። “የብሔራዊ ደኅንነት አደጋው ከየት ይመነጫል?” የሚለውን በአግባቡ ተንትነው የተረዱ፤ ከአሉባልታ ይልቅ ለእውቀትና ለጥናት የተገዙ መሆን አለባቸው።
አሁን ላይ ግብጽ የኢትዮጵያውያንን የልብ ትርታ እያዳመጠች በታላቁ የህዳሴ ግድብና የውሃ አያያዝ፤ እንዲሁም አሞላል ላይ የሚደረጉ ድርድሮችን ጫና የመፍጠር አዝማሚያን ትከተላ ለች። የኢትዮጵያ መንግሥት “ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለህዝቦቼ የህልውና መሠረት ነው” ብሎ ሲናገር ህዝ ቡም በዚሁ አግባብ ሚዲያውም ህዝቡም ሊደግፈው ይገባል። ለብሔራዊ መግባባት ሊያገለግሉ የሚችሉ አጀንዳዎችም በአግባቡና በወቅቱ መቅረብ አለባ ቸው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2012
አዲሱ ገረመው