አዲስ አበባ፡- የግብጽ መንግሥት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አለቃቀቅና ሙሌት በተመለከተ አቅርቦት የነበረው መደራደሪያ ሀሳብ ኢትዮጵያን ለግድቡ ግንባታ የምታወጣውን ያህል የገንዘብ መጠን እንደሚያከስራት ተገለጸ፡፡
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ትላንት ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በግድቡ ግንባታ ሂደትና በተደረገው ድርድር ዙሪያ በሰጡት ገለጻ፤ ግብጽ ለድርድር አቅርባ የነበረው አዲስ “ፕሮፖዛል” የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ከመሆኑም ባሻገር ድርድሩ ተቀባይነት ቢያገኝ ኖሮ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ለግድቡ እያወጣች ያለውን ያህል ገንዘብ እንደሚያከስራት ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ግብጽ ይዛ ከቀረበችው የድርድር ሀሳብ መካከል፤ “በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ ይለቀቅልኝ” ማለቷ እና “የአስዋን ግድብ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 165 ሜትር ሲደርስ ኢትዮጵያ ውሃ መልቀቅ አለባት፤” እንዲሁም “ሶስተኛ ወገን በአደራዳሪነት ይግባ” የሚል አቋም ተካትቷል፡፡
የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እንዴት፣ ምን ያህል፣ በምን አይነት ሁኔታ የሚሉትን ቁጥጥር በግብጽ በኩል የተቀመጠው ሌላኛው ምክረ ሀሳብ ሲሆን፤ ይህም የአገርን ሉዓላዊነት የሚዳፈር በመሆኑ ተቀባይነት አላገኘም።
በሌላ በኩል፤ የውሃ መጠኑን ኢትዮጵያ በየዓመቱ አጠራቅማለሁ ብላ ከያዘችው የጊዜ ገደብ በተቃራኒ በየዓመቱ የሚጠራቀመውን የውሃ መጠን በማሳነስ እስከ 13 ዓመት ሊደርስ የሚችል የጊዜ ገደብ የሰፈረበት ሀሳብም ተነስቷል። ይህም ኢትዮጵያን በየዓመቱ ለገንዘብ ኪሳራ እንደሚዳርግና በአጠቃላይ ወጭም ለግድቡ እየወጣ ያለውን ያህል ገንዘብ እንደሚያከስር በስሌት ተደርሶበታል።
በአጠቃላይ፤ ግብፅ ያቀረበችው ምክረ ሃሳብ ኢትዮጵያ በውሃው ላይ ያላትን መብት የሚጥስ እና ብሄራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ በመሆኑ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን እንደማትቀበለው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በሀሰት መረጃ ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ለመፍጠር ከፍተኛ ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውንና የኢትዮጵያ መንግሥት ለጉዳዩ ቴክኒካዊ ትኩረት አድርጎ ዘላቂ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ግንባታውን በፍጥነት እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ከግብጽ ጋር ያለው ድርድር እስከ መሪዎች ሊደርስ ይችላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ያለውን የግድቡን የግንባታ ሂደትና የውሃ ሙሌት ሥራ የሚጻረር የትኛውም ሀሳብ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደማይኖረውና በድርድሩ የሌሎችን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ገልጸዋል። ለዚህም ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ መርኅን እየተከተለች ቢሆንም፤ በግብጽ በኩል እየታየ ያለው የማጥላላት ዘመቻና ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ የመፈለግ አዝማሚያ ከግንባታው መፋጠንና ውስጣዊ ችግሮች አንጻር መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያም ቴክኒካዊ ሥራውን እየሰራች ዲፕሎማሲያዊ ሥረዎችም እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2012
አዲሱ ገረመው