በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱት 139 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንድም የሴት መሪ እንደሌለ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረ መድህን አስታወቁ። በሀገራቱ የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ለውጥ ለማስቀጠልና የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማሳደግ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን ትላንት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና በተሰጠበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱት 139 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንድም የሴት መሪ ያለመኖሩን አውስተው፤ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ ለሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ንቁ ተሳትፎ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀው፤ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አካላት ሴቶች በፖለቲካ ላይ ያላቸውን ዝቅተኛ ተሳትፎ ለማሻሻል ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሰባ የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት በዚህ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ባተኮረ ስልጠና ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካይና የቦርድ አባል የሆኑት ወይዘሮ ብዙወርቅ ከተተ በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እጅግ ያነሰ እንደሆነና ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ የሚገባው መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ከ139 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አንድም ሴት መሪ እንደሌለ በማሳያነት ጠቁመዋል። አዲስ የተሻሻለው የምርጫ አዋጅ ለሴቶች የተሻለ እድል የሚከፍት መሆኑንም ገልፀው፤ ሴቶች በተፈጠረው እድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
ለመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባና ለዚህም ሴቶችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ ብዙወርቅ፤ ተሳትፏቸውን ወደተፈለገው ደረጃ ለማድረስ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም አስታውቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው፤ በሀገር ደረጃ የሚፈለገውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሴቶች ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ስልጠና በኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት አዘጋጅነትና በፊንላንድ “የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ” በተባለ ተቋም ትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ተተቁሟል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2012
ተገኝ ብሩ