«ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለም»
ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፡- ላለፉት ሃያ ዓመታት በተለያዩ የውጭ አገራት ተበታትነው የነበሩ ቅርሶችን በግል ጥረታቸው በማሰባሰብ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የቢሮክራሲው መንዛዛት ተስፋ እንዳስቆረጣቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ገለጹ። ሚኒስቴሩ በበኩሉ ጉዳዩ በሂደት ላይ በመሆኑ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር እንደሌለ ገልጿል።
አቶ አለባቸው ደሳለኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ክብርት ዶክተር ሂሩት ካሳው የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ወደ አገር ቤት ለመመለስ እንግሊዝ በሄዱበት ወቅት እንዳገኟቸውና ለሃያ ዓመታት በግል ጥረታቸው ያሰባሰቧቸውን ቅርሶች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው በመናገራቸው ሚኒስትሯ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ጥያቄውን አምነውበት የድጋፍ ደብዳቤ ልከውላቸዋል።
አቶ አለባቸው በተለያዩ አገሮች ዞረው ያሰባሰቧቸውን ቅርሶችና ሰነዶች ወደ አገር ቤት ለመመለስ በተስፋና በጉጉት ቢጠብቁም የቢሮክራሲው ተስፋ አስቆራጭነት ያሰቡትን ማሳካት እንዳላስቻላቸውና በዚህም ቅሬታ እንደተሰማቸው አመላክተዋል፡፡
ሁኔታው የተፈጠረው በሚኒስትሯ አለመተባበር ሳይሆን ባለው የአስተዳደር ብልሽት በመሆኑ ችግሩ ወደፊት ተፈትቶ ህልማቸው እውን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ያሉት አቶ አለባቸው፤ እርሳቸው በሕይወት እያሉ ለወገኖቻቸውና ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ጥልቅ ፍቅር ማሳየት ባለመቻላቸው ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡
«አንድ ቀን ልጆቼ ቅርሱን ይዘውት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ተስፋ አለኝ» ያሉት አቶ አለባቸው፤ እስከዚያው ግን በደረሰባቸው ተስፋ አስቆራጭ ቢሮክራሲና ትብብር ማጣት የኢትዮጵያን ቅርስና ታሪክ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የነበራቸውን ሃሳብ መሰረዛቸውን ተናግረዋል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚኒስትሯ አማካሪ አቶ ወርቅነህ አክሊሉ ‹‹አቶ አለባቸው ቅርሶችን በማሰባሰብ ለአገራቸው እየፈጸሙ ያሉት ሥራ የሚያስመሰግናቸው ነው፤ በሚኒስትሯ የተገባው ቃል አልተሰረዘም፤ጉዳዩን ከፍፃሜ ለማድረስም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ነው፤ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለም» ብለዋል።
አማካሪው ‹‹ቅርሶቹ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ለአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርግ ደብዳቤ ጽፈናል። ቅርሶቹ ሲመለሱ በቅርስነት የተያዙ ቤቶች ውስጥ እንዲቀመጡ ለማመቻቸት እየተሰራ ነው። ይህን ሁኔታም ለአቶ አለባቸው እንዲያውቁ አድርገናል። በመሆኑም ጉዳዩ በሂደት ላይ በመሆኑ ተስፋ የሚያስቆርጥና ሃሳብንም የሚያስቀይር ነገር የለም›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ