• ሕዝቡን የአሉባልታ ወሬዎች ሊፈታተኑት አይገባም
• አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ይደረጋል
• ኢትዮጵያ ሳተላይት ታመጥቃለች
አዲስ አበባ፡- የደህንነት ተቋማት ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድመው የማነፍነፍ አቅማቸውን ለማሳደግና ሲከሰትም በአጭር ጊዜ የማስቆም ብቃታቸውን ለማጎልበት የሚያስችሉ የአቅም ማሻሻያ ተግባራት በተያዘው 2012 በጀት ዓመት እንደሚሰሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ፡፡ በኢኮኖሚው መስክም በሥራ ዕድል ፈጠራና የኑሮ ውድነትን ማቃለል ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ ትናንት በአምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ስብሰባ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የዓመቱን የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ ዜጎች በገዛ አገራቸው ተፈናቃይ የሆኑበት አሳዛኝ ታሪክ ተጽፏል፡፡ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባለፈው አንድ ዓመት በጋራ ባደረጉት ርብርብም ከሁለት ሚሊዮን በላይ የነበረው የውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ከ100ሺ የማይበልጥ ሆኗል፡፡
እነዚህን ዜጎች ወደ ተረጋጋና መደበኛ ኑሮ የመመለስ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቷ ገልጸው፣ መሰል ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የደህንነት ተቋማት ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድመው የማነፍነፍ አቅማቸውን ለማሳደግና ሲከሰትም በአጭር ጊዜ የማስቆም ብቃታቸውን ለማጎልበት የሚያስችሉ የአቅም ማሻሻያ ተግባራት በበጀት ዓመቱ እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ብቁ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ጥናት ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር እንደሚሸጋገር ጠቅሰው፣ በሂደቱም የአሠራርና የሕግ ማዕቀፎቹን በማሻሻል በአጭር ጊዜ ጠንካራ የፌዴራል ፖሊስ ይኖረናል ብለዋል፡፡ የክልል ፖሊሲችንም አቅም ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
‹‹የመከላከያ ሠራዊታችን በሙያ አቅም የላቀ እንዲሆን እየተሰሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናከረው ይቀጥላሉ›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ የደህንነት፣ የጸጥታ ተቋማትንና የመከላከያ ሠራዊትን ሕጋዊ ማዕቀፎችና አቅሞችን በማዳበርና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ አሁን በአገራችን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ሰላም ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ የአገሪቱን ሰላም የማስጠበቁ ሥራ ያለ ሕዝቡ ተሳትፎ አይሳካም፡፡ በቀጣይ በሚካሄዱ የሰላም ምክክሮች ከተለያዩ የኅብረተሰብ አደረጃጀቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን 100ሺ የሚቆጠሩ አመቻቾችን የማሰልጠን ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ሕዝቡም ሰላምን በዘላቂነት በመገንባትም ሆነ ሕግን በማስከበርና በማክበር የሰላም መደፍረስ ምልክቶችን ጥቆማ በማድረስና ከሕግ አስከባሪ አካላት በጋር በመስራት የሰላም ባለቤትነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ እዚህም እዚያም የሚወረወሩ አሉባልታዎች ሊፈትኑት እንደማይገባ ጠቁመው፣ ‹‹አጋራችንን በጋራ ጥረት ሰላማዊ ለማድረግ በአርቆ አስተዋይነት ነገሮችን ሁሉ መጠየቅ እና መመዘን ይገባል›› ብለዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ነፃ ዴሞክራሲያዊ፣ ተአማኒትና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አስገንዝበዋል፡፡ ሂደቱን ለማሰናከልና ለማጠልሸት የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ተግባራትን በሕግና በሥርዓት እንደሚያስተካክልም አስታውቀዋል፡፡
የበጀት ዓመቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራት በጠናከረ ደረጃ የሚከናወኑበት እንደሆነ አመልክተው፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዓላማዎችም የማክሮ ኢኮኖሚውን ጤንነት መጠበቅ፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግና ለዜጎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገለጻ፤ የግብርናን ምርታማነት ለማሳደግም አገራዊ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት አዲስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ድሬዳዋ ላይ ለማቋቋም ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር በሽርክና በመፈራረም ሥራው በቅርቡ ይጀመራል፡፡ ግብርናን ለማዘመንም አስፈላጊውን የቀረጥ ማበረታቻ በማድረግ አርሶ አደሩ የዘመናዊ እርሻ መሣሪያዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
የመስኖ ልማት በሦስት ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በማሰማራት የተጀመረ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም በአገሪቱ 12 ሺ የተማሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደረግ የመስኖ ልማትና አቅም ግንባታ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የዋጋ ንረት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይ እንደሚጎዳ ጠቅሰው፣ የዋጋ ንረቱን የመቆጣጠር ሥራ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡ የዋጋ ንረቱ ይበልጥ የሚስተዋለው በምግብ ሸቀጦች ላይ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት መሠረታዊ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ከውጭ በማስገባት የዋጋ ንረቱ ሸማቾችን እንዳይጎዳ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለግብርና፣ ለደን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት የሚያስፈልጉትን የሳተላይት መረጃዎች ለመቀበል የሚውል የኢትዮጵያ ሳተላይት በታኅሣሥ ወር 2012ዓ.ም ላይ በቻይና ከሚገኝ የማምጠቂያ ማዕከል ወደ ጠፈር እንደምትልክም ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል፡፡ ሳተላይቱን ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሚቆጣጠሩበት ጣቢያም በእንጦጦ በሚገኘው ፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ጌትነት ምህረቴ