የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ፣ ለውጡን በማስቀጠል፣ በኢኮኖሚው፣ በዴሞክራሲው፣ በምርጫ ሂደቱ እና በማህበራዊ መስኮች በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተጠቀሱት የያዝነው ዓመት የመንግሥት አቅጣጫዎች ሁሉንም መስኮች የዳሰሱ ናቸው የሚሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ አስካል ጥላሁን፣ እነዚህን የሕዝብ አጀንዳዎች ለማሳካት ሕዝቡን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በእኔነት ስሜት ርብርብ ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጎችን የማጸደቅ ሥራ አንዱ ተግባሩ መሆኑን ገልጸው፣ ለአገር ለውጥ ሊያመጡ፣ ሰላምን ሊያስፍኑ፣ ፍትህን ሊያጎለብቱ፣ ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉ የሕግ ማዕቀፎች ወደ ምክር ቤቱ ለመጽደቅ ሲመጡ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ይገልጻሉ፡፡ የወጡ ሕጎችም ተግባር ላይ መዋላቸውን ለመከታተል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዕቅዶቹ ተፈጻሚ መሆናቸውን፣ የተቋማትን ጥንካሬና ብርታትን እያበጠሩ በማውጣት ክፍተቶች እንዲታረሙ ጥንካሬዎች እንዲበረታቱ የማድረጉ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም ይገልጻሉ፡፡ ኅብረተሰቡ በሁሉም ሥራዎች ተሳታፊ እንዲሆንም የምክር ቤት አባላት በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እንደ ድልድይ በመሆን ሚናችንን የምንወጣ ይሆናል ሲሉ ወይዘሮ አስካል ይገልጻሉ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አሸናፊ ጋሚ በፕሬዚዳንቷ የተጠቀሱት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ መስኮች የሚሰሩ አቅጣጫዎች ሕዝቡን በማስተባበር ተግባራዊ ከሆኑ ተጨባጭ ውጤቶች ማስገኘት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ መንግሥት ቅድሚያ ተሰጥቶት መስራት ያለበት የሰላም ጉዳይ መሆኑን አመልክተው፣ ይህ የሕዝብ ጥያቄ በአቅጣጫው መካተቱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚ መስክም የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነት ችግሩ ከሰላም ያልተናነሰ ፈታኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረው፣ ችግሩን ለመፍታት የተቀመጡት አማራጮች ሕዝቡም የሚጠብቃቸው ናቸው ሲሉ አቶ አሸናፊ ይጠቁማሉ፡፡ ለእዚህም ሕዝቡን በማንቀሳቀስ መስራት እንደሚገባ፣ ለውጤቱ መረባረብ እንደሚጠበቅ ያስገነዝባሉ፡፡ ለአቅጣጫዎቹ ተግባራዊነትም ምክር ቤቱ በበለጠ ትጋት የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎቹን ያጠናክራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ያቀረቧቸው አንኳር አንኳር የሥራ አቅጣጫዎች እንደሚሳኩ እምነታቸው መሆኑን የገለጹት ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ተሾመ መንግሥቱ፣ ሰላም ከማስፈን፣ ኢኮኖሚውን ከማሳደግ፣ ፍትህን ከማጎልበት፣ ግብርናውን ከማዘመን፣ የጤናንና ትምህርትን ጥራት ከመጠበቅና ተደራሽነት ከማረጋገጥ አኳያ የተቀመጡ አቅጣጫዎች የሚለኩ ናቸው፡፡
የምክር ቤቱ አባላትም አቅጣጫዎቹ ተግባራዊ ሆነዋል ወይስ ተጓትተዋል ወይ ብለን ለመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነትና ሥራ ይጠብቀናል፤ ለዚህም ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ጌትነት ምህረቴ