አዲስ አበባ፡- እየጨመረ የመጣውን የባንኮች ቁጥር ተከትሎ በመካከላቸው ተገቢ ያልሆነ ውድድር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስገነዘቡ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋክልቲ መምህርና የሂጅራ ባንክ ፕሮጀክት አደራጅ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙከሚል በድሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ‹‹የባንኮች ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር ውድድሩም አብሮ እያየለ ይመጣል፡፡ ይህም ባንኮቹ ተወዳዳሪ ሆነው መውጣት የሚያስችሉ አሠራሮችን እንዲቀይሱ የሚያስችል ሊሆን ይችላል፤ በአንጻሩ ግን ባንኮቹ ተገቢ ያልሆነና ሥርዓት አልባ ፉክክር ውስጥ ሊያስገባቸው ይቻላል፡፡
ውድድሩ አላስፈላጊ እየሆነ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም የተበላሸ ብድር እንዲበዛ፣ የብድር ማስያዣዎች የሚገመቱበት መንገድና የፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናት በማካሄድ ረገድ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ሊቀንሰው እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
ባንኮቹ በተበራከቱ ቁጥር አሁን ካለው በበለጠ የባለሙያዎች መቀማማት እንደሚፈጥር ያስገነዘቡት አቶ ሙከሚል፣ ይህም አንዳንድ ባንኮችን ሊያዳክምና ሊጎዳ የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖርም አስገንዝበዋል፤ የአንደኛውን ባንክ መረጃ ወደ ሌላኛው የመስጠት አዝማሚያ ሊፈጠርና በዘርፉ ላይ ጤናማ ያልሆነ ከባቢ እንዲፈጠር እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ አንድ ሕንፃ ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ምናልባትም ጎን ለጎን ሃያ እና ከዚያ በላይ የባንክ ቅርንጫፎችን እንድንመለከትና ባልተገባ መልኩ ሀብት እንዲባክን እንደሚያደርግም አብራርተዋል፡፡
እነዚህን ስጋቶች ለመከላከል ባንኮች የአደጋ ቅነሳ ሥራቸውን በጣም በትኩረትና በጥንቃቄ ማከናወን እንዳለባቸው ያስገነዘቡት አቶ ሙከሚል፣ ይህም ከባንኮቹ በተጓዳኝ እንደ አንድ አስተዳዳሪ አካል የብሔራዊ ባንክ ሚና መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ፣ የባንኮች የኢኮኖሚው ዋነኛ ዘዋሪና ጤናማነት መሠረት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከሌሎቹ አገልግሎቶችም በላይ ዘርፉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የአቶ ሙከሚልን ሀሳብ በማጠናከር የባንኮች ቁጥር ሲጨምር በመካከላቸው ተገቢ ያልሆነ ፉክክር ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ደንበኛ ለመሳብ ወይም ተበዳሪ ለማግኘት ከተለመደው ውጪ በዝቅተኛ የዋስትና መያዣ ከፍተኛ ገንዘብ መስጠት ይኖራል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ ኪሳራው ከፍተኛ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
በዚህ ዓይነት ያልተገባ አካሄድም በርካታና ግዙፍ ባንኮች በአጭር ጊዜ ኪሳራ ላይ መውደቃቸውንና ከገበያ መውጣታቸውን ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፡ ብሔራዊ ባንክም ለአገሪቱ ኢኮኖሚና ለሴክተሩ ጤናማነት ሲል የባንኮቹን አሠራር በየጊዜው የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት አስታውቀዋል፤ መንግሥትም ዘርፉን የሚቀላቀሉትን ተከታትሎ ፈር ማስያዝ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ የኃላፊነት ስሜት ከውጭ የሚመጣ ሳይሆን ከግል የሚጀምር ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ባንኮቹ ጤናማ የፉክክር አካሄድ ምርጫቸው ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ታምራት ተስፋዬ