አዲስ አበባ፡- የአየር ፀባይና ሁኔታ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጥናትና በመተንተን የሚያቀርበውን የትንበያ መረጃ ተደራሽነትንና ተአማኒነቱን ለማስፋትት በዘመናዊ መሣሪያና ብቃት ባለው የሰው ኃይል ራሱን እያጎለበተ መሆኑን ብሔራዊ የሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ኤጀንሲው የአየር ፀባይና ሁኔታ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጥናትና በመተንተን የሚያቀርበው ትንበያ ተደራሽነትን ለማስፋትና ተአማኒነቱን ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በተለይ ከሰው ኃይል አቅርቦት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ራስን ከማጎልበት አኳያ ኤጀንሲው ከፍተኛ እምርታን በማስመዝገብ ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፈጠነ፣ በ2004 ዓ.ም 20 ብቻ የነበረውን ሰው አልባ አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ መከታተያ መሣሪያ ብዛት በአሁኑ ወቅት 322 ማድረሱን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም ያልነበረ አንድ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር በጣና በለስ አባይ ተፋሰስ ላይ ተተክሏል›› ያሉት አቶ ፈጠነ፣ በቀጣይም ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመስራት የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳርን ብዛት ወደ አራት ለማሳደግ ጅምር ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በተለይ የመኪና ፍሰት እና ኢንዱስትሪ በሚበዛባቸው አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሃዋሳ በመሳሰሉ ከተሞች የአየር ብክለት መከታተያ መሣሪያዎች ተከላ ማካሄዱንም አስታውቀዋል፡፡
የሰው ኃይል አቅም በማጎልበት ረገድ ኤጀንሲው በ2004 ዓ.ም የነበሩትን ከስምንት የማይበልጡ የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቃን ሠራተኞች ቁጥር አሁን ላይ 60 ማድረሱን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ለመስጠት እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡
በመረጃ ተደራሽነት ረገድም ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስፈላጊውን መረጃ በአስፈላጊው ወቅት በማቅረብ ላይ ስለመሆኑም ጠቁመው፣ ይሁንና የሚሰጡ መረጃዎች ተተንትነው በሚቀርቡበት ወቅት ሕዝብ ዘንድ የአረዳድ ክፍተት እንደሚስተዋልም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹መረጃዎቹ ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለአብዛኞች ግልፅ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች መሰራት አለባቸው›› ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው ያለፈው ክረምት የአየር ጸባይና በሚቀጥለው በጋ ወቅት የሚጠበቀውን የአየር አዝማሚያን አስመልከቶ ከሰሞኑ በሰጠው መረጃ፣ ባለፈው ክረምት ወር በመላ አገሪቱ የተስተዋለው የዝናብ መጠንና ስርጭት በአብዛኛው ጥሩ ገፅታው ያመዘነ መሆኑን ጠቅሶ፣ በተለይም ለግብርናው ሥራና ለውሃ አቅርቦት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በተያዘው ዓመት በጋ ወቅት በብዙ አገሪቱ አካባቢዎች ላይ አንፃራዊ እርጥበታማ አየር ፀባይ ሊዘወተር እንደሚችልም መተንበዩ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ታምራት ተስፋዬ