አቶ ካብቱ ሽኩር በአራዳ ክፍለ ከተማ አራት ኪሎ ሰብለ ዓሣ ቤት ጀርባ ባለው መንገድ ዳር አልባሳትን በመነገድ ይተዳደራሉ፡፡ ይህንን ሥራ ከጀመሩም ስምንት ወር እንደሆናቸውና ሙሉ ቀን እንደሚሠሩ ይገልፃሉ፡፡
በክፍለ ከተማውና ወረዳው ትብብር የሽግግር ጊዜ ፍቃድ እንዳወጡ የሚናገሩት አቶ ካብቱ፣ ቀደም ሲል ጎዳና ላይ ልብስ ሲሸጡ በነበረበት ወቅት በፍርሃት ተሞልተው እንደሚሰሩና ልብሶቻቸውም የሚወሰዱበት ጊዜ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በተለይም አዩኝ አላዩኝ ተብሎ በሚደረግ እንቅስቃሴ ከእግረኛ ጋር መላተሙ፣ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር መጋጨቱና እነርሱንም ለመሸሽ ሲባል መንገድ በሚያቋረጡበት ጊዜም ለትራፊክ አደጋ መጋለጡ ፈታኝ ጊዜ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በተሰጣቸው ቦታ ጊዜያዊ የሽግግር ፍቃድ አውጥተው ተረጋግተው እየሠሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
ወይዘሪት ለይላ አብደላ በበኩላቸው በዚሁ በአራት ኪሎ የሴቶች አልባሳት ከነአላባሽ በመነገድ የሚታዳደሩ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ልክ እንደ አቶ ካብቱ ሁሉ በመንገድ ላይ በሚነግዱበት ወቅት ብዙ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ በመሆኑም አሁን በመስራት ላይ ያሉት ሥራ ቀደም ሲል ከሚሰሩት ጋር አይገናኝም፡፡‹‹መንገድ ላይ ስንሠራ መባረር አለ፤ የሰውና ተሽከርካሪ ግፊያ አለ፡፡ ሥራው ሁሉ የአባሮሽ ያህል በመሯሯጥ ነበር የሚሰራው፤ መረጋጋትም አልነበረም፡፡ አሁን አንድ ቦታ ላይ ቁጭ ብለን ተረጋግተን በተሰጠን ቦታ በመስራት ላይ ነን፡፡›› ይላሉ፡፡
በአካባቢው በተመሳሳይ ንግድ ሥራ የሚሠሩት አቶ ነስሩ አህመድ፣ በተሰጣቸው ፈቃድ ተረጋግተው እየሠሩ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና በቦታው በቋሚነት ተደራጅተው አነስተኛ ሱቅ በመስራት ዕቃቸውን ከሥራ ቦታ ወደቤት እንዲሁም ከቤት ወደሥራ ቦታ ከማመላለስ ቢገላገሉ ደስተኛ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ በጎዳና ላይ ከመነገድ የአሁኑ የተሻለ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡
በአዲስ አበባ ጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ይጠቅሳል፡፡በቢሮው መደበኛ ያልሆነ ንግድ ሥርዓት ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሉሌ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደሚገልፁት፤ ከሌሎችም ሀገር
ልምድ በመውሰድ የከተማዋን ገፅታ ሊመጥን የሚችል ዲዛይን ተነድፎ ሁለት መቶ ቦታዎች ለመያዝ ታቅዶ 148 ቦታዎች መለየቱንና መፅደቁን ይናገራሉ፡፡ ይህም የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ወይም ሕገወጦችን ሥርዓት ለማስያዝ ታስቦ በሁሉም ክፍለ ከተማ የተዘጋጀ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
አቶ ዳኛቸው፣ ‹‹በከተማው ምክትል ከንቲባ በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት ወጣቶች የሚደራጁበትን ቦታ ተረክበንና የሊዝ ውል ፈርመን 16 የነዳጅ ማደያ ኩባንያዎች እንዲሠሩ አስተላልፈናል፤ ማደያዎቹ ብዙ ወጣት የሚያሳትፉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ላቢያጆ፣ ጎሚስታ፣ ሻይ ቤት፣ መዝናኛና ሌሎችንም ዘርፍ ባቀፈ መልኩ ዲዛይን ተሠርቶ ጸድቋል፡፡›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ወደ ግንባታ እንደሚገባና በ2ኛው ሩብ ዓመት ተጠናቀው ወጣቶች እንዲሠሩ የሚመቻች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቦታ ይሰጣል ስለተባለ መደበኛ ነጋዴውም በሌላ ዘርፍ ላይ የተሰማራውም እንዲሁም ከክልል ድረስ ሰዎች የመምጣት ሁኔታ እንደነበር አቶ ዳኛቸው ተናግረው፤ ቢሮው ግን የከተማው ነዋሪ መታወቂያ ያለው በዚህ ዘርፍ ላይ ደግሞ መሰማራቱን እስከ ቀጣና ድረስ ወርዶ በማረጋገጥ ነዋሪዎችን በማሳተፍ ሥራው እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ወጣቱ ባለበት ክልል እና ከተማ ላይ እዚያው የሥራ ዕድል ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ስለተንቀሳቀሰ መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች ችግር መፍታትና ችግሩን መቅረፍ አይቻልም፡፡ የፌዴራል መንግሥት ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ወጣቱ ባለበት ክልል እና ከተማ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት ሁሉም ክልሎች እንቅስቃሴ ውስጥም ገብተዋል::
አቶ ዳኛቸው አክለውም ባለፈው ዓመት መደበኛ ያልሆነ ንግድን የጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሥርዓት ለማስያዝ በተደረገ ጥረት መስፈርቱን ያሟሉትን 19ሺ 600 ሰዎችን ቦታ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የሽግግር ጊዜ ፈቃድ የታክስ መለያ ቁጥር አውጥተው መክፈል የሚገባቸውን ግብር በሠሩት ልክ እየከፈሉ ሥራ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
አቶ ዳኛቸው፣ ‹‹የአርሶ አደሮች አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳት በግ፣ ፍየል፣ በሬ መሀል ከተማ መጥተው የሚሸጡበት ሁኔታ አለ፡፡ የጎዳና ላይ ንግድ ሕገወጥ ስለሆነ ሥርዓት መያዝ አለበት፡፡ የቁም እንስሳት መሀል ከተማ አራት ኪሎና ፒያሳ መሸጥ ስለሌለበት ይህ ሥርዓት መያዝ አለበት፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓመት በሠፊው ታቅዶ በአምስቱም መግቢያ ለአትክልትና ፍራፍሬ፣ ለእህል እንዲሁም ለቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት ለመሥራት ቦታ ተረክበን ዲዛይን ነድፈን ወደ ሥራ ገብተናል›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ ደንብ ፖሊስ የመሳሰሉት እንዲሁም ባለድርሻ አካላትም ለዚህ ሥራ ትኩረት ሰጥተው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሲወጡ አይስተዋልም፡፡ በሜክሲኮ አካባቢና በሌሎችም ቦታዎች ከአስፓልት ዳር ባሉ እግረኛ መንገዶች በሕገወጥ ንግድ የተጨናነቀ ሲሆን፣ ይህም እግረኛውን ለትራፊክ አደጋም ጭምር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ