አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት በኢንስፔክሽን አክሬዲቴሽን ‹‹iso፣17020››፣ 2012 ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አንዳስታወቀው፤ በኢንስፔክሽን ዘርፍ ዓለም አቀፍ እውቅናውን ለማግኘት በአፍሪካና በዓለም አቀፉ የላቦራቶሪ አክሬዲቴሽን ትብብር ከግንቦት 5 እስከ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ግምገማ ተደርጎበታል፡፡
በግምገማው የተገኙ ክስተቶችን አስተካክሎ ለገምጋሚ ቡድኑ በማቅረቡ በሕክምና ላቦራቶሪ ‹‹ISO 15189››2012 እና በፍተሻ ላቦራቶሪ ‹‹ISO/IEC17025››2017 ካገኘው በተጨማሪ በኢንስፔክሽን አክሬዲቴሽን ‹‹ISO/IEC 17020››፣ 2012 ዘርፍም ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት መቻሉን አስታውቋል፡፡
የኢንስፔክሽን ዘርፉ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት በተለይ አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ሌሎችም ምርቶችን የኢንስፔክሽን ሥራ እየሰሩ ሰርተፍኬት ለሚሰጡ ተቋማት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁሟል፡፡
በሕክምና፣ በፍተሻ፣ ላቦራቶሪ ከሚያዝያ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን የጠቆመው ጽሕፈት ቤቱ፣ ዓለም አቀፉ ገማጋሚ ቡድንም ጽሕፈት ቤቱ ይህን እውቅና ባገኘበት ወቅት በነበረበት ደረጃ ላይ መሆኑን በማረጋገጡ እውቅናው እንዲቀጥል መወሰኑንም አስታውቋል፡፡
ከመስከረም 8 እስከ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በኮትዲቯር በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ አክሬዲቴሽን ትብብር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ጽሕፈት ቤቱ በተገመገመባቸው አገልግሎቶች ተቀባይነት ማግኘቱንም ጠቁሟል፡፡
‹‹ይህን መሠረት በማድረግ በአገሪቱ በኢንስፔክሽን ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡና ከጽሕፈት ቤቱ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ የሆኑ የኢንስፔክሽን ተቋማት ጽሕፈት ቤታችን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ለመስጠት ያስችለቸዋልም›› ብሏል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው፣ በቀጣይም አሁን ያገኘውን ዓለም አቀፍ እውቅና ለማስጠበቅ በሰርተፍኬሽንና በካሊብሬሽን ዘርፎች የዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ታምራት ተስፋዬ