አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በያዝነው በጀት ዓመት ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የእግረኛ መንገዶች የመልሶ ግንባታ ሥራ እንደሚያከናውን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የሚገነባው መንገድ 50 ኪሎሜትር ይደርሳል፤ ከነዚህ መካከል 20 ነባር የእግረኛ መንገዶች የመልሶ ግንባታ ሥራ ይከናወናል። የግንባታዎቹ ሳይት ርክክብ እየተፈጸመ ሲሆን፣ ግንባታውም የፊታችን ጥቅምት ይጀመራል።
ግንባታው ከ20 በላይ በሚሆኑ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዞች አማካኝነት እንደሚከናወን አቶ ጥዑማይ ጠቅሰው፣ የእግረኛ መንገዶቹ ከሚከናወንባቸው ቦታዎች መካከል ከምኒልክ ሆስፒታል ስድስት ኪሎ፣ ከሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ቻይና ኮሌጅ፣ ከአክሱም ሆቴል አድዋ ድልድይ፣ ከሰሜን ሆቴል ሰሜን ማዘጋጃ፣ ከጎሮ አደባባይ አይሲቲ ፓርክ፣ ከሆላንድ ኤምባሲ የሺ ደበሌ፣ ከገላን ኮንዶሚኒየም ደብረ ዘይት መንገድ ያሉት እንደሚገኙበት አቶ ጥዑማይ አብራርተዋል፡፡
ነዋሪው እየተገነቡ ያሉ የእግረኛ መንገዶችንም ሆነ የአስፋልት መንገዶችን በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም መንገዶች ላይ የሚከናወኑ ሕገወጥ ተግባራትን በመከላከል መንገዶቹ ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲውሉ እና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ መተባበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የእግረኛ መንገዶች ግንባታ ዋናው ዓላማ እግረኞችን ከተሽከርካሪ አደጋዎች ለመከላከልና ደ ህ ን ነ ታ ቸ ው ን ለ መ ጠ በ ቅ ፣ ተ ሽ ከ ር ካ ሪ ዎ ች ን ም በምቾት እንዲሄዱ ለማስቻል መሆኑን ጠቁመው፣ በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚነግዱ ሰዎችን ሥርዓት በማስያዝ በኩል የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ