አዲስ አበባ፡- አስረኛው አዲስ ቢዩልድ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና የመሰረተ ልማት ኤግዚቢሽን ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
በኢትኤል ማስታወቂያና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና በቱርክ አጋሩ (Ladin Internatinal Fair and Congress Organization INC) አዘጋጅነት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንትብብር የሚካሄደው የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና መሰረተ ልማት ኤግዚቢሽን፤ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት በደማቅ ሥነሥርዓት መስከረም 28 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት እንደሚከፈት ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች የተውጣጡ አመራሮች ትናንት በዌስተርን ቤስት ፕላስ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል።
በመግለጫው እንደተመለከተው፣ በኤግዚቢሽኑ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቱርክ ፣ ከጀርመን ፣ ከሳውዲ አረቢያ ፣ ከህንድ ፣ ከኦማን ፣ ከታይላንድ ፣ ከኩዌት ፣ ከኢራን ፣ ከኳታር ፣ ከፓኪስታን ፣ ከዩክሬንና ቻይና በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግብዓት አቅርቦትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ 97 ኩባንያዎች ይሳተፋሉ።
የሲሚንቶና ኮንክሪት ምርቶች ፣ ኬብሎች ፣ የኢነርጂ ስርዓትና የቴሌኮም ሥራዎች ፣ የብረታ ብረት ፍሬሞችና ፣ የብረት ሥራ ውጤቶች ፣ ቀለም ፣ የፊኒሽንግ እቃዎች ፣ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች፤ እንዲሁም አዲስ ቴክኖሎጂ የሆነው post-tension and pre-stress steel technology እና ሌሎች ከ 22 በላይ የግንባታ ግብዓትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤቶች ለዕይታ ይቀርባሉ። የኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እየፈተኑ ባሉት የጥራት መጓደል ፣ የዋጋ መናርና የማጠናቀቂያ ጊዜ መጓተት ተግዳሮቶች ላይም ውይይት ይደረጋል።
በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ማበልጸጊያ ክፍል ኃላፊው አብዱ ጀማል የብረታ ብረት የአገር ውስጥ ምርት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከሚፈልገው 40 ከመቶ እንደማይበልጥ ጠቅሰው በዘርፉ የሚስተዋሉ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የአገር ውስጥ አቅምን ለመጠቀም መንግሥት አልሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤግዚቢሽኑ የውጭ ኩባንያዎች ወደ አገራችን ገብተው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂና ጥበቦች አገር ውስጥ ላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲያስተዋውቁ ያደርጋል ያሉት አቶ አብዱ የአገር ውስጥ ድርጅቶችም በውጭ አገራት ያለውን የቴክኖሎጂ እድገት ተረድተው ራሳቸውን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲያዘጋጁ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
ለውጭና አገር ውስጥ የዘርፉ ተዋንያኖች የልምድ ልውውጥ ማድረጊያና የገበያ ትስስር መፍጠሪያ መድረክ እንደሚሆን የታመነበትን ኤግዚቢሽን 6 ሺ ጎብኚዎች ይመለከቱታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
የትናየት ፈሩ