አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል የባህል፣ የትምህርትና የቋንቋ ልውውጥ ለማካሄድ የሚያስችል የወዳጅነት ማህበር ተመሰረተ። ማህበሩ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት በማጠናከር የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር እገዛ እንደሚያደርግም ተመልክቷል።
ኢትዮ ጃፓን ወዳጅነት ማህበር ትናንት በጊዮን ሆቴል ሲመሰረት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፤ ሁለቱ አገራት ቀደም ብሎ በነበሩ መንግሥታት የተጀመረ ወዳጅነት አላቸው። ይህ ወዳጅነት ለማጠና ከር እና የባህል፣ የትምህርት እንዲሁም የቋንቋ ልው ውጥ ለማካሄድ ማህበር መመስረቱ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ያግዛል።
በሁለቱ አገራት መካከል የባህል መመሳሰሎች አሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በምሳሌነትም የአርሷአደሩን የሥራ ትጋት ጠቅሰዋል። በሌላም በኩል ጃፓን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት እድል መስጠቷ የባህልና የቋንቋ ልውውጡን እንደሚ ያሳድገው አመልክተዋል። በጃፓን በኢትዮጵያ የአገራቱ ቀን መከበሩ ወዳጅነታቸውን ይበልጥ ማሳደ ጉን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኬ ማትሱንጋ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ህዝቦች ታሪካዊ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው በመጥቀስ፤ ህዝቦቹ በጋብቻ መተሳሰራቸው የባህልና የቋንቋ ልውውጡን እንዳጎለበተው ተናግረዋል። በኢትዮጵያና የጃፓን ቋንቋና ባህልን ለማሳደግና ለማስተዋወቅ ማህበሩ የጎላ ሚና እንዳለውም ገልፀዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሀረገወይን ገረሱ እንዳሉት፤ ማህበሩ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማሳደግ የተመሰረተ ነው። ማህበሩ የቋንቋ፣ የባህል እንዲሁም የቴክኖሎጂ ልውውጥ በሁለቱ አገራት እንዲኖር ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። የጃፓን መንግሥት የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ እገዛ እንዲያደርግ ማህበሩ ይሰራል። ወጣቶችም በማህበሩ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
መርድ ክፍሉ