መስቀል አደባባይ በታክሲ እየሄድኩ ነው፤ድንገት የመንገድ መብራት ለሰከንዶች አቆመን። ከታክሲው ረዳት መቆሚያ በኩል አሳዛኝ የታዳጊዎች ድምጽ ወደ ጆሯችን በመድረሱ ተሳፋሪው አይኑን ወደውጪ አፍጧል።
«የጎዳና ልጅ ነኝ፤
አባት እናት የለኝ፤
ሳገኝ እበላለሁ ሳጣም ብርድ ጠብሶኝ፤
አምስት አስር ትሁን እያያችሁ አትለፉኝ» የሚል ግጥም በዜማ ታጅቦ ለጆሯችን ደረሰ። ግጥሙ የአምስቱ የጎዳና ህጻናት የልመና ቃል ነው። ቀደም ብለው ህጻናቱ የትራፊክ መብራት የያዛቸውን ተሽከርካሪዎች መስታወት በመጥረግ ገንዘብ ይቀበሉ ነበር። አሁን ላይ ግን ልመናቸውን በግጥም አድርገዋል። የተወሰነው ተሳፋሪ ያለውን እየሰጠ የሌለው ደግሞ የሐበሻ የመጀመሪያ እርዳታ እየተባለ ስላቅ የሚሰነዘርበትን «ምጽ..» የሚል የሀዘን ድምጽ ያሰማል። ሌላውም «ምስኪኖች» እያለ በአይኑ ሸኝቷቸው ጉዞውን ይቀጥላል።
እኔ ግን ከታክሲው ስወርድ ህጻናቱን ዳግም እንደማገኛቸው እያሰብኩ ነበር። ምክንያቱም ከጎዳና ህይወት ስልጠና ተሰጥቶት ወደ ኪነጥበብ ሙያ የገባው አንድ ወጣት ያጫወተኝን ታሪክ ለማጣራት ጓጉቻለሁና። ወጣቱ ከጥቂት ወራት በፊት ጎዳና ህይወት ላይ ሳለ ሌሊት በመኪና የሚመጡ ማንነታቸውን የማያውቃቸው ሰዎች የአደንዛዥ ዕፅ መርፌ ሞክረውባቸው ገንዘብ ከፍለዋቸው እንደሚሄዱ አጫውቶኝ ነበር።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት ላይ ወደ ቦታው አመራሁ። ስታዲየም አካባቢ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች እሳት እየሞቁ ክብ ሰርተው ተቀምጠዋል። ከወራት በፊት ወጣቱ ያጫወተኝ ታሪክ እውነት መሆኑን ለማወቅ መምጣቴን ነግሬያቸው አብሬያቸው ተቀመጥሁ። እነርሱም ጉዳዩን በዝርዝር አጫወቱኝ።
ሳሚ ይባላል፤ ከሌሎቹ በአካል ከፍ ይላል። የ19 ዓመት ወጣት ነው። «ምን አዲስ ነገር አለው» ብሎ ንግግሩን ጀመረልኝ። እርሱ እንደሚለው፤ ማታ ማታ የጎዳና ልጆችን ፈልገው በመኪና የሚመጡ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች አሉ። የሚመጡት የአደንዛዥ እጹ ሻጭና ተጠቃሚዎች ናቸው። ሌሊት የጎዳና ተዳዳሪዎች በሚተኙበት ጥግ ስር ይመጡና ያገኙትን ሰው ይቀሰቅሳሉ። ከዚያም «መርፌ ልንሞክርነው?» የሚል ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ በእጽ የተሞላ መርፌ እንደሚወጓቸው ይናገራል።
እንደ ወጣቱ ገለጻ፣ ባለመኪናዎቹ አደንዛዥ ዕፁ መርፌውን የተወጋው ልጅ ላይ የሚያስከትላቸውን የባህሪና የአካል ለውጦች በንቃት በመከታተል ስለዕፁ ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ። ከዚህ በኋላ ትክክለኛ ዕፅ ከሆነ ገዢው ለዕፅ አዘዋዋሪው ክፍያውን ይፈጽማል። ሻጭም መሞከሪያ ለሆነው የጎዳና ተዳዳሪ አንድ መቶ ብር ወርውሮ ከአካባቢው ይሰወራል። የጎዳና ወጣቶችም ይህን ጉዳይ ተላምደውት ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የዕፅ መሞከሪያ ሆነው በርካታ ምሽቶችን እያሳለፉ ይገኛሉ።
በመስቀል አደባባይ አካባቢ ያገኘኋት ሰላም መኩሪያ የተባለች የጎዳና ተዳዳሪ እንደምትናገረው፤ ሌሊት የሚመጡ ግለሰቦቹ የሚያስቡት ስለራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው። የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ መርፌውን ከሞከሩ በኋላ ስለሚያስከትለው ችግር እና ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ምክር ሰጥተው አያወቁም። አንዳንድ ወጣቶች በርካታ ጊዜ መርፌው ስለተሞከረባቸው ሱስ ይዟቸዋል። ግለሰቦቹ ባልመጡ ቀን መርፌውን ፍለጋ እንቅልፍ በአይናቸው ሳይዞር እንደሚያድር ታዝባለች።
ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ በርካታ የጎዳና ወጣቶች የሱስ ተጠቂ መሆናቸውን የምትገልጸው ወጣት ሰላም፤ ዕፅ ሞካሪዎቹ ማንነታቸው የማይታወቅ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል አልተቻለም ትላለች። የጎዳና ተዳዳሪዎች ህይወት አስቸጋሪ በመሆኑ ማንኛውንም ነገር አድርገን ገንዘብ ማግኘት እንፈልጋለን። ከዚህ ችግር እንድንላቅቅ ከተፈለገ የአደንዛዥ ዕፅ ሞካሪዎቹን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋል እንደሚገባ ታሳስባለች። ለዘላቂ መፍትሄው ደግሞ የጎዳና ወጣቶችን ህይወት ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ትናገራለች።
የሥነ አዕምሮ ህክምና ባለሙያው አቶ ሰለሞን ጥበበ በበኩላቸው፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች በሚወስዱት የአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት ከአካላዊ ጉዳት ጀምሮ እስከ አዕምሮ የጤና መታወክ ያጋጥማቸዋል። በተለይ በምግብ እጦት እየተሰቃዩ አደንዛዥ ዕጹን ሲጨምሩበት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ የጤና ችግር ያስከትልባቸዋል። ከመጠን በላይ የመክሳት እና የመተንፈሻ አካላት ችግር ይደርስባቸዋል። ከሁሉም በላይ ግን አሳሳቢው ስነልቦናዊ ቀውሱ ነው። እራስን የማጥፋት ስነልቦናዊ ቀውስ ውስጥ የሚገቡ የሱስ ተጠቂዎች በርካቶች ናቸው። የጎዳና ተዳዳሪዎቹም ፈልገውም ሆነ ሳይፈልጉ በሚወስዱት እጽ ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ከሆነ፤ የጎዳና ተዳዳሪዎችም እንደማንኛውም ዜጋ በቂ የስነአዕምሮ ህክምና ሊሰጣቸው ይገባል። በተለይ ህጻን ልጅ ይዘው ዕፅ የሚጠቀሙት ስለእራሳቸውና ስለልጃቸው ጤና ተገቢው ምክር እና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። አብዛኞቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከ18ዓመት በታች በመሆናቸው በወቅቱ በቂ የባለሙያ ህክምና ከተሰጣቸው የችግሩን ግዝፈት ሊረዱ ይችላሉ። በዘላቂነት ግን ችግሩን ለመቅረፍ ከተፈለገ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ አሁን ካሉበት አስከፊ ህይወት ተላቀው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩበትን መንገድ መፈለግ ይገባል ይላሉ።
በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ደኅንነት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀምበር፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች የዕፅ መርፌ ከመወጋት እስከ ከፋ የጾታዊ ጥቃት እንደሚያጋጥማቸው ይናገራሉ። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አወቃቀር ግን የጎዳና ህጻናትን ችግር ለመፍታት የሚያስችል አለመሆኑ እንቅፋት ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ ህብረሰተቡ ጋር ወርዶ የሚሰራ ወረዳ ላይ የሚገኝ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያ አለመኖሩ ነው። በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ በወረዳ ደረጃ አንድ የማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኛ ቢኖር ማን ከአካባቢው እንደለቀቀ እና ማን ወደ ከተማ ሄዶ ጎዳና ላይ እንደወደቀ በቀላሉ ለማወቅ ይቻል እንደነበር ያስረዳሉ።
መረጃው ሲኖረው፤ ለምን? ብሎ ሊጠይቅ እና መፍትሄው ላይ መስራት ይቻል እንደነበር የሚናገሩት አቶ ፈለቀ፤ አሁን ግን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መስሪያቤት ስሙ ብቻ በፌዴራል ደረጃ ቢኖርም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ችግር ለመፍታት በሚያስችል አደረጃጀት አልተዋቀረም። በመሆኑም አወቃቀሩ ባለመስተካከሉ ችግሩን ለመከላከል እንዳልተቻለ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ፈለቀ ማብራሪያ፤ ተቋማት ተቀናጅተው በጉዳዩ ላይ አይሰሩም። በበርካቶችም ችግሮቹን የመከላከል ተግባሩ የሚኒስቴሩ ብቻ አድርገውታል። ለአብነት የዕፅ መርፌ የሚወጉትን የህግ አካላት ቢጠይቁ፤ የጤና ተቋማት ደግሞ የሚያደርሰውን ጉዳት አስመልክቶ ቢያስተምሩ የጉዳቱ መጠን እንደሚቀንስ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
በጌትነት ተስፋማርያም