ጄሶ ከጤፍ ዱቄት ጋር ተቀላቅሎ የተጋገረ እንጀራ በከተማው እየተሸጠ በነበረበት ሰሞን ያልተቀለደ የፌዝ ቀልድ አልነበረም፡፡ አንዱ የጄሶ እንጀራ በልቶ የተሰማውን ስሜት በፌስቡክ ሲገልፅ ‹‹ግድግዳ ላይ ተለጠፍ፣ ተለጠፍ ይለኛል›› ብሎ ነበር፡፡ እነዚህን ለሰው ልጆች ምግብነት የሚውሉ ጠቃሚ ነገሮችን ማለትም ዘይቶች፣ ዱቄት፣ የህፃናት ምግብ፣ ጁሶች፣ ኦቾሎኒ፣ በርበሬ፣ ጨውና ሌሎችም አይነቶች ምግቦችን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለጥቅም ማዋል የቱን ያህል በተጠቃሚዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ስለሚታወቅ ድርጊቱ ከሰብአዊነት ውጭ ነው፡፡
ባለፉት ጊዜያት በከፍተኛ መጠን ለብልሽት የተዳረጉና ለጤና እጅግ አደገኛ መሆናቸውን በምርመራ ለማወቅ የተቻለ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦች እንዲወገዱ መደረጋቸው፤ የምግብ አምራች ፋብሪካዎች፣ እነዚህን ምግቦችና መጠጦች ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡ ሁሉ መታገዳቸው ቢገለፅም፤ እነዚህ በቁጥጥር የተረጋገጡት ብቻ እንጂ ያልተደረሰባቸውንና ጉዳት እያደረሱ ያሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡
ከምግብ ግብአቶችና የታሸጉ ምግቦች በተጨማሪ በርካታ መድሃኒቶችም በሕገወጥ መንገድ ገብተው ለገበያ የቀረቡና የተበላሹ መሆናቸው፣ ታላቅ ቅናሽ አድርገናል በሚል የማጭበርበሪያ መንገድም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ በገበያ ላይ ውለው በመገኘታቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተበላሹ ምግቦችም ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረጉን በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በተደጋጋሚ ማሳሰቡና ርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡
እነዚህ የምግብ ሸቀጦች በሞጆ ደረቅ ወደብ፣ በቃሊቲና በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ጎጂነታቸው እየታወቀ መግባታቸው መንግሥት በሕገ- ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የሚወስደው እርምጃ ጠንካራ እና አስተማሪ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
ሕዝብን ለጉዳት በመዳረግ ጊዜያዊ ጥቅማቸውን በማሳደድ ላይ የሚገኙት አስመጪዎችና አከፋፋዮች እንዲሁም ቸርቻሪ ነጋዴዎች በማሸጊያቸው ላይ ገላጭ ጽሑፍ የሌላቸው፣ የተመረቱበትና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የማይታወቅ፣ አመራረታቸው ችግር ያለባቸው፣ በጤና ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትሉና የሚመረቱባቸው ስፍራዎች በማይታወቁት ሕገወጥ ምርቶች ላይ የቁጥጥር ሥርዓቱ ሲጠብቅባቸው አምራቾቹ የምርቶቻቸውን ስም በመቀየር በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ከፍተኛ ጉዳት አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ እንዲያስተካክሉ በምርቶቹ ላይ በተገለፀው አድራሻዎቻቸው ለማግኘትና የቁጥጥር ሥራ ለመሥራት ቢሞከርም ህጋዊ ስላልሆኑ አብዛኞቹን ባስመዘገቡት አድራሻ ማግኘት አልተቻለም።
ይህም መንግሥት የሕብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ተቆጣጣሪ አድርጎ ያደራጃቸው ተቋማት ጠናካራ ቁጥጥርና ክትትል አድርገው ሕገወጦችን ሥርዓት የማስያዝ ተግባራቸውን እንዳልተወጡ ያሳያል፡፡ ቀደም ሲል በርበሬ ከሸክላ ጋር ቀላቅለው ኅብረተሰቡን ሲጎዱና ያልታወቀ ተክል ጨምቀው ከዘይት ጋር ቀላቅለው ሲሸጡና የሰውን ልጅ ለሞት ሲዳርጉ ጠንካራና ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል ርምጃ ባለመወሰዱ ሕገወጦች ከጊዜ ወደ ጊዜ የልብ ልብ እየተሰማቸው የራሳቸው ወገኖች ላይ የጭካኔ ዱላቸውን ሲያሳርፉ ታይተዋል፡፡
ዛሬ ደግሞ አንዱ ስልታቸው ሲደረስበት ሌላ የምርት ስም በመቀየር በክፋት ሥራቸው መቀጠላቸው የቁጥጥሩን ደካማነት በመገመት በመሆኑ እነዚህ የሕዝብ ወገናዊነት የሌላቸውና በጥቅም የታወሩ ሕገወጦችን አደብ ሊያስገዛ የሚችል ጠንካራ ርምጃ በመውሰድ የህብረተሰቡን ሕይወት መታደግ የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ መንግሥት አፋጣኝ ርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም