አዲስ አበባ፡- ደንበኞች ወርሐዊ የቴሌኮም አገልግሎት ሂሳባቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መክፈል እንዲችሉ በኢትዮ ቴሌኮምና ንግድ ባንክ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን ለመጨመር የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የድህረ ክፍያ አገልግሎት ደንበኞች የአገልግሎት ሂሳባቸውን በቀላሉ መክፈል እንዲችሉ ተግባራዊ ከተደረጉ የክፍያ አማራጮች በተጨማሪ፤ ከመስከረም 24 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ ደንበኞች ወርሐዊ የቴሌኮም አገልግሎት ሂሳባቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ መክፍል እንዲችሉ ስምምነት ተደርጓል፡፡
የክፍያ አገልግሎቱ ሲ.ቢ.ኢ ብር፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ኤ.ቲ.ኤም ሲሆን፤ በቀጥታ ባንክ ማዘዣ እንዲሁም በማኛውም የባንኩ ቅርንጫፍ በአካባቢ በመቅረብ መክፈል እንደሚችሉ በመግለጫው ተጠቅ ሷል፡፡ በባንኩ በኩል ካሉት የመክፈያ አማራጮች በተጨማሪ ደንበኞች በአቅራቢያቸው በሚገኙ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በፍራንቻይዝ የሽያጭ ማዕከላትና አጋር የንግድ ማዕከላት እንዲሁም በይሙሉ ኤሌክትሮኒክ የአየር ሰዓት መሙያ አማካኝነት ወይም በሞባይል ካርድ ወርሐዊ የአገልግሎት ሂሳባቸውን መክፈል የሚችሉበት አማራጭ መኖሩም ተጠቁሟል፡፡
ቀደም ሲል በለሁሉ የክፍያ ማዕከል ሲሰበሰብ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ክፍያና በቅርቡ በህዳሴ ቴሌኮም ሲሰበሰብ የነበረው የአገልግሎት ክፍያ መቋረጡም በመግለጫው ተገልጿል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጨማሪም ሁሉንም አማራጮች በሌሎች ባንኮች በስፋት ለማስጀመር እየሰራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው