አዲስ አበባ፦ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዘመናዊ ህንፃ ለመገንባት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሰደው መሬት ላይ ግንባታ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ መሬቱን መነጠቁን ገለጸ።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቦጃ ታደሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ፍርድ ቤቱ በ2009 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘመናዊ የህንፃ ግንባታ ለማካሄድ ጥያቄ አቅርቦ ከአንድ ዓመት በኋላ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስም በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ከሒልተን ሆቴልና ከካዛንቺስ ጫፍ ከቤተመንግስቱ ፊትለፊት አንድ ሄክታር መሬት ካርታ በመረከብ ግንባታውን ለማካሄድ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል።
አቶ ቦጃ ‹‹የጠየቅነው አራት ሄክታር መሬት ሲሆን፤ የተሰጠን አንድ ሄክታር መሬት ነው። ይህም በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ከፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ለእኛ ከተሰጠው ቦታ አጠገብ የኪራይ ቤቶች የሚያስተዳድረው ህንፃ ስለነበር ከፌዴራል መንግስት ጋር በመነጋገር ወደ ፍርድ ቤቱ ማጠቃለል እንደሚቻል መተማመን ላይ በመደረሱ ነው›› ብለዋል።
ህንፃው ዘመናዊና የአገሪቱን ግጽታ የሚገነባ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ህንፃዎችን ተሞክሮ የተወሰደበት፣ የፍርድ ቤቱ አስተዳደራዊ ስራዎች የሚከናወኑበት ሬጂስትራር፣ የችሎት ክፍሎችን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የአቃቤ ህግና የጠበቆች አገልግሎት መስጫ ክፍሎችና ሌሎችን የያዘ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቦጃ ፤ ሁለት የተያያዙ ህንፃዎች ሲሆኑ፤ በወቅቱ የህንፃው ግንባታ አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ መገመቱን ያስረዳሉ፡፡
በ2011 በጀት ተይዞ ለማስገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ሳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግለሰብ፣ በመንግስትና በግል የተያዙ መሬቶች ላይ አሰሳ ሲያደርግ የተሰጣቸው መሬት መወሰዱን በመገናኛ ብዙኃን መስማታቸውን አቶ ቦጃ ይናገራሉ።
አቶ ቦጃ ጉዳዩን እንደሰሙ ከፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በጋራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮችን “መሬቱ የተወሰደው እኛ ተጠይቀን፤ ፈቅደንም አይደለም ፡፡ በወቅቱ መገንባት ባለመቻላችንም አይደለም። ምክንያቱም ከተሰጠን ዓመትም አልሞላውም” በማለት ስንጠይቅ ከኃላፊዎቹ ያገኘነው ምላሽ መሬቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን አለማወቃቸውን ገልጸዋል። “የማን መሆኑን ነው የምታውቁት” ብለን ስንጠይቅም “ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተሰጥቶ ለረጅም ጊዜ ያልገነባ መሆኑ እና ከዚያም በፊት ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት እንደተሰጠ መረጃዎች እንዳሏቸው ነው” የነገሩን ብለዋል። ቦታው ለፍርድ ቤቱ ሲሰጥ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይዞታ መክኖ ቢሆንም መረጃዎች በከተማ አስተዳደሩ የስራ ክፍሎች ከላይ እስከታች ባለመመጋገባቸው መወሰዱን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች፤ ለፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ፍርድ ቤቱ እንዳይሰጠው ካለመፈለግና ከፍርድ ቤቱ የበለጠ ሌላ አሳሳቢ ነገር ኖሮ አለመሆኑን ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅር ተከለ ኡማ፤ የፍርድ ቤቱና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ጭምር ስለተወሰደ ወደ አቧሬ በሚወስደው መንገድ ካምፑ አካባቢ ጎን ለጎን ለመገንባት እያጸዱ በመሆኑ ሰፋ ያለና ከዚህ ያላነሰ ቦታ እንደሚሰጠን ቃል ተገብቷል ያሉት ኃላፊው፤ ‹‹ከእኛ መደረግ የሚገባውን ሁሉ አድርገናል። በደብዳቤ ጭምር ጠይቀናል። እስካሁን ደብዳቤ አልተጻፈልንም፤ ቦታውም አልተሰጠንም፤ መቼ እንደሚሰጠንም አናውቅም፤ በቀጣይ ከኃላፊዎቹ ጋር እንነጋገራለን›› ብለዋል።
አቶ ቦጃ፤ የከተማ አስተዳደሩ የሰጠውን ካርታ መንጠቅ የሚገባው በወቅቱ መገንባት ባይቻል እንደሆነ መመሪያና ደንቡ እንደሚያዝዝ፤ ህጉ ግን ተግባራዊ እንዳልሆነ አመላክተዋል።
እንደ አቶ ቦጃ ገለፃ፤ ፍርድ ቤቱ በአገሪቱ ተጠቃሽ ተቋም ቢሆንም ኢትዮጵያን የሚገልጽ ዘመናዊና ለዳኝነት ታስቦ የተሰራ ዘመን ተሻጋሪ ህንፃ የለውም። የዳኝነት ስራውን ማዕከል ተደርጎ የተሰራ ህንፃ ባለመኖሩ ፍርድ ቤቱ በህገ መንግስቱ ዳኝነት በግልጽ ችሎት መካሄድ እንዳለበት የሚያስቀምጠው ተግባራዊ እየሆነ አይደለም። በግልጽ ችሎት ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እየተጋፋ ነው። ጊዜውን የሚመጥን፣ ከጉዳዮች ፍሰት፣ ከዳኞች ቁጥር ጋር የተመጠነ ባለመሆኑ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎት ለመስጠት አልተቻለም።
የከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ ምላሽ እንዲሰጡ ለአንድ ሳምንት ያህል በተንቀሳቃሽ ስልክ ብንደውልም ሊያነሱ አልቻሉም። በመጨረሻም ጉዳዩን በጽሁፍ ገልጸንላቸው በኋላ እደውላለሁ ቢሉም ምላሽ አልሰጡንም። ከዚህም በተጨማሪ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊውን ኢንጅነር ሽመልስን ለማግኘት ብንጥር ስልካቸው ዝግ ሆኖብናል። በጉዳዩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን።
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኸኝ