አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የጎንዮሽ ጉዳት ሪፖርት ማድረጊያ የኤሌክትሮኒክስ እና የሞባይል መተግበሪያ ይፋ አደረገ።
ከትናንት በስቲያ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደው መድረክ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሔራን ገርባ እንዳሉት፤ ደህንነታቸው ሳይታወቅ ለገበያ የሚቀርቡ የመድኃኒት ምርቶችን ለመቆጣጠወር ሜድሴፊቲ /MedSaftey/ የተባለ የኤሌክትሮኒክ ሪፖርት ማድረጊያ እና የሞባይል መተግበሪያ ተግባራዊ ተደርጓል። ይህም የመድኃኒት ጥራትና ፈዋሽነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የመድሃኒት አጠቃቀም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ሲሆን፤ በቀጣይም አሁን የተዘጋጀውን የኤሌክትሮኒክስ ሪፖርት ማድረጊያ እና የሞባይል መተግበሪያ ተግባራዊ በማድረግ የመድኃኒት ጥራትና ፈዋሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ሪፖርት ማድረጊያ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ድረ ገፅ www.fmhaca.gov.et ላይ የሚገኝ ሲሆን ለሞባይል መተግበሪያው ለአይፎን ስልክ ተጠቃሚዎች አኘስቶር ላይ ለአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች ፕለይ ስቶር ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ፕሮግራሙን ይፋ ያደረጉት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደገለፁት፤ የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ የመድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ለ100 ሺ ህዝብ 200 ሲሆን በኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም ከ20 ሺ ህዝብ 1400 የመድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ሪፖርት ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
ዛሬ የተመረቀው የኤሌክትሮኒክ ሪፖርት ማድረጊያ እና የሞባይል መተግበሪያ ይህንን ችግር ለመቅረፍና የመድኃኒት ጥራትና ቁጥጥርን ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኸኝ