አዲስ አበባ፦ በ2011ዓ.ም ሁሉንም አይነት አደገኛ እጾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በተያያዘ ተሳታፊ የሆኑ 80 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ። በአዲስ አበባ ከተማ ለመልሶ ማልማት በተከለሉና በሻሸመኔ አካባቢ የተተከሉ እፆችን እንዲወገድ ማድረጉንም ጠቁሟል።
በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የአደገኛ ዕጽ ቁጥጥር ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መንግስተአብ በየነ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ባለፈው ዓመት ከሐምሌ አንድ ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ሁሉንም አይነት አደገኛ እጽ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
ኮኬይን 186 ኪሎ ግራም፣ ሄሮይን ዘጠኝ ነጥብ ሁለት ኪሎ ግራም፣ ካናቢስ አንድ ሺ አንድ መቶ አራት ኪሎ ግራም በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በተያያዘ 80 ሰዎችን በቁጥጥር ሰር ማዋሉን ተናግረዋል። የወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊዎቹ የ17 የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፤ 57 ወንዶች እና 23 ሴቶች መሆናቸውንም አክለው ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማም ፈርሰው ለመልሶ ግንባታ እና ለልማት ታጥረው በቆዩ ቦታዎች ግንባታቸው ባለመከናወኑ እንዲሁም እንደመደበቂያም ስለሚጠቀሙባቸው በእነዚህ ቦታዎች የአደገኛ ዕጽ ብቅለቱ አልፎ አልፎ እንደሚታይ ኮማንደር መንግስተአብ ተናግረዋል። ‹‹አደገኛ ዕጽ ብቅለት በተጨባጭ እየደረስንበት እያስወገድን እንገኛለን። አሁን በክረምቱ ወራት እንኳን ቂርቆስ፣ ኮልፌ እና ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ሁለት ሶስት ጊዜ አጋጥሞን በተደጋጋሚ አስወግደናል›› ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በመልሶ ማልማት ታጥሮ የተከለለ አንድ ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንዲሁም በሻሸመኔ አካባቢ ወደ ሰባት ሄክታር መሬት ላይ ተገኝቶ እንዲወገድ መደረጉንም አብራርተዋል። ሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች ብቅለቱ የታየው እስከ 30 እግር የሚለካ እንደሆነ ነው የገለጹት።
ከእዚህ ወንጀል ድርጊት ጋር ተያይዞ የተያዙ ሰዎች የሉም ያሉት ኮማንደሩ፤ የክፍሉ የክትትል ሰዎች በሚያደርጉት ጥናት የሚደረስበት እንዲሁም በሰዎች ጥቆማና መረጃ የምናገኘውን እናስወግዳለን ብለዋል።
እንደኮማንደር መንግስተአብ ማብራሪያ፤ እነዚህ ሰዎች ሲያበቅሉ የሚንቀሳቀሱት ሁኔታዎችን አመቻችተው ነው። በመሆኑም ከአብቃዮቹ ጋር ተያይዞ እስካሁን ያጋጠመን ነገር የለም። ቦታው ለመልሶ ማልማት የተከለለ በመሆኑና ከዕይታ ውጪ ሆነው ድርጊቱን ስለሚፈጽሙም አልተጋለጡም። ሆኖም የተመረቱ ምርቶችን ሲያከፋፍሉ፣ ሲቸረችሩና ሲያዘዋውሩ ከእነኤግዚቢታቸው እንይዛለን።
ሰዎች አደገኛ ዕጹን የሚጠቀሙባቸው በብዛት ሺሻ ቤቶች፣ ጫት መቃሚያ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች ናቸው ያሉት ኮማንደር መንግስተአብ፤ በየጎዳናው የሚቸረችሩና የሚጠቀሙ ሰዎችም እንዳሉ ጠቁመዋል። የክትትል ክፍላቸው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥናት በማካሄድና በጥናት ውጤቱ መሰረትም ኦፕሬሽን እንደሚካሄድ ተናግረዋል። በድርጊቱ የሚሳተፉ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎች እና ተጠቃሚዎች በቁጥጥር ስር እንደሚውሉም ጠቁመዋል።
የወንጀል ድርጊቱን ማስቆም የሚቻለው በቅንጅት የመከላከል ስራ ሲሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል። በእዚህ ድርጊት በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ማካበት የሚፈልጉ ግለሰቦችና ህገ ወጥ ተጠቃሚዎች ከድርታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
ዘላለም ግዛው