አዲስ አበባ፦ የመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በ2011 በጀት ዓመት ባደረጋቸው ማሻሻያዎች የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት መሻሻሉን አስታወቀ። ኤጀንሲው በተጠናቀቀው በጀት አመት የእቅዱን 92 ነጥብ 85 በመቶ ማሳካቱንም ገልጿል፡፡
የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አድና በሬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል መድሃኒቶቹ እያሉ በኤጀንሲውና በጤና ተቋማት መካከል ባለው የመረጃ ልውውጥ ክፍተት በኤጀንሲው መጋዘን መድሃኒት እያለ የአቅርቦት ችግር እንደነበርና በ2011 በጀት ዓመት የፈጣን ምላሽ ስርዓት ተዘርግቶ የ74 ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች እና የኤጀንሲው አስተባባሪዎች በየሳምንቱ በመገናኘት በኤጀንሲው ያለው የመድሃኒት አቅርቦት ክፍተት እየተለየ የመድሃኒት አቅርቦቱ ተደራሽ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ አድና ገለፃ የአሰራር ማሻሻያውን ተከትሎ በጤና ተቋማት በጀት ከሚገዙት 1ሺ 272 አይነት መድሃኒቶች 90 ነጥብ 7 ከመቶ፣ እንዲሁም በጤና ፈንድ ፕሮግራም ከሚቀርቡ አንድ መቶ አንድ መድሃኒቶች 95 በመቶ ማሰራጨት ተችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የህይወት አድንና መሰረታዊ መድሃኒቶች ተደራሽነት ከ65 በመቶ ወደ 95 በመቶ አድጓል።
እንደ ወይዘሮ አድና ማብራሪያ በዚህ አሰራር የተነሳ ሆስፒታሎች ለውጥ መምጣቱን የመሰከሩ ሲሆን ስራውም ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል። ኤጀንሲውም ማሻሻያው በቀጣይ የሚያስፈልገውን መድሃኒት ለመለየት፣ ክምችቱን ለማሳለጥና ቅርንጫፎቹም ዝግጁ እንዲሆኑ ማገዙንና መድሃኒቶቹን ከአንዱ ወደ ሌላው አዟዙሮ ለመጠቀምም ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ተናግረዋል። እንደ አገርም የመድሃኒት እጥረት እንዳይፈጠር፤ በጉዞ ላይ ያሉት መድሃኒቶችም ቶሎ እንዲገቡ ማድረጉንና ይህም ከዚህ ቀደም በዋና መስሪያ ቤት መድሃኒት እያለ ያጋጥም የነበረውን እጥረት ለመቅረፍ እንዳስቻለ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የህክምና መሳሪያዎች ኬሚካሎችን (ሪኤጀንት) የተለያዩ ድርጅቶች ስለሚያመርቷቸው በወቅቱ ለማቅረብ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ያሉት ወይዘሮ አድና ከዚህም በተጨማሪ የመሳሪያ ገጠማና ጥገና ለማድረግ የሚያስቸግርበትና መሳሪያዎቹም ለረጅም ጊዜ የሚቆሙበት ሁኔታ ነበር ብለዋል።
ይህን ለማስተካከል የህክምና መሳሪያዎችን በነፃ አቅርቦ ኬሚካሎቹን ለሶስት ዓመት መሳሪያውን ካቀረበው ድርጅት ለመግዛት የሚያስችል አሰራር መፈጠሩንና ለስመንት የሚባል የግዥ ስልት ነድፈው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሰረት ከዚህ በኋላ የሚገዙት የህክምና መሳሪያ ሳይሆን ሬኤጀንት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱም መሳሪያውን፣ ተከላውንና ጥገናውን እንደሚያከናውንና በዚህ መልኩም በ50 ሆስፒታሎች የመሳሪያዎች ተከላ መከናወኑን የገለፁት ወይዘሮ አድና ቀሪዎቹም በአጭር ጊዜ እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ አሰራር ምርመራን ቀልጣፋ በማድረግ እንግልትን ይቀንሳልም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በብዛት የማይፈለጉና ህይወት አድን የሆኑ ነገር ግን አቅራቢ የማይገኝላቸውን መድሃኒቶች በተደጋጋሚ ጨረታ ያወጡ እንደነበርና በዚህ የተነሳ የመድሃኒት የመቆራረጥ ችግር ያጋጥም እንደነበር ጠቅሰው፤ ይህን ችግር ለመቅረፍም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ 350 መድሃኒቶችን በረጅም ጊዜ የግዢ ስምምነት /በፍሬምወርክ አግሪመንት/ ለመግዛት ከሶስት መድሃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ለሶስት ዓመት መዋዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኤጀንሲው በ2011 በጀት ዓመት ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ገዝቶ አስራጭቷል ያሉት ወይዘሮ አድና ይህም ከእቅዱ አንጻር ሲታይ 92 ነጥብ 85 በመቶ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የመድሃኒት ብክነት ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ የዘንድሮው ዓመት ብክነትም 1 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኸኝ