አዲስ አበባ፦ የስታቲስቲክስ መረጃ አቅርቦትን ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በዓለም ባንክ ድጋፍ በ”ስታቲስቲክስ ለውጤት ፕሮጀክት” አማካይነት የመረጃ አሰባሰቡንና አቅርቦቱን ተደራሽና ተጠቃሚዎች በቀላሉ የሚያገኙት ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በአስር ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደተጀመረ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አፈጻጸሙ ታይቶ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በመጨመሩ በ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስድስት ባለ አራት ወለል ህንጻዎችን በተለያዩ ክልሎች መስራት እንደተቻለም ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በዋናው መስሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የስልጠና ማዕከል እና ቤተመጻህፍት እንደተገነባም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በቴክኖሎጂ በመታገዝ የጠራ መረጃን ለመሰብሰብ የሚያስችል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን የማጠናከር ስራ መከናወኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለተቋሙ ስራ የሚመጥኑ ባለሙያዎችን በማብቃት ቀላልና ቀልጣፋ እንዲሁም ተደራሽ መረጃን ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ ስራዎች ደግሞ ኤጀንሲው የተጣለበትን ከባድ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ከማገዛቸውም በላይ የሚሰበሰቡ መረጃዎች የጠሩና ትክክለኛ እንዲሆኑ እገዛ እንዳላቸው ነው የተናገሩት።
ኤጀንሲው መረጃ ስለተገኘ ብቻ ይዞ አይቀርብም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ መጀመሪያ ትክክለኛነቱ ከሲስተም፣ ከአዘገጃጀትና ከአሰባሰብ ዘዴ (ሜተዶሎጂ) አንጻር ይመሳከራል ፤ በማስከተልም መረጃው መስክ ላይ የሚሰበሰብበትና የሚቀነባበርበት ስርዓት ይቃኛል ብለዋል፡፡ እነዚህን አካሄዶች ዘመናዊ የማድረግና የጥራት መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ዝግጁ የማድረግ ስራም እየተከናወነ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
“ቀድሞ በወረቀት ይሰበሰቡ የነበሩ መረጃዎችን በሙሉ በዘመናዊ ስልኮች (ታብሌት) እንዲቀየሩ አድርገናል፤ ይህ ደግሞ የስራው ጥራት እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ በፊት በወረቀት ተሰብስቦ ወደ ማዕከል ገብቶ በኮምፒውተር ተገልብጦ የሚሰሩ ስራዎችን በማስቀረት በቀጥታ ግንኙነት (ኦን ላይን ) መረጃውን አቀነባብሮ ማውጣት አስችሏልም “ ብለዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ባለስልጣኑ በዚህ ልክ ዘመናዊ መሆኑ የስርጭት ሁኔታውን በማቀላጠፍ ሰዎች መረጃን በፈለጉት ጊዜ እንዲያገኙ ከማገዙም በላይ የመረጃዎች ጥራት፣ ወቅታዊነትና ተደራሽነት እንዲጠበቅ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ።
የስታቲስቲክስ መረጃ አሰባሰብና ስርጭት በየትኛውም ጊዜ ሊቆም የማይችልና ቀጣይነት ያለው ተግባር በመሆኑ በየዓመቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ለጥናት በጀት የሚመደብ ሲሆን፤ የተቋሙን አቅም ለመገንባት ለጋሽ አካላት የሚሰጧቸው ድጋፎችም ለተቋሙ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም “ስታቲስቲክስ ለውጤት “የተሰኘው ፕሮጀክት ስራውን ቢያጠናቅቅም ኤጀንሲው ካሉት 25 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 19ኙ ህንጻ ስለሚያስፈልጋቸው ሌሎች ለጋሽ አካላትንና ፕሮጀክቶችን የማፈላለግ ስራ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
ሁሉንም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማገናኘት አስፈላጊ በመሆኑም ይህንን ለማድረግ ከልማት አጋሮች ጋር የተጀመሩ ስራዎች በቀጣይ የሚገለጹ እንደሚሆንም ጨምረው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
እፀገነት አክሊሉ