አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢ.ሰ.ማ.ኮ) አስታወቀ፡፡
ኮንፌደሬሽኑ ከአሜሪካ የትብብር ማዕከል ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ሰራተኞች በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ በሚኖራቸው ሚናና መርሆች ላይ ያተኮረ ውይይት ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደበት ወቅት የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ እንደተናገሩት፤ ተቋማቸው አገራዊ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ስራዎችን ማከናወን ጀምሯል፡፡ በዚህም ከምርጫው በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫው በኋላ የሚኖሩትን ድርሻዎች የሚያመለክት አቅጣጫ አስቀምጦ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች መብታቸው ተከብሮ በሰላማዊ ሁኔታ ፕሮግራማቸውን ማቅረብ እንዲችሉ መድረኮችን ማመቻቸት፣ ምርጫው ግልፅና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ መደገፍና ማበረታታት፣ ለአባላቱ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት መስጠት እንዲሁም ሰራተኛው ያመነበትን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት እንዲመርጥ ጣልቃ አለመግባት ኮንፌደሬሽኑ በምርጫው ሂደት ወቅት ለመተግበር ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሸናፊነቱን ያረጋገጠው የፖለቲካ ፓርቲ የሕዝብ ድምፅ ተከብሮ ስልጣን እንዲረከብ መደገፍ የኮንፌደሬሽኑ ድህረ-ምርጫ አቅጣጫ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ሠራተኞች የሰራተኛውን በነፃ የመደራጀት መብት፣ የስራ ዋስትናና የሙያ ደህንነትን የማክበርና የማስከበር፣ በስራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ የመተግበር እንዲሁም ዘላቂ ሰላም በማስፈን ድህነትን የመቅረፍና ብልፅግናን የማምጣት ዓላማዎች ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጥ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት የኮንፌደሬሽኑ ጠቅላይ ምክር ቤት ለምርጫው ሂደት ያስቀመጣቸው የኮንፌደሬሽኑ መርሆች እንደሆኑ አቶ ካሣሁን ገልፀ ዋል፡፡
አቶ ካሣሁን ‹‹ሰራተኛው ሰርቶ መኖር የሚችለው ሰላም ሲሰፍን ብቻ በመሆኑ ኮንፌደሬሽኑ ለአባላቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ጨምሮ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ሌሎች ተግባራትንም ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል›› ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2012 ዓ.ም
አንተነህ ቸሬ