የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት በአራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ያካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው ከወትሮው የተለየ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ለዕለቱ ስብሰባው ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የጋለ ክርክር አድርገውበታል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አቶ አፅብሃ አረጋዊ፣ የኮሚሽኑ ረቂቅ አዋጅ የምርመራ ሂደት የሕዝብ ውይይት መድረክ የተዘጋጀበት ባለመሆኑ ተገቢነት የሌለው የረቂቅ አዋጅ የምርመራ ሂደትን የያዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፣ ረቂቅ አዋጁ ብዙ የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎችን ይጥሳል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንንና የማንነት ጥያቄ አጠያየቅ ሥርዓትንም ይጋፋል፡፡ የመንግሥት አካላትን የአስፈፃሚነት ስልጣን በመጋፋትና ሕዝቦች የስልጣን ባለቤት እንዳይሆኑ በመንፈግ ሌሎች ችግሮችን ይፈጥራል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ክልሎችን ባለማሳተፉ ትልቅ ክፍተት አለበት፡፡ ሰፋፊ የሕዝብ ሃሳብ ማሰባሰቢያ መድረኮች ሊዘጋጁ ሲገባ የረቂቅ አዋጁ የምርመራ ሂደት ግን እነዚህን ቅደም ተከተሎች ያልተከተለ ነው፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ገለልተኛ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸውም አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ ረቂቅ አዋጁ መሰረታዊ ችግር ያለበት በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ማፅደቁ ቀላል ሊሆን ይችላል፤ውጤቱ ግን አደገኛ ነው፤በኋላ ችግር ያመጣል›› ብለዋል፡፡
አቶ ዊንታ ተክሉም ረቂቅ አዋጁ መጽደቅ የለበትም ብለው የመከራከሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ ረቂቅ አዋጁ ለክልሎች የተሰጠውን መብት የሚጥስ፣ ሕግን ያልተከተለና የሕገ-መንግሥቱን ምሰሶዎች የሚንድ በመሆኑ ሊፀድቅ አይገባውም፡፡ የማንነት ጥያቄዎች መቅረብ ያለባቸው ለክልሎች ሆኖ ሳለ በኮሚሽን እንዲታዩ መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡
‹‹ ክልሎች ስለኮሚሽኑ አስፈላጊነት ሳይጠየቁ በመቋቋሙ ኮሚሽኑን ‹አናስገባም› ቢሉ ችግር አይፈጠርም ወይ?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ረቂቅ አዋጁ ሕዝቡ ሳይወያይበትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሃሳብ ሳይሰጡበት ከፀደቀ ችግር ይፈጠራል›› ያሉት አቶ ዊንታ፣ ምክር ቤቱ የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ እንዳያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ አጥናፉ ጌጡ የረቂቅ አዋጁን መጽደቅ ከደገፉት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳስረዱት፣ ረቂቅ አዋጁ የትኛውንም የመንግሥት አካል ስልጣንና ተግባር የሚጋፋና የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚጋፋ ባለመሆኑ ተገቢነት ያለውና ወቅታዊ የሆነ እርምጃ ነው፡፡ ኮሚሽኑ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ችግሮችን በማጥናት የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ የሚያቀርብ በመሆኑ በአገሪቱ የተሟላ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
‹‹የሕገ መንግሥትን አለመከበር በተመቸን ጊዜ ልናነሳውና ልንጥለው እንፈልጋለን እንጂ ሰዎች ሲደበደቡና ሲሰቃዩ ‹ሕገ መንግሥት ተጣሰ› አላልንም፤በሕገ መንግሥት ሽፋን የተካለሉና የማንነት ጥያቄ ያላቸው አካባቢዎች ስላሉ ‹ኮሚሽኑ የነዚያን አካባቢዎች ጉዳይ ይመረምራል› የሚል ስጋት ስላለ ነው፤በእርግጥም መመርመር አለበት፤ ‹ችግር ያመጣል› የሚል ኃይለቃልና ማስፈራሪያ መጠቀም ተገቢ አይደለም›› በማለት ረቂቅ አዋጁ እንዳይፀድቅ መከራከሪያ ያቀረቡትን የምክር ቤት አባላት ሃሳብ ተቃውመዋል፡፡
‹‹ነፃ ተደርገው የተደራጁ ተቋማት ምን ያህል ነፃ እንደነበሩ ምክር ቤቱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብም ታዝቧቸዋል፡፡ ዛሬ ግን የሌሎች ተቋማትን ስልጣን በማይጋፋ መልኩ የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያመጣ ተቋም በማቋቋም ለሕዝብ ችግር መፍትሄ መስጠት ለምን ኃጥያት ይሆናል›› ያሉት አቶ አጥናፉ፣ ከኮሚሽኑ ነፃነትና ገለልተኛነት ጋር ተያይዘው የተነሱ ጥያቄዎችም የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ከመጽደቅ የሚያግዱ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡
አቶ ሻምበል ነጋሳም የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን ደግፈዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ ረቂቅ አዋጁ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች እንዲሁም የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በዝርዝር የተመለከቱትና ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከሌሎች ሕጎች ጋር የማይጣረስ በመሆኑ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ የወሰንና የማንነት ጉዳዮች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ችግሮችን ስለፈጠሩና ኮሚሽኑ በጥናት ላይ ተመስርቶ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ የሚሰራ በመሆኑ የኮሚሽኑ መቋቋም ችግር አይፈጥርም፡፡ ‹‹ረቂቅ አዋጁ በግልፅ የተቀመጡ ሃሳቦችን የያዘ ነው፤ሕዝብን ያላሳተፈ አሰራር ነው ተብሎ የቀረበው ሃሳብም አሳማኝ አይሆንም›› ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ እንዳይቋቋም ከማድረግ ይልቅ ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ሥራውን ሲሰራ በጥንቃቄ እንዲያከናውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የተሻለ እንደሆነም አቶ ሻምበል አሳስበዋል፡፡
‹‹ረቂቅ አዋጁ በሕገ መንግሥት ሽፋን ስንሰራቸው ለነበሩ ስህተቶች ምህረት የምናገኝበት ነው›› ያሉት ወይዘሮ ገነት አብደላ፣ እርምጃው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመካስና ሕገ-መንግሥቱን ለማስከበር የወጣ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ የኮሚሽኑ መቋቋም እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በኋላ ዛቻና ማስፈራሪያ ይበቃዋል፤እንዲያውም ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልጋል›› በማለት ‹‹የኮሚሽኑ መቋቋም ችግር ያመጣል›› ያሉትን የምክር ቤት አባላት ሃሳብ ነቅፈዋል፡፡
በአባላቱ መካከል የሞቀ ክርክር ከተካሄደ በኋላ ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ ኮሚሽኑ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች እንደማይጥስና አማራጭ ምክረ ሃሳቦችን የማቅረብ እንጂ በራሱ ውሳኔ የማይሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሰብሳቢው እንዳሉት፣ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረስ አይደለም፡፡ አንድ ክልል እውቅናና ድጋፍ ያልሰጠው ሕግ ተፈፃሚ አይሆንም ከተባለ ይህ ዓይነቱ ስርዓት ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ሥራውን ሲያከናውን ተፅዕኖ ሊደረግበት አይገባም፡፡
‹‹ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ጥያቄውን ያቀረቡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የሌሎች የመንግሥት አካላትን ስልጣን ይጋፋል ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ የቋሚ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ውይይት ላይ ተጋብዞ ስልጣኔን ይጋፋል የሚል ተቃውሞ አላቀረበም›› ብለዋል፡፡ በቀጣይም የኮሚሽኑ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ለምክር ቤቱ አቅርበው እንደሚሾሙ አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም 33 የምክር ቤቱ አባላት የተቃወሙትና አራት አባላት ደግሞ ድምፅ ከመስጠት የታቀቡበት ሰፊ የሃሳብ ክርክር የተካሄደበት ረቂቅ አዋጅ፣ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በዕለቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት አገራዊ ተልዕኮውን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ ያስችለዋል ብሎ የተወያየበትን የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀትን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአን ድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጭ ድምጽ አጽድቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
በአንተነህ ቸሬ