
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ብዙ ውጣ ውረድ አልፏል። ሄድ መለስ የሚለው የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደትም በርካታ ተስፋዎች እንዳሉት ሁሉ ስጋቶችም እንደተደቀኑበት ምሁራን ይገልጻሉ።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ገመዳ ፈቃዱ እንደሚሉት፣ ዴሞክራሲ የሚለካው አገሪቱ በህግና በህገ መንግሥት ብቻ ስትተዳደር ነው። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ህግና ህገ መንግሥት ቢኖርም ለገዥዎችና ለንጉሱ የወገነና የተጻፈ በመሆኑ ዴሞክራሲ ይቅርና ምልክቶቹም አልነበሩም።
በተመሳሳይ ደርግም ወደስልጣን ከመጣ በኋላ በአጼው ዘመነ መንግሥት ከወጡት ሁለት ህገ መንግሥቶች የተሻለ ህገ መንግሥት ወጥቶ ሥራ ላይ ቢውልም አገሪቱ የምትተዳደረው በኮሚቴ በመሆኑ የዴሞክራሲ ምሰሶዎች የሚባሉት የህዝብ የስልጣን የስልጣን ባለቤትነት፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት፣ የህግ የበላይነትና የፍርድ ቤት ነጻነት ጥያቄ ውስጥ የወደቁ ነበሩ ይላሉ።
እንደ ዶክተር ገመዳ ገለጻ የዜጎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ስላልተመለሱ በተካሄደው የትጥቅ ትግል ደርግ ሊወድቅ ችሏል። ደርግ ከወደቀ በኋላ በሽግግር ቻርተሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ታይቷል። በ1987 ዓ.ም የዴሞክራሲ ምሰሶዎች ተብለው የሚጠሩት ማለትም የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት፣ የፍርድ ቤት ነጻነትና መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችንም ጭምር ያካተተ አሁን በሥራ ላይ ያለው ህገ መንግሥት ሊጸድቅ ችሏል።
ያም ሆኖ ግን ህገመንግሥቱ እነዚህን የዴሞክራሲ መርሆዎች ቢይዝም አተገባበሩ ላይ ተጨባጭ ክፍተቶች መስተዋላቸው የዴሞክራሲ ምህዳሩ ሊጠብ ችሏል ። በተለይ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ ወዲህ ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲን ለመተግበር ያለው ተነሳሽነት ውስን መሆኑን ዶክተር ገመዳ ይጠቅሳሉ።
ለአብነትም የመንግሥት ስልጣን የያዘው አካል ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ እነሱ በሚፈልጉበት መልኩ መጠቀም ታይቷል። በተመሳሳይ ህዝቡም ዴሞክራሲን እንደ ባህል ከመያዝና ከማዳበር ይልቅ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን አሳልፎ ሲሰጥ ተስተውሏል። በዚህ ምክንያት የዴሞክራሲ ባህል አልጎለበተም፤ የፖለቲከኞች ቁርጠኝነትም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ዴሞክራሲ በአንድ ሌሊት የሚመጣ ሳይሆን በሂደት እየዳበረና እየሰፋ የሚሄድ ነው የሚሉት ዶክተር ገመዳ ለምሳሌ በአሜሪካ ከ200 ዓመት በፊት የተጀመረ ዴሞክራሲ ነው እየጎለበተ ሄዶ ዛሬ ላይ ተጠቃሽ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የቻሉት ይላሉ። እንዲሁም ጥሩ የዴሞክራሲ መስመር ላይ የሚገኙት ጀርመንና ህንድም ከጀመሩት ውለው ማደራቸውን ለአብነት ያነሳሉ ።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁለት ክስተቶች ሊያጋጥሙት ይችላሉ የሚል ሀሳብ ያላቸው ዶክተር ገመዳ ከለውጡ ወዲህ ዴሞክራሲን ለመተግበር ያለው ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ተስፋ የሚደረግበት ነው።
በአንጻሩ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ መሻሻሎች ቢኖሩም ህገ መንግሥቱ ካልተለወጠ፤ ሥርዓቱም ካልተቀየረ፣ ተቋማት በሚፈለገው መልኩ ካተገነቡና ምርጫ ተካሂዶ ህዝቡ የራሱ ተወካይ መምረጥ ካልቻለ ሙሉ ለውጥ አለ ማለት አይቻልም ይላሉ።
እንደ ዶክተር ገመዳ አገላለፅ ከአራት ዓመት በፊት የተካሄደው ምርጫ ፍትሃዊና ነጻ አለመሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ ይደመጣል። በተመሳሳይ መንግሥትም የምርጫ ሂደቱ ትክክል እንዳልሆነ አምኖ የመጪውን ዓመት ምርጫ ፍትሀዊና ነጻ ለማድረግ የምርጫ ቦርድን እንደገና የማዋቀር ሥራ እየሰራ ይገኛል።
ሆኖም መንግሥት አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የተዋጣለት የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት ይከብደዋል። ምክንያቱም በአገራችን ከ130 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመኖራቸውና እነዚህም አገራዊ ውይይቶችን አድርገው ጠንካራ ፓርቲዎችን ባለመፍጠራቸው ምክንያት የተሻሉትንና ለህዝብ ጥቅም የቆሙትን ፓርቲ ለመምረጥ አዳጋች ነው።
ለመጪው ጊዜ የተሳካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማካሄድም አንደኛ በፓርቲዎች መካከል ነጻ ክርክርና ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። ከሌሎች አገራትም ውድቀትና ስኬት እንደ ተሞክሮ መውሰድና ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ይጠቅማል።
በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ ቁርጠኝነቱና ተነሳሽነቱ መኖር አለበት ብለዋል። ዶክተር ገመዳ ሁለተኛ መሰረት ያለው ጠንካራ ዴሞክራሲ ለመፍጠር የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ አብሮ መታሰብ አለበት።በተለይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ምርጫ ቦርድ፣እንባ ጠባቂና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት ሆነው መዋቀር አለባቸው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሲመረጡ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም የመሟገት ብቃታቸው፣የትምህርት ደረጃቸው፣አገርን ለመምራት ያላቸው ቁርጠኝነት ተጠንቶ መሆን አለበት። ምክንያቱም አንድ ተመራጭ ቢያንስ 100 ሺህ ሰው ነው የሚወክለው።
ለሦስት መንግሥታት በህግ አማካሪነት ያገለገሉት ዶክተር ፋሲል ናሆም እንደገለጹት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሌላው አገር ዴሞክራሲ ቀድቶ የማምጣት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ መብቱን የሚያገኝበት ሥርዓት የመፍጠር ጉዳይ ነው።
ይህም ከአገራት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። የሚፈለገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር አንኳር ነጥቦች በህገ መንግሥቱ ላይ ነው የሚሰፍሩት። በህግ መንግሥቱ ተወያይቶና የጋራ መግባባት ላይ ደርሶ እነዚህ ጉዳዮችን የመተግበር ሥራ ነው የሚሆነው።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታ ሁለት ስጋቶች አሉበት ያሉት ዶክተር ፋሲል አንደኛው ማዕከላዊ መንግሥት ጫና ፈጥሮ እሱ በሚፈልገው መልኩ ብቻ እንዲመራ ማድረጉ ነው።ይህም ህዝቡ የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት በነጻነት ማራመድ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጥራልና ጥንቃቄ ይሻል።
ሌላው በዴሞክራሲ ስም ልቅ ሥርዓት አልበኝነት እንዳይፈጠርም ጥንቃቄ ይፈልጋል። ሁለቱ ፅንፎች እንዳይፈጠሩ በህግ ሚዛኑን እየጠበቁ መሄድ ይገባል። ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤት አንዱን ወገን ለመጥቀም ወይም ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን ህጉን ሥራ ላይ ለማዋል በነጻ የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።
ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ይጠቅማሉ ብለው በህገ መንግሥቱ ያልተካተቱና መካተት አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦችም ዶክተር ገመዳ ጠቁመዋል። አንደኛ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህግ የማውጣት ስልጣን በህገ መንግሥቱ ቢሰጠው የተሻለ ይሆናል።
ህግ የመተርጎም ስልጣንም ለፌዴሬሽን ከሚሰጥ ይልቅ ለፍርድ ቤት ቢሰጥ ዴሞክራሲ ግንባታው በጎ ድርሻ ይኖረዋል። እንዲሁም ከወረዳ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ሆነው የፍትህ ሥራ ብቻ ቢሰሩ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ይፋጠናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሁለተኛ የኢትዮጵያው ችግር ህግ አውጪዎችና ህግ አስፈጻሚም መሆናቸውን ዶክተር ፋሲል ይገልጻሉ። ለምሳሌ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ህግ አውጭ ነው።ሥራ አስፈጻሚ ውስጥም ይገኛል።
ህጉን ራሱ ያወጣዋል ራሱ ያስፈጽመዋል።ይህ የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ባህሪ ቢሆንም ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ለሚፈለገው ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የራሱ ሚና አለው ሲሉም ተናግረዋል።
ሦስተኛ ኢትዮጵያ የምትዳደረው በፌዴራል ሥርዓት ስለሆነ የክልል መንግሥታት ግንኙነት ህግ መንግሥታዊ እውቅና አግኝቶ ኃላፊነቱና ስልጣኑ በግልፅ ሰፍሮ መቋቋም አለበት።
ይህ ተቋም በክልሎችም መካከል ሆነ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥታት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶችን የሚፈታ ይሆናል። ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል ወይም የአማራና የትግራይ ክልሎች ቢጋጩ ችግራቸውን ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ የሚፈታ ይሆናል።
ያለ መንግሥታት ግንኙነት የፌዴራል ሥርዓት እንደማይኖር የሚገልጹት ዶክተር ፋሲል በኢትዮጵያ የመንግሥታት ግንኙነት አለ። ምክንያቱም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ከክልል ፍርድ ቤቶች፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከጤና ቢሮዎች፣የፌዴራል ፖሊስ ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖችና ወዘተ ተቋማት የሚያደርጉት ውይይትና ምክክር የመንግሥታት ግንኙነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ግንኙነቱ መደበኛ ነው ወይስ ኢ መደበኛ የሚለው መታየት ይገባል። የመንግሥታት ግንኙነቱ መደበኛና ኢመደበኛ ቢሆን ጥቅምና ጉዳቱ ተጠንቶ የተሻለውን መምረጥ እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4/2011
ጌትነት ምህረቴ