
አዳማ፡- የህብረተሰቡን የፍትሕ ጥያቄ ከመመለስና የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ የፍትህ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ፤ ህብረተሰቡም የዚሁ ተግባር ተባባሪ እንዲሆን ተጠየቀ። የኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቀን ትናንት በአዳማ ገልማ አባገዳ ተከብሯል።
የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ መሀቡባ አደም በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ የክልሉ ህዝብ ለዓመታት በፍትህ እጦት እና በሕግ የበላይነት አለመከበር ምክንያት ለችግር በመጋለጡ በሰፊው ቅሬታውን ሲያቀርብ ቆይቷል። በቅሬታም ሳይቆም ባደረገው ትግል ለለውጥ በቅቷል።
ይሁን እንጂ አሁንም የፍትህና የሕግ የበላይነት ሥራው በሚፈለገው ልክ የሰፈነ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ለፍትህ መስፈንና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
እንደ ወይዘሮ መሀቡባ ገለጻ፤ በፖሊስ በኩል አጥፊዎችን ይዞ ለህግ ከማቅረብ፣ በዓቃቤ ሕግ በኩልም ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ክስ ከመመስረት፣ በፍርድ ቤቶች በኩልም በተገቢው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ተደግፎ ፍርድ ከመስጠት አኳያ ባሉ ሂደቶች ላይ ህብረተሰቡ ዛሬም ድረስ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች አሉ።
በዚህ ረገድ ፍትህ እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስራት የሁሉም ኃላፊነት ቢሆንም የፍትህ አካላት ግን ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን በመገንዘብ መስራት ይኖርባቸዋል።
አሁንም ድረስ አጥፊዎችን የሕግ ተጠያቂ በማድረግ ሂደቱ በሚስተዋል ችግር የደቦ ወንጀል እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፣ የጦር መሳሪያን ጨምሮ የሚታዩ ሕገወጥ የሸቀጦች ዝውውሮችም በህብረተሰቡ ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን እያሳደሩ ይገኛሉ።
ይህ ደግሞ የፍትህ አካላቱ ተቀናጅተውና ተናብበው ካለመስራት፣ የባለድርሻዎች ትብብር ማነስ፤ እንዲሁም የህብረተሰቡ በሚፈለገው ልክ አጋዥ ያለመሆን ሂደት ውጤት ነው። በመሆኑም የህዝቡን የፍትህ ጥያቄ ከመመለስና የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ የፍትህ አካላቱ ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን ተገንዝበው፤ ባለድርሻዎችም አጋዥ ሆነውና ህብረተሰቡም በባለቤትነት ተሳትፎ በቅንጅት ሊሰሩ ያስፈልጋል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሐመድ ኑሬ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ፍትህ ለአንድ አገር ህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነገር ነው። ከዚህ አኳያ የክልሉን ህዝብ የፍትህና የሕግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነው አበረታች ውጤት ማየት ተችሏል። በተለይም አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁና የዜጎች መብቶች እንዲከበር ከማድረግ አኳያ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ለውጡ ከሚፈልገው ውጤት እንዲሁም የህብረተሰቡን የሰላም፣ የፍትህና የሕግ የበላይነት ጥያቄዎችን በበቂ ሁኔታ ከመመለስ አንጻር ብዙ መጓዝን፣ በቅንጅት መስራትን የሚፈልጉ ተግባራት አሉ። ሂደቱም ከአቅም፣ ከግብዓትና አመለካከት ብሎም ከሙያ ሥነምግባር ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን ለይቶ መሙላት፣ ለሙያ ሥነምግባር ተገዢ ሆኖ መስራትን የሚጠይቅ ነው።
በመሆኑም ፍትህ የሰፈነባትና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት አገርን እውን ከማድረግና የዜጎችን ሁለንተናዊ የፍትህ ጥያቄ ከመመለስ አኳያ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ተገንዝቦ መስራት ይኖርበታል።
በመድረኩ ላይ በክልሉ የተከናወኑ ዓበይት የፍትህ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በዓመቱ ውስጥ በርካታ ለውጥ ማምጣት የቻሉ የሕግ ማስከበር ሥራዎች መከናወናቸው ተነስቷል። ይሁን እንጂ አሁንም ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር ተያይዘው በህዝቡ የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎች በመኖራቸው እነዚህን ችግሮች ለይቶ ከመሰረታቸው ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4/2011
ወንድወሰን ሽመልስ