
አዲስ አበባ:- የአዲስ ዓመት አቀባበልን አስመልክቶ “ጳጉሜን ፌስቲቫል” በሚል ስያሜ የተዘጋጀው ፕሮግራም ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በጉለሌ እፅዋት ማእከል በመካሄድ ላይ ነው።
ዝግጅቱ በስድስቱም የጳጉሜን ቀናት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን የተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች ባህላዊ ጨዋታዎች፣ ባህላዊ ምግቦች አሰራርና አመጋገብ፣ አልባሳት ኤግዚቢሽንና ሽያጭ፣ የፎቶ ግራፍ አውደ ርእይና ሌሎች በየክልሉ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች በዝግጅቱ ላይ ለእይታ እየቀረቡ ይገኛሉ።
የ“ጳጉሜን ፌስቲቫል” ድርጅት ሀሳብ አፍላቂ፣ መስራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሀይለአብ መረሳ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የዚህ ድርጅት ሀሳብ የመነጨው የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ሲሆን ሁሉንም ነገር አጠናቅቆ ወደ ሥራ የገባው የዛሬ ሁለት ዓመት ነው። ይህ አሁን እየተከበረ ያለው ሁለተኛው “ጳጉሜን ፌስቲቫል” ዝግጅት ሲሆን ከአምናው ዘንድሮ በተሻለ ሁኔታና በድምቀት በመከበር ላይ ነው።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የ“ጳጉሜን ፌስቲቫል” ዋና አላማ አዲሱን ዓመት እኛ ኢትዮጵያውያን በታደሰና በጠንካራ መንፈስ፤ ለሰላም፣ ለሥራና ብልፅግና በተነሳሳ ስሜት እንድንቀበለው ማድረግ ሲሆን፣ በአገራችን ሰላም እንዲሰፍ፣ በመካከላችን ፍቅር እንዲነግስ፣ የባህል ልውውጥ እንድናደርግ እድሉን መፍጠር ነው።
አንዳንድ ጊዜ በሀገራችን ግጭት የሚፈጠረው ስለማንተዋወቅ ነው የሚሉት አቶ ሀይለአብ እርስ በርስ ልንተዋወቅ፣ አንዱ የአንዱን ባህል ሊያውቅና የአገሩ እሴት መሆኑን ልንገነዘብ ባለመቻላችን ነው። ይህን አይነቱን ችግር ለመፍታትም በማሰብና ድርጅቱ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ታስቦ የተወጠነና እዚህ የደረሰ ነው።
ከሥራ አስኪያጁ ገለፃና በዝግጅቱ ላይ በመገኘት መረዳት እንደተቻለው ከየክልሉ በመጡ የባህል ቡድኖች አማካኝነት በርካታ ባህላዊ ጨዋታዎች፣ በየክልሎቹ ባህላዊ ሙዚቃ የታጀበ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ፣ የችግኝ ተከላና ሌሎች ፕሮግራሞች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ ይህም እስከ ዝግጅቱ ፍፃሜ ጳጉሜን ስድስት ድረስ ይቀጥላል።
እንደ አቶ ሀይለአብ ገለፃ በተለያዩ አገራት ባህላዊ የጎዳና የፌስቲቫል ሳምንት ማዘጋጀትና ማክበር በጣም የተለመደ ነው። እኛ አገር ግን ይህ ባህል የለም። በመሆኑም “የአሥራ ሶስት ወር ፀጋ” ባለቤት መሆናችንን ተጠቅመን 13ኛዋን ወር ለዚህ ዝግጅት ልናውላት ይገባል። ይህም ባህላችንን ለማስተዋወቅና በሂደትም ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እናሳድጋለን። ይህ እነብራዚልና ሌሎች አድርገውት ዛሬ የትና የት ደርሰዋል።
አቶ ሀይለአብ እንደሚሉት ከሆነ በሌሎች አገራት አዲስ ዓመት ከመግባቱ በፊት ለሳምንታት ወይም ለወር ባህላዊ ግብይትና ሌሎች እንደሚደረጉት ሁሉ በእኛምጋ ጳጉሜን በ13ኛ ወርነቷ የ“ጳጉሜን ፌስቲቫል” በሚል ልናከብራት ይገባል። ይህ ለኛ አዲስ ስለሆነ እንደ ችግር ልንቆጥረው እንችላለን።
ይህ ለአዲስ ዓመት መቀበያ ሲባል ቻይናን ጨምሮ በርካታ አገራት የሚያደርጉትና በቱሪስት ፍሰት ምክንያት ኢኮኖሚያቸውን እየደጎሙበት የሚገኝ ተግባር ነው። ስለዚህ ዝግጅቱን ወደ ጎዳና ትርኢትነት መቀየርና ለቀናት በማስኬድ ልክ እነ ስፔን፣ ብራዚልና የመሳሰሉት አገራት ከኮርማ ጋር በሚደረገው ዓመታዊ ትግል/“kobullfighting” እያገኙት እንዳለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እኛም ልናገኝ ይገባል።
በስድስቱ ቀን ዝግጅት የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች በየቀኑ በስፍራው እየተገኙ ችግኝ ተከላና የመሳሰሉትን ተግባራት እንደሚያከናወኑ ከተገኘው መረጃ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን አጠቃላይ ፕሮግራሙ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማና ሌሎች በሚገኙበት በበዓሉ ዋዜማ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህልና ቴአትር አዳራሽ በሚቀርብ ዝግጅት እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 4/2011
ግርማ መንግስቴ