
በተለያዩ ጊዜአት የሚወጡ የጥናትና ምርምር ምክረ ሀሳቦችን ወስዶ ወደ ስራ በመቀየር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አፈወርቅ ካሱ ተናገሩ ፡፡
አድማስ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው 12ኛው አመታዊ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በትምህርት ጥራት፣የዩኒቨርስቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ትስስር አለማቀፋዊነት በከፍተኛ ትምህርት ላይ በሚል በተዘጋጀ ው መድረክ ላይ ጥናት ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተልዕኮ ከተሰጣቸው ስራ ውስጥ አንዱ ጥናት ምርምር ማካሄድ ነው ያሉ ሲሆን የሚጠኑት ጥናትና ምርምሮች ከተሰሩ በኋላ በመሰራጨት ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆን አለባቸውም ብለዋል፡፡የዚህ አይነቱ የምርምር ጉባኤ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ተደራሽ ከሚደረጉባቸው መንገዶች አንዱ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የጥናትና ምርምር ውጤቶች በተመራማሪዎች እንዲህ ሲቀርቡ ምክረ ሀሳብ አንስተው ወደ ስራ ለሚቀይሩ ሌሎች አካላት ጥሩ ግብአትም ጭምር ናቸው ብለዋል ዶክተር አፈወርቅ ፡፡ የሚጠኑ ጥናቶችን ህብረተሰቡ በሚረዳው ቋንቋ ተተንትነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የምርምር ስራዎች ተሰርተው ብቻ መቀመጥ የለባቸውም፤ በተለያዩ መድረኮች ላይ ቀርበው ምሁራን ሊወያዩባቸውና ለማህበረሰቡም ተደራሽ መሆን ነው ያለባቸው ሲሉ ሚኒስቴር ዴኤታው ያሳስባሉ፡፡
እንደ ዶ/ር አፈወርቅ ገለፃ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደዚህ አይነት ጥናትና ምርምርን በመስራት ውጤቱንም የሚያሳዩበትና የሚማከሩበት መድረክ አዘጋጅተው የማህበረሰብ ክፍሎችን፣የሚመለከታቸው አካላትና ቀጣይ ተመራማሪዎች እንዲሳተፉበት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
ዘመናዊ ጥናትና ምርምር በሀገራችን ከተጀመረ በጣም ቅርብ ጊዜ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ከተለያዩ የአለም ሀገራት ጋር ስናስተያይ ገና ብዙ ይቀረናል ተብሏል፡፡ መንግስትም አሁን ላይ ለጥናትና ምርምር ልዩ ትኩረት ሰጥቶበት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ሚኒስቴር ዴኤታው አስታውሰዋል፡፡
እንደ ሀገር የሚታተሙ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በሀገራዊ የምርምር መፅሄቶች ላይ ማሳተም እንዲሁም ዕውቅና ባላቸው አለም አቀፍ መፅሄቶች ላይ ማሳተም የሀገራችንን ገፅታ የምንቀይርበት አንዱ ማሳያ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
እንደዚህ አይነቱ መድረክ መዘጋጀቱ ለሀገራችን ተመራማሪዎች ጥሩ የዕውቀት ሽግግር ማድረጊያ መንገድ ነው ያሉት የአድማደስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋዬ ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው እንደዚህ አይነት መድረኮችን እንደሚያዘጋጅም ተናግረዋል ፡፡
እንደ ዶክተር ሞላ ገለፃ አሁን ላይ በሀገራችን ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ከፍ እያለ ነው፡፡ ተቋማቱም በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ጠቁምው ዩኒቨርስቲያቸውም በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ እንዳለም አስታውቀዋል፡፡
አሁን በሀገራችን ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ተቀራርበው አብሮ የመስራት ነገር አይታይም ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዚህ ዙሪያ በርካታ መሰራት ያለባቸው ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል ፡፡
ሐይማኖት ከበደ