
ኢትዮጵያዊ አንዱ ክልል ከሌላው ክልል፤ አንዱ ጎሳ ከሌላው ጎሳ የተሰናሰለ። በደምና ስጋ የተሳሰረ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያውያን በባህል። በታሪክ። በሃይማኖትና እምነት የተጋመድን ህዝቦችም ነን ። በዚህ ማህበራዊ። ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር አንዱ ለሌላው። ሌላው ለአንዳችን ጋሻና መከታ ሆነን ኖረናል።
ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው በጀግንነት። በአንድነት፣ በአልበገር ባይነትና ለሀገራችንን ዳር ድንበር ክቡር መስዋዕትነት በመክፈልና ሉአላዊነታችንን በማስጠበቅ ጭምር ነው። ይሄ አንድነታችን ያስገኘው ጀግንነት ከአፍሪካ ብቸኛ በቀኝ ያልተገዛን ሀገር ለመሆን አስችሎናል። ይሄ አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያኖሩልን እኛም የምንኮራበት የጀግንነት ታሪካችን ነው።
ኢትዮጵያውያን ገድላቸው ይሄ ብቻ አይደለም፤ አለም ስልጣኔ ሳይዘልቀው ሳይንሰና ቴክኖሎጂ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ከመድረሱም በፊት የስልጣኔ በር ከፋች በመሆን ዛሬም ድረስ ለአለም የሚደንቅ እጅግ ውብና አስደናቂ የእጅ ስራ ጥበብ ባለቤት መሆን ችለዋል። አክሱም። ላሊበላ ።
የፋሲል ግንብ እና ሌሎችም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎች የዚህ አብይ ምስክሮች ናቸው። ይህም ከእኛ ኢትዮጵያውያን አልፎ የዓለም ቅርስና መኩሪያ ሆኖ ተመዝግቧል። ቀደምት አባቶቻችን ይሄንን ድንቅ ጥበብ አስቀምጠው በማለፋቸው ዛሬ የቱሪስት መስህብ በመሆን የኢኮኖሚያችን አንዱ የገቢ ምንጭ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛል። ይሄም ሌላኛው የእኛነታችን መኩሪያ ሀብታችን ነው።
ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ህይወታቸው እስካሁን አለም ላይ የማይታይና የማይሰማ በአንድ ገበታ አብሮ መብላትና መጠጣት፤ በደስታና በችግር ጊዜ መረዳዳት። ሲታመሙ ማስታመም ሲሞቱ አልቅሶ መቅበር። ዘር። ሀይማኖትና ፆታ ሳይለዩ አንተ ትብስ አንቺ ብሎ መተሳሰብና መከበባር አብሮን የኖረ አስደናቂው የምንኮራበት ባህላችን ነው።
በእድር። በእቁብና በሌላውም መሰል ማህበራዊ ተቋማት ራሳችንን በማደራጀት የኢኮኖሚ ችግሮቻችንን። የሚያጋጥሙ ግጭቶችን የምንፈታበት። ዳኝነት የምንሰጥበት። ይቅርታና ምህረት የምንጠያየቅበት የእኛነታችን መኩሪያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ባለቤትም ነን። ይሄ ኢትዮጵያዊ ኩራታችን እና ልዩ መገለጫችን ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ኢትዮጵያዊነት ኩራት መሆኑን የገለጹት “ትላንት፣ አባቶቻችን በመተማ፣ በአድዋ፣ በማይጨውና በካራ ማራ አጥንታቸውን ከስክሰው። የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩዋት አገር አለችን። በውብ አገር ዘመን ተሻጋሪ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ነን።
መነሻችንን የምናውቅ ታላቅ ህዝብ ነን። በልዩነት የደመቀው ህብረታችን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል። ጠላቶቻችንን አንበርክኳል። ሉአላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ ለሌሎች ህዝቦችም የነፃነት ትግል አርአያ ሆኗል። ብዙ ዓይነት ባህል ቋንቋ እና እምነት ቢኖረም ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደ እና የተዋሀደ ነው።”በማለት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ኩራት ነው ስንልም ሳንሳቀቅ። ሳንፈራ። ሳንሰደድ። ደህንነታችን ተጠብቆ የምንኖርባት ዋስትና የምትሰጠን ሀገር አለችን እያልን ነው። የተፈጥሮ ጸጋዎች ኩራታችን ናቸው። የትም ሳልሰደድ የኖርኩት ሀገሬ ኩራቴና መመኪያዬ በመሆኗ ነው። አክሱም ላሊበላ የጥበብ መነሻ እያልን የምናደንቃቸው የእኛነታችን መገለጫ ኩራታችን ናቸው።
በአለም ቅርስነት የተመዘገቡት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን የእኛነታችን ማሳያ የማንነታችን መገለጫ ናቸው። ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ያላት። የሰው ልጅ መገኛ ሀገር የታሪካዊ ባህላዊና ስነጥበባዊ መነሻ ሀገር ናት ። የአየር ንብረቷ የህዝቧ እንግዳ ተቀባይነት ሁሉ የኢትዮጵያውያን መገለጫዎች ናቸው ይህ ነው ኢትዮጵያዊ ኩራታችን።
ይሄንን አባቶቻችን ያቆዩልንን የኢትዮጵያዊነት ኩራት በተሻለ መልኩ ማስቀጠል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊያ ኃላፊነት ሊሆን ይገባዋል። ዛሬ ከእኛ የሚጠበቀው የነበረን ታሪክ ማውራት። ባለፈ ታሪክ መኩራራት ብቻ ሳይሆን አሁንም ወቅቱን የዋጀ ታሪክ ሰርተን ለትውልድ ማስተላለፍ ነው። ከዚህ ዘመን ትውልድ የሚጠበቀው አደራ ይሄው ነው። ኢትዮጵያዊ ኩራትን ወደ ፊት ማስቀጠል ከሁሉም የሚጠበቅ ቢሆንም በዋነኛነት ወጣቱ ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ አለበት።
ሀገር የሚቀጥለውና የሀገራዊ ኩራት የሚጠነክረው ዛሬ የሚጠበቅብንን ለኢትዮጵያዊነት ኩራት የሚሆኑ ታሪኮችን ሰርተን ማለፍ ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን ነውና እውቀታችንን። ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሳንሰስት በሃቅ። በቅንነትና በሀገር ስሜት እንስራ። በዚህም ሀገራችንን ከገባችበት ማህበራዊ። ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችም በማውጣት ለብሔራዊ ኩራታችን መሰረት የሆነች አገር እንገንባ።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011