
አዲስ አበባ፡- ህግና ሥርዓትን ተከትለው በማይንቀሳቀሱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የትምህርት ማህበረሰብ ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።ህግና ሥርዓትን በተገቢው መንገድ ማስከበር የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቷል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ካለፉት ዓመታት ችግሮች በመማር፣ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም ከህግና ሥርዓት ውጪ የሆኑ ነገሮችን የማረም ሥራ በ2012 የትምህርት ዘመን ይሰራል፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ህግና ስርዓት በማያከብሩ ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ማህበረሰብ ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል።
“አንዳንድ ለስለስ እና ለፈስፈስ ያሉ ህጎቻችንን ማየት፣ መመርመር እና ማስተካከል ይገባናል” ያሉት ዶክተር ሳሙኤል በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ ተማሪም ሆነ መምህር አለባበስ ፣ የጸጉር አቆራረጥ እና ሌላውም ሥርዓት ያለው ሊሆን እንደሚገባም ተናግረ ዋል።አሁን በአንዳንድ ቦታ ላይ የሚታየው መምህሩ ከተማሪው የማይለይበት ሁኔታ መሆኑን ገልጸው፣ መምህር እንደ ቀለም አባትነቱ በአለባበሱ፣ በጸጉር አቆራረጡም ሆነ በሌላውም አርአያ ሊሆን ይገባል። ሆኖም ግን እስካሁን በዚህ ዙሪያ የተልፈሰፈሱ ነገሮች ስላሉ ሰብሰብ ማለት ይገባቸዋል ብለዋል።
ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ በእቅድ የሚመራ ነው።መምህራን ተማሪዎቻቸው ሙሉ ሰው ሆነው እንዲወጡ ይፈልጋሉ።አብዛኛው መምህር ይህንን ያደርጋል።መምህሩ ተማሪው ሙሉ ሰው እንዲሆንለት ከፈለገ ደግሞ የተቀመጠው የትምህርት ጊዜ ሳይሸራረፍና ሳይቆራረጥ መተግበር አለበት፣ መምህሩ ተማሪውን ባለማብቃቱ፣ ከትምህርት እንዲነጠል በማድረጉ ተማሪው ለሚያደርሰው ጥፋት መጠየቅ አለበት።
“ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም ተማሪውን ብስጭት ውስጥ የሚከቱ፣ የራሳቸው አጀንዳ እንዲፈጸምላቸው የሚፈልጉ አሉ”ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለእነዚህ አካላት ከዚህ በኋላ እድል ሊሰጣቸው አይገባም።ከግቢ ጥበቃ ጀምሮ በመታወቂያ ከሚነሱ አተካሮዎች እስከ መኝታ ክፍል ድረስ እንዲሁም በካፍቴሪያ፣ ቤተመጽሐፍት፣ ላብራቶሪ፣ ሬጅስትራር ያሉ ሠራተኞቻችን ተማሪዎቻቸውን የሚይዙበት አግባብ የተማሪውን መብት አክብረው፤ ተማሪው ደግሞ ግዴታውን ተወጥቶ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት ወላጆች ተማሪዎቻችንን ሲያስረክቡን ንጹህ ጥርስ ያለው ፣ቆዳው ንጹህ የሆነ ልጅ ነው። ዩኒቨርሲቲ ሲመጣ ግን ጸጉር ማንጨባረር፤ ከእናቱ ከአባቱ ውጪ የሆነ ባህል መልመድ፤ ሌላው ቀርቶ ሱሪውን እንዴት እንደሚታጠቅ ይጠፋዋል።”ቡና ጠጥቶ የማያውቅ ልጅ ተቀብለን ጫት የሚበላ ተማሪ እናወጣለን። ስለዚህ እነኚህ ነገሮች ሁሉ ስርዓት ሊይዙ ይገባል።
በዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ የሚገኙ ኢንቨስትመንቶችን በሚመለከት ዩኒቨርሲቲዎች ከአካባቢው መስተዳድር ጋር በመሆን ችግሩን መፈታት እንደሚገባቸው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ነገር ግን ወደ ግቢ የሚገባ ማንኛውም አደንዛዥ እጽም ሆነ ሌላ በአጠቃላይ ስርዓት አልበኝነት ከትምህርት የማባረር እርምጃ የሚያስወስድ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2012 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚመጣ ተማሪ ተማሪ ሆኖ መምጣት እንዳለበት ያሳሰቡት ዶክተር ሳሙኤል፤ ጸጉሩ የተስተካከለ፣ ልብሱ በንጽህናና በአግባቡ የሚለብስ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።ይህንን ለመከላከልም ሆነ ሥርዓት ለማስያዝ ሰነድ ተዘጋጅቷል።
በሚቀጥለው ዓመት በተሻለ ደረጃ የውስጥ ክፍተቶቻችንን አርመን ߹የውጭ ግፊትን ተቋቁመን የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሳካ ለማድረግ በእኛ በኩል ከፍተኛ ዝግጅት አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል።ሁሉም በግቢ ውስጥ የሚገኙ ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዳይከሰት ጠንቅቀው መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
አብርሀም ተወልደ