
‹‹ በዓለም ዙሪያ በመሶብ የሚበላ ማህበረሰብ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፣ ክብ ሰርተን ላንተ ይህ ይገባሃል መባባልና መገባበዙም የእኛው አኩሪ ባህል ነው። ሰው በልቶ የማይጠግብ የማይመስለንም እኛ ነን። ይህ ሲሆን ደግሞ ብሔር፣ ዘርና ጎሳ እንዲሁም ቀለም ለይተን አይደለም።ይልቁንም በአንድነት ተሰባስበን እናደርገዋለን እንጂ›› ይላሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ስለ አገራዊ ኩራት ሲናገሩ።
ይቀጥሉናም ለአንድ ነገር በደቦ የምንሰራው እኛ፣ ቡና ተገባብዘን ችግራችንን የምንፈታው እኛ ብቻ መሆናችንም አንዱ ኩራታችን መሆኑን ያስረዳሉ።የአገር ኩራት ማለት ራስን መውደድ ነው።ምክንያቱም ራስን ያልወደደ ሌላ ሰው አይወድም፣ ራሱን ያላከበረም ሌላ ሊያከብር አይችልም።በራሱ ያልኮራም እንዲሁ ስለ አገር ኩራት ሊያውቅና ሊያወራ አይችልም ባይ ናቸው።
በሌላ በኩል የአገር ኩራት ማለት የአገር ፍቅር ነው።ቤተሰብ ተመርጦ እንደማይታይ ሁሉ አገርም ምርጫ የላትም።ስለሆነም በእርሷ ማንነትና ምንነት መኖር ስንጀምር ምርጫችን እርሷ ብቻ መሆኗን እንረዳለን በእርሷም ኮራን እንላለን የሚሉት አቶ ኦቦንግ፣ አገራችን ደሃ፣ ሀብታም፣ ኋላቀር እያልን የምንተዋት ወይም የምናንቋሽሻት አይደለችም።ይልቁኑ ማንም ምንም ቢል የተሰራንባትና የተፈጠርንባት ምድር ስለሆነች ኩራታችን ነች ይላሉ።
ዛሬ ይህ ሁሉ ኩራት ተሸርሽሮ አልቆ አንተ የእንትና አንተ እንትን ልጅ መባባል ተጀምሯል። ይህ የመጣው ደግሞ በአንዳንድ የማያገናዝቡ ሰዎች አማካኝነት ነው። የራስን ክብርና ስልጣን ለማቆየት ሲባል በጠንካራ መሰረት ላይ የተሰራው ኩራት እንዲፈራርስ ሆኗል። ትውልዱም አገር ናፋቂ ሳይሆን ውጪ አድናቂና ናፋቂ እንዲሆን ተሰርቶበታል። ስለሆነም አሁን አገራዊ ኩራትን መልሶ ለማምጣት ከራስ የጀመረ ሥራ መሰራት እንዳለበት ይናገራሉ።
ኢትዮጵያን ዝቅ አድርጎ የሚያየውን ወጣት ምን ያህል ታላቅ እንደነበረች ማሳየትና ስብዕናውን መቀየርም ላይ መሰራት አለበት ይላሉ። አገሬ መመኪያዬ የሚል ትውልድ መፍጠር ላይ መጀመሪያ ካልተሰራ አደጋ እንደሆነ ይገልጻሉ።
‹‹የአገር ኩራት ማለት የመኖር ተስፋና የምንመ ራበት መርህ ማለት ነው። እኛ የምንኖርባትና እትብ ታችን የተቀበረባት ምድር ኢትዮጵያ ናት። ስለዚህም ከኢትዮጵያ አፈር ተሰርተናልና ኩራታችንና ማንነ ታችን ኢትዮጵያ እንጂ አሜሪካ ወይም ቻይናና ሌሎች አገራት ሊሆኑ አይችሉም።›› የሚሉት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በባህል ዘርፍ የሚያስተምሩት ዶክተር ዋልተንጉስ መኮንን ናቸው።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ‹‹ኩራት አንድነት ነው፣ ኩ ራት አ ብሮነት ነ ው፣ ኩ ራት ጥ ንካሬ ነው። ኩራት መመኪያ፣ ዋስትና፣ መኖሪያና ማፍሪያ፣ መጠለያና ማንነትም ነው። ስለዚህም አገራዊ ኩራትም በአገር መመካትን፣ መኖርና የፈለግነውን ማድረግ ነው። በዚህ መሰረት ላይ የታነጸ ሰው ደግሞ በአገሩ ይኮራል ልንለው እንችላለን ይላሉ።
እንደ ኢትዮጵያዊነት እኮራለሁ ሲባልም በማንነት፣ በታሪክ ፣ባፈራናቸው ሀብቶች፣ በተፈጸሙ ገድሎች መኩራት እንደሆነ የሚያወሱት ዶክተር ዋልተንጉስ፣ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት አገር በመሆኗ ነጻነትን ተላብሰን እንድንኮራ አድርጋናለች። በየትኛውም ቦታ ላይ ብንገኝ ማን ይደፍረናል የሚል ስሜት እንዲሰማን ያደረገውም ይህ መሆኑ ነው። የይቻላልን መንፈስ ከእኛ አልፎ ለአፍሪካ አገራት ማስተማራችንም ታሪክና ኩራት ስላለን ነው። ማስቀጠሉ ችግር ሆኖ ቢታይም ይላሉ።
በአመራረትና በአሳሳል እንዲሁም በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች ከሌሎቹ ደምቆ መታየትም አንዱ ኩራታችን ነው። ስለሆነም ኩራት ታሪክ ነው፣ የስነልቦና አሳሳሉ ኩራት ነው፣ የተፈጥሮ ጸጋዎች ኩራት ናቸው። በመሆኑም እነዚህ እኔነትን ፈጥረው መተማመን እንዲኖር ያስችላሉና ኢትዮጵያን ብዙ መኩሪያዎች እንዳሉን እንረዳለን የሚሉት ዶክተር ዋልተንጉስ፤ ይሁንና አሁን አሁን በተለያዩ ምክንያቶች በወሬ ብቻ የምንኮራ እየሆንን መጥተናል። በተግባር የሚታይ የኩራት መመኪያ ጠፍቷል። ስለሆነም ያንን ሊያመጡና ሊመልሱ የሚችሉ ሥራዎችን መስራት ለነገ መባል የለበትም ሲሉ አበክረው ይናገራሉ።
‹‹ይህችን ድንቅና ታሪከ ብዙ፣ እጅግ የተለያየ የታሪክ መስህብ ያላት አገራችን በቅጡ ባለመያዛችን ታሪካችን እንደ አልባሌ ተረት፣ ቅርፃ ቅርፃችን እንደ ልጆች መጫወቻ፣ ይህንን ያቆዩልን ጀግኖቻችን እንደ ማንም ሳይቆጠሩ እዚህ ደርሰናል። በዚህ ደግሞ ኩራታችንን ተነጥቀናል›› የሚለው ደግሞ የላስታ ወረዳ ባህል ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ቸኮለ ታዘበው ነው።
‹‹ያለን ኩራት አገር ተሻግሮ የእኔ ነው ባዩ ሲበዛ እየተመለከትን መምጣታችንን በጤፋችን ብቻ መመልከት በቂ ነው›› የሚለው ወጣት ቸኮለ፤ አገራዊ ኩራት ማለት ኢትዮጵያዊ የሆነ አስተሳሰብን በተግባር ማሳየት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ከእኔ አንተ ቅደም መባባሉ፣ ለሰዎች ማሰቡ፣ እንግዳ ተቀባይነቱ፣ አንድነትን መሰረት ያደረገ መከባበሩ ወዘተ ነው። ሆኖም ይህ ዛሬ አለወይ ከተባለ በእኔ ግምት አለ ለማለት እቸገራለሁ። ምክንያቱም ያንተ ክልል ይህ አይደለም ከዚህ ውጣ እየተባባልን መጥተናልና።
እንደ ወጣት ቸኮለ ገለጻ፤ ኩራትን ለመመለስ መፍትሄው ልዩነት ውበት መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡ ‘የእኔ’ የሚለውን ሳይሆን ‘የእኛ’ የሚለውን አባቶች እንዳወረሱን ሁሉ እኛም በተለይ ወጣቶች እኛ እሚለውን አስፍተን አገራችንን ባላት ሁሉ ከፍ ማድረግ ከቻልን የአገር ኩራታችን ተመልሶ ይመጣል። ኩራት ያልነው ሁሉ እውነት ከልብ ኩራት ሆኖ መታየት ሲችልም ነው አገራዊ ኩራት በትክክል ሊረጋገጥ የሚችለው። ስለሆነም መንግሥትና ማህበረሰቡ ለቀደመ ማንነቱና ኩራቱ ሊሰራ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
ጽጌሬዳ ጫንያለው