
አዲስ አበባ፡- ህብረተሰቡ በራሱ ያመረተው ሰላም ለአገር አንድነትና ብልጽግና እንዲሁም ለሰላም መረጋገጥ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል አስታወቁ።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ትናንት ‹‹ሰላምን እተክላለሁ ለሀገሬ.›› በሚል መሪ ሀሳብ የሰላም ቀንን አስመልክቶ በተደረገ የፓናል ውይይት ላይ እንዳሉት፤ ሰላም በራሱ በህብረተሰቡ ከተመረተ ውስጣዊ ሰላም በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ይረጋገጣል።
በማህበረሰብ መካከልም ጥብቅ ትስስር ይፈጠራል። ይህ ደግሞ አገርን ለራሳቸው ጥቅም ለመበጥበጥ የሚነሱ ሰዎችን አደብ ለማስገዛት ፍቱን መድሃኒት እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ገለጻ፤ የሰላም መደፍረስ የሚመጣው ሰላም ከየትና እንዴት ይመጣል የሚለው ላይ መግባባት ባለመቻሉ ነው። ስለሆነም ህብረተሰቡ በራሱ ባህልና እሴት የገነባው ሰላም ካለ አንድ አይነት ምልከታ ላይመጣ የሚችልበት ሁኔታ አይፈጠርም። በመሆኑም ማህበረሰቡ በራሱ የሚያመርተው ሰላም እንዲኖረው በማድረግ ዙሪያ መሰራት አለበት።
የግጭቶች መነሻ ምክንያቶች ምንም ይሁኑ ምንም ቅድሚያ ለአገር፣ ለሰላምና ለሕዝቦች ደህንነት በማሰብ በውይይት መፍታት የሚመጣው ህብረተሰቡ የራሱን እሴት አበልጽጎ ሲኖርበት እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ለኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ በመገዛት፣ በመከባበር፣ በመደጋገፍና በመናበብ ሀሳቡ እንዲጎለብት በጥምረት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ በተለይ ሁለት ነገሮች አብነት እንደሆኑ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ተከታታይ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን በሚገባ መጠቀምና ቁርጠኝነቱን ወደ ባህልና ህብረተሰቡ ማውረድ የበለጠ ህብረተሰቡ ሰላሙን በራሱ እንዲጠብቅ ያግዘዋል። ስለሆነም የአረንጓዴ ሰላም አምባሳደሮችን በማጠናከር፣ ቅድመ ግጭት ሥራዎችን በመስራትና ለሰላም ዘብ የሚቆሙትን ሁሉ በማበረታታት ወደፊት መቀጠል ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ይበጅ ዘንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ 300ሺ የሰላም አምባሳደሮችን ማሰልጠኑን ተናግረዋል። ይሁንና አሁንም ህብረተሰቡ ያልሰራው ሰላም ዘላቂነት ስለሌለው ህብረተሰቡ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ ለአገሪቱ ሰላም መስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የታመነበት የሰላም ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠ ሲሆን፤ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ማዕከሉ የኢትዮጵያውያንን ባህልና ማንነት ይበልጥ በሚያንጸባርቅ መልኩ የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
የበዓሉ አካል የሆነው የእግር ጉዞ ከወሎ ሰፈር አደባባይ እስከ ደንበል ድረስ በፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ ታጅቦ ተከናውኗል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው