
አዲስ አበባ፡- መሰረታዊና ህይወት አድን መድኃ ኒቶች አቅርቦት መሻሻሉን የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አድና በሬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፣ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የመሰረታዊና ህይወት አድን መድኃኒቶች አቅርቦት የመቆራረጥ ችግሮች ኤጀንሲው በዘረጋቸው አዳዲስ የአሰራር ስልቶች መቀረፍ ጀም ረዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ ኤጀንሲው ከወሰዳቸው ማሻሻያዎች መካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት፣ አዳዲስ ስልቶችን በመጠቀም የመረጃ ልውውጡን ቀልጣፋ ማድረግ፣ የግዥ ሥርዓቱን በዓይነትና በመጠን መለየቱ እንዲሁም አሰራሮችን በየጊዜው በመፈተሽ ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ተጠቃሽ ናቸው።
ከመንግሥት ጤና ተቋማት ጋር ቋሚ የግንኙነት ሰንሰለት መዘርጋት፣ በክምችት ረገድ የትኛው መድኃኒት እንዳላቸው እና እንደሌላቸው መለየት እንዲሁም የትኛውን መድኃኒት እንደሚፈልጉ ለማወቅ ስለሚረዳ ኤጀንሲው የደንበኞችን ፍላጎት ቀድሞ በማወቅ አሰራሩን ለማስተካከል አግዞታል።
በዚህም ሳቢያ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የመድኃኒት አቅርቦት መቆራረጥ አሁን ላይ መሻሻል ማሳየቱን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
በዘውዲቱ ሆስፒታል የፋርማሲ ክፍል ኃላፊ ወይዘሪት ሃና ልካስ እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት ይስተዋል የነበረው የመድኃኒት እጥረት በአሁኑ ሰዓት የተሻለ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። ሆስፒታሉ የመድኃኒት አቅርቦት ሊገጥመው ያልቻለው ኤጀንሲው የአሰራር ስልቱን በማዘመኑ እንደሆነ ገልጸው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ማቅረብ ካልቻለ እንኳን አስቀድሞ ሆስፒታሉን ከሌላ እንዲገዛ ስለሚያሳውቅ በአሁኑ ወቅት የመሰረታዊና ህይወት አድን መድኃኒቶች ችግር እያጋጠመ አይደለም ብለዋል።
የመድኃኒት አቅርቦቱ አሁን ላይ ችግር ባይኖርም የአገልግሎት ተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ እጥረት ሊከሰት ስለሚችል መንግሥት በአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ገንብቶ ቢያቀርብ ዘለቄታ ያለው መፍትሄ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
የጳውሎስ ሆስፒታል የመድኃኒት አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ደበላ ገመዳ በበኩላቸው የመሰረታዊና ህይወት አድን መድኃኒቶች አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥራት፣ በመጠንና በፍጥነት የማሻሻል ሁኔታ እያሳየ ቢሆንም አሁንም ሙሉ ለሙሉ ችግሩ ተቀርፏል ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።
አንድ ታማሚ የህይወት አድን መድኃኒት በፍጥነት ካላገኘ ህይወቱን የሚያጣበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የገለፁት ኃላፊው፤ በፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የአገልግሎት ፈላጊ ቁጥር ኤጀንሲው በየጊዜው እየፈተሸ አቅርቦቱን ማስተካከል ይኖርበታል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
ማዕረግ ገብረእግዚአብሄር