
አዲስ አበባ፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ዘርፍ ልምድ አለመኖር፣ እንደ ሀገር የአመለካከትና የመዋቅር ችግር በመኖሩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች እየተደጋገፉ አለመ ሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
አድማስ ዩኒቨርሲቲ አሥራ ሁለተኛውን አገር አቀፍ ዓመታዊ ኮንፈረንስ ‹‹ የትምህርት ጥራት፣ የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪዎች ትስስር እና የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነት” በሚል ርዕስ በሀርመኒ ሆቴል አካሂዷል።
በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አፈወርቅ ካሱ እንደተናገሩት፣ ዘመናዊ ምርምር በሀገራችን የተጀመረው በቅርብ መሆኑና ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች መመጋገብ ባለመቻላቸው መድረስ ያለብን የእድገት ደረጃ እንዳንደርስ አድርጎናል ብለዋል። ለሀገርም የሚፈለገውን ያህል አስተዋፅኦ ሳያደርጉ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል። በሁሉም ዘርፍ ጠንካራ የሆነ ጥናትና ምርምር ሲያካሂዱ አይስተዋሉም።
ከአፍሪካ ሀገሮች አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት ለጥናትና ምርምር የሚበጅተው በጀት ከዓመታዊ ገቢው ዜሮ ነጥብ ሦስት ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ ይሄም ሌላው እንቅፋት መሆኑን አንስተዋል። የዚህ ውጤትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚውና ማህበራዊ ችግሮቻችን እየተበራከቱ እንዲመጡ በር ከፍቷል።
አሁን ባለንበት ሁኔታ መንግሥት ሀገራዊ ፖሊሲዎችን ለማውጣት ጥናትና ምርምርን አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ከፍተኛ የሆነ በጀት በመበጀት እየተንቀሳቀሰ ነው። እንዲሁም በሁሉም ዘርፍ ጥናትና ምርምርን የሚደግፍና የሳይንስ ባህል እንዲጎለብት ለማድረግ አዲስ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋዬ በበኩላቸው እንደገለፁት፣ ጠንካራ ዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስር አለመኖሩ በሀገራችን የትምህርት ጥራት አሳሳቢና አነጋጋሪ እንዲሆን አድርጎታል።
በርካታ ሀገሮች በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ውስጥ ኢንዱስትሪዎች አሉ ፣ይህም ሁኔታ ተማሪዎችን ምርታማ በማድረግ ለሀገር ከፍተኛ የሆነ ሥራን እንዲሰሩ አድርጓቸዋል። በኛ ሀገር ደግሞ ከፖሊሲ በዘለለ ተማሪዎች በተግባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አለመማራቸው ከንድፈ ሃሳብ የዘለለ እውቀት እንዳይኖራቸው በማድረግ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል እንዳይኖር ማድረጉን ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም አድማስ ዩኒቨርሲቲ ለጥናትና ምርምር ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለሀገር የሚጠቅሙ ሥራዎችን እየሰራ ነው። ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ በመስራት በተግባርና በንድፈ ሀሳብ ጠንካራ የሰው ኃይል እያፈራ ይገኛል። እንዲሁም ለመንግስት በወቅቱ ግብር በመክፈልና የማህበረሰብ ሥራዎችን በመስራት ለሀገር እድገት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
ሞገስ ፀጋዬ