አዲስ አበባ፡- በ2011 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የ4ሺ597 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ ማለፉን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገ/እግዚአብሔር እንደገለፁት፣ በ2011 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የ4ሺ597 ሰዎች ህይወት በትራፊክ ያለፈ ሲሆን፣ የትራፊክ አደጋው አገሪቱ ካላት አነስተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር አኳያ ሲታይ እጅግ የከፋ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በትራፊክ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ4 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ወይዘሮ ሙሉ አስረድተዋል። የመንገድ አጠቃቀም ህግና ሥርዓት ባለመከበሩና ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ የመንገድ ትራፊክ አደጋ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እያስከተለ ይገኛልም ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየእለቱ የሚያጋጥሙትን አደጋዎች ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ አዳዲስ ህጎችን የማውጣት፣አዳዲስ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ በማድረግ፣ ሥራ ላይ ያሉት ህጎች ማሻሻል፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ በዘርፉ ውስጥ ድርሻ እንዲኖረው የማድረግ፣ ተቋማዊ አደረጃጀት በአዲስ መልክ በመዋቀርና ሌሎች ገንቢ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ማእረግ ገብረ እግዚአብሔር