አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሚከበረው የሠላም ቀን አንድምታው የላቀ ቢሆንም ሠላም ከቃላት ባለፈ በተግባር መደገፍ እንዳለበትና ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን በማስቀደም ሊከናወን እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር እንዳወቀ ፀጋው ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የሠላም ቀን ማክበሩ የሰላም እሴት ዋጋው የላቀ መሆኑን ለማሳየት የታለመ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱን ሠላም የሚነሱ ኢ-ህገመንግሥታዊ እና ኢ-ሞራላዊ ክስተቶች እየተበራከቱ ስለመምጣታቸው አብነት ነው። በመሆኑም የሠላም ቀን ማክበሩ አስፈላጊ ቢሆንም ከቃላት ባለፈ ግን ተግባር ሊታከልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሠላም የሠላም ቀን በማክበር አሊያም ደግሞ የአንድ ቀን ኮንፈረንስ በማካሄድ ሊረጋገጥ እንደማይችል የገለፁ አቶ ኑሩ፤ መንግሥትና ህዝብ ስለሠላም አስፈላጊውን ዋጋ ሊከፍሉ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም ሠላምን የሚያውኩ አካላት የሠላም ቀን ስለተከበረ ብቻ ሠላምን እንደማይሹና በህግ አግባብ ሊዳኙ እንደሚገባ አሳስበዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋሉ ከሞራል እና ሰብዓዊነት ያፈነገጡ ተግባራትም በወቅቱ ሊታረሙና ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ የግድ ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ፣ የሠላም ቀን ለማምጣት ሰዎች ልባቸውን ለመግዛትና መልካም ተግባራትን ለማከናወን ሠላም ወሳኝ ነው። እሳቤው የሰዎች ሞራልን ካልተለወጠ ቀናት ብቻ ለውጥ አያመጡም። መገናኛ ብዙሃንም የሠላም ጉዳይን አንድ ቀን ጉዳይ አድርገው ካሰቡ ስኬታማ አይሆኑም። በመሆኑም በዚህ ረገድ በሰፊውና በተደጋጋሚ ሊሠሩ ይገባል። የአስተሳሰብ ለውጥም ሊመጣ የሚችለው በሂደት እንጂ በአንድ ቀን ለውጥ አይመጣም።
ከዚህም በዘለለ ሌሎች ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊከበሩም ይገባል። ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ በዓል ተከብሮ የነበረ ሲሆን ያመጣው ለውጥ ሊገመገም ይገባል፣ መልካም ጅምሮችም ሊበረታቱ ይገባል ብለዋል። ከማህበረሰቡ አስተሳሰብና ሥነልቦና ጋር የተጋመዱ ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተግባቦት መምህር የሆኑት አቶ ገዛኸኝ በርሄ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩ ተስፋ ሰጪ ለውጦች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዜጎች ቅድሚያ ለሠላም ሊሰጡ ይገባል። በተለይም ደግሞ በሐሰተኛ መረጃዎች ላይ በመመስረት የዜጎችን ሠላም የሚያውኩ ሰዎችም ከስህተታቸው ታርመው ወደ ተሻለ የእሳቤና ተግባቦት መምጣት ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥትም በሠላም እሴቶች ላይ አበክሮ ሊሠራ ግድ ይላል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችንም ለመፍታት በመነጋገር እና ተግባራት ስልቶችን መንደፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። አልፎ አልፎ በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በኃይል አሊያም ደግሞ በአመጽ መንገድ ብቻ መፍትሄ ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት መሆኑን ያብራሩት አቶ ገዛኸኝ፣ በርካታ አገራት ተግባቦትንና ድርድርን ወደ ጎን በመተው ኃይል መጠቀማቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው አብራርተዋል። ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በሶሪያ፣ ሱዳን እና ሊቢያ የሚስተዋሉ ችግሮች ለሠላም ቅድሚያ አለመስጠትና ተጋባቦትን እንደ ዋንኛ የሠላም መሣሪያ ካለመጠቀም የመነጨ መሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር