አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወኗቸው ተግባራትና በሰጡት አመራር ባመጡት ለውጥ 12 ዓለም አቀፍ ሽልማቶች እና እውቅናዎችን አግኝተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የአፍሪካ የፆታ ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ባከናወኑት ተግባር የ2018 ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡
በ2018 በዩጋንዳ ብሄራዊ የጀግኖች ቀን በዓል ላይ በካምፓላ የተገኙት ዶክተር ዓቢይ፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ ሽልማት የሆነውንና ለአፍሪካ ጀግኖች የሚሰጠውን የክብር ሜዳሊያ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሚሶቮኒ እጅ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ባመጡት ሰላም በ2018 ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን ከፍተኛ ሽልማት በአቡዳቢ ከሀገሪቱ ልዑል ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እጅ ተቀብለዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማምጣት፣ ለማስጠበቅና ለማቆየት ባደረጉት አስተዋፅዖ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) ፊሊኒክስ ሃሬፍ ቢኒይ ሽልማት የ2019 አሸናፊ ሲሆኑ፣ የዚሁ ዓመት የዩኔስኮ የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነውም ተመርጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ በሻንግሪ ላ ለንደን ይፋ በተደረገው የዓለም የቱሪዝም ሽልማት በቱሪዝም አመራር የ2019 አሸናፊ ሆነዋል። በጀርመን የፍራንክፈርት ከተማ የሚገኘው የፍራንክፈርት የሰላም ጥናት ማዕከል የ2019 የሔስያን የሰላም ሽልማቱን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ይገባቸዋል ብሎ መርጧቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሽልማቱ የበቁት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ታሪካዊ የሰላም ስምምነት በመፈፀማቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በመጪው መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ሽልማታቸውን በጀርመን ፍራንክፈርት ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአሜሪካ የሚገኘው እና ዓለማችን ታዋቂውና ተነባቢው ሳምንታዊ የዜና መፅሄት በሆነው የታይም መፅሄት በመሪዎች ዘርፍ የ2019 የዓለማችን 100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል ዶክተር ዓቢይ አህመድን አንዱ አድርጎ መርጧቸዋል።
በአሜሪካን ሀገር የሚገኘው ፎሬን ፖሊሲ የተባለ ህትመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድን የ2019 በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ባለብሩህ አእምሮ አሰላሳዮች ዝርዝር ውስጥ አንዱ አድርጎ አካቷቸዋል፡፡
ተቀማጭነቱን እንግሊዝ ባደረገው በኒው አፍሪካ መፅሄት የ2018 የዓለማችን 100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥም አንዱ ሆነው የተመረጡት ዶክተር ዓቢይ አህመድ፣ በዚሁ ሀገር በሚገኘው የአፍሪካ ሊደርሺፕ መፅሄት የ2018 የአፍሪካ ምርጥ ሰውም ተብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ የ2019 የኖቬል የሰላም ሽልማት እጩም ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥም ከልዩ ልዩ ድርጅቶች እና ተቋማት እውቅና እና ሽልማቶችን ማግኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ድልነሳ ምንውየለት