አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ሳይንስ ፋኩልቲ ከ100 ዓመታት በላይ ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የተሰበሰቡ የእጽዋት እና እንስሳት ናሙናዎችን የያዘው የሙዚየም ህንጻ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ባለሙያዎች ገለጹ።
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በበኩሉ ጥናት አድርጎ በቅረቡ ህንጻውን ለማደስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲው ዲጂታላይዜሽን ባለሙያ አቶ ፍሰሃ ጌታቸው በበኩላቸው ህንጻው በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን የተገነባ መሆኑን አስታውሰው በፍጥነት እድሳት ካልተደረገለት ኢትዮጵያ ያሏትን ከ160ሺ በላይ የዕጽዋት ምርምር ሃብቶች ልታጣ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል። ህንጻው ከማርጀቱ እና ከመሰነጣጠቁ ባሻገር ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የሀገሪቱ ሀብቶች በጠባብ ቦታ ታጭቀው እንዲቀመጡ አስገድዷል።
ሙዚየሙ የተጨናነቀ ከመሆኑ አንጻር ከዚህ ቀደም እሳት መፈጠሩን ያስታወሱት አቶ ፍሰሃ፣ሰዎች በወቅቱ በመኖራቸው በፍጥነት ባይጠፋ ኖሮ አደጋው በሙዚየሙ የሚገኙትን መተኪያ የሌላቸውን ሃብቶች የማውደም አቅም ነበረው ። በሌላ በኩል ባለሁለት ወለል ህንጻ የሆነው ሙዚየም የላይኛው ወለል ፈርሶ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶ እንደሚያውቅ አስረድተዋል። በመሆኑም ለህንጻው አፋጣኝ እድሳት ከማከናወን ባሻገር በቋሚነት ዕጽዋቱን ጠብቆ ለምርምር ሥራ ማዋል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ከውጭ አገራት እና አገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሰበሰቡ የእጽዋት ዝርያዎች በሙዚየሙ መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ፍሰሃ፤ ከዚህ በተጨማሪ የእንስሳት አካላት ማሳያ ሙዚየም እና የተለያዩ ተፈላጊ የጥናት መጽሐፍት በህንጻው መኖራቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም የችግሩን ግዝፈት ተመልክቶ በአንድ ጀንበር በርካታ ሃብት ሊጠፋ የሚችልበትን አደጋ በማጤን የእጽዋት ናሙናዎቹን ከነሙሉ መረጃቸው ወደዲጅታል መረጃ ለመቀየር ጥረት ማድረግ ይገባል። በዋናነት ግን የህንጻ ግንባታ እና እድሳቱ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነ በየጊዜው ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመሰጠቱን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት ባዮሎጂ እና ባዮዳይቨርሲቲ ማኔጅመንት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ወርቅነህ እንደገለጹት፣ በሳይንስ ፋኩልቲው በሚገኘው ሙዚየም ውስጥ ከ100 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው የእጽዋት ሃብቶች ለአደጋ ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፕሮጀክት ኃላፊ ኢንጂነር አርዓያ ተክለሃይማኖት ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በአራት ኪሎ ሳይንስ ፋኩልቲ የሚገኘውን የሙዚየም ህንጻ እርጅና በአግባቡ እንደሚያውቁ ተናግረዋል። ሙዚየሙ በያዛቸው የሀገር ሃብቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በማሰብ ለህንጻው ጥገና ለማከናወን ጥናቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለህንጻው እድሳት ምን ያህል ወጪ እንደተመደበ እንደማያውቁ የተናገሩት ኢንጂነር አርዓያ፣ የብሩ መጠን ከጥናቱ በኋላ የሚታወቅ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው፣የሙዚየሙን መጨናነቅ ለመቀነስ የማስፋፊያ ግንባታ ከዩኒቨርሲቲው አቅም ጋር ታይቶ ወደፊት ምላሽ የሚሰጠው ቢሆንም በ2012 ዓ.ም ግን ሙዚየሙን ወደማደስ ሥራ ይገባል። በመሆኑም በውስጡ የያዛቸውን ንብረቶች በማይጎዳ መልኩ ደረጃ በደረጃ ክፍሎቹን እያደሱ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ጌትነት ተስፋማርያም