• የአፋርን ሕዝብ ፍላጎት መሰረት አድርገው ሊሠሩ ይገባል
• የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በዕውቀት እንደሚፈቱ ይጠበቃል
ሠመራ፡- አዲስ የተሾሙት የአፋር ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ አባላት የክልሉን ሕዝብ ፍላጎት መሰረት በማድረግ እንዲሁም የክልሉ ሠላም በማስጠበቅበና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሊሠሩ እንደሚገባ የአብዴፓ ሊቀመንበርና የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ገለፁ፡፡
የአፋር ክልል ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ አስቸኳይ ስብስባውን ትናንት በማካሄድ አቶ አወል አርባን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ የሾመ ሲሆን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ያቀረቡትን 21 የካቢኔ አባላት ሹመትንም አፅድቋል፡፡
የአብዴፓ ሊቀመንበርና የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በወቅቱ እንደገለፁት፤ አዲስ የተሾሙት የካቢኔ አባላት የክልሉን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አቅም አላቸው ተብሎ የታመነባቸው ሲሆኑ፣ የህዝቡን ፍላጎት ለማርካትም ከህዝቡ ጋር በቅርበት መሥራት ይጠበቅብቻዋል፡፡ ከህዝብ ጋር በቅርበት የመሥራት፣ በአግባቡና በተደረጀ መልኩ መሥራት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ የልማት ጥያቄዎችን፥ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተትን በእውቀት ሊፈቱ እንደሚገባቸው ሊቀመንበሯ አስገንዝበው፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የተሻሻለ የአስፈፃሚ አካላት ማቋቋሚያና ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ አዋጁን አሁን ካለው አገራዊ ለውጥ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንደተሠራም ተናግረዋል፡፡
አዲሱ አደረጃጀት አቅምን፥ ሀብትና የሰው ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችልም ገልፀዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር፣ የመሰረተ ልማት፣ የአገልግሎት አሰሰጣጥ፣ የትምህርት ጥራት የተደራሽነት ችግሮችን ለመፍታት በተደረጀና በብቃት መምራት የሚያስችል ኃይል መደረጃቱንም አመልክተዋል፡፡ ለውጡ እስከ ታችኛው መዋቅር እንደሚወርድም ኢንጅነር አይሻ አስገንዝበዋል፡፡
አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው፤ «በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው ለውጥ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በክልሉም በተመሳሳይ ይተገበራል» ብለዋል፡፡
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለፃ፤ የመንደር ማሰባሰብና የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሞች የህዝቡን ተጠቃሚነት ባማከለ መንገድ ይካሄዳሉ፡፡ ከአገር ሽማግሌዎች የሴትና የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት ልማትና ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባር ይከናወናል፡፡
በክልሉ ሠላም የማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን በማረጋጥ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በመቻቻል እንዲኖሩ የማድርግ ሥራ እንደሚሠራ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ፍትህን የማስፈንና ብሔራዊ አንድነትን የማጠናከር ሥራም እንደሚተገበርም ተናግረዋል፡፡ «የተለያዩ የማህበረሰብ አደራጃጀቶችን በመፍጠር ልማታዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የጋራ ርብርብ ይደረጋል» ሲሉም ገልፀዋል፡፡
በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ለማፍራት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት አቶ አወል «የአፋር ህዝብ ያለውን ባህላዊ መዋቅር ከመንግሥታዊ መዋቅሩ ጋር በማጣመር ይሠራል» ብለዋል፡፡ ሴቶችንና ወጣቶችን በየደረጀው ባለው የመንግሥት መዋቅር በፍትሐዊ መልኩ ለማሳተፍ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት የአስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት የቀረበው ረቂቅ አዋጅም በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን፣ 18 ቢሮዎች በአዋጁ ላይ በመመስርት አቋቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
በዘላለም ግዛው