የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለአገሪቱ ኢንዱስትሪያዊ ሽግግርን ያመጣል ተብሎ ብዙ እየተሰራበትና ውጤቶችም እየተመዘገቡበት ነው። ዘርፉ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣ ዘንድ እየተከናወኑ በሚገኙና በቀሪ ተግባራት ዙሪያ ከፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ከአቶ አስፋው አበበ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው የተቋቋመበት ዓላማ ምንድን ነው?
አቶ አስፋው፦ ዋና አላማው ለኢንዱስትሪው መዋቅራዊ ሽግግር መሰረት የሚሆኑ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በብዛትና በዓይነት በመላው አገሪቱ ከግብርናው ጋር ተሳስረው መስራት እንዲችሉ በሂደትም ግብርናውን ተክተው ለኢንዱስትሪው መሰረት እንዲጥሉ ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር ተቋሙ በምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ አስፋው፦ በተለይ ባለፈው ዓመት ዋና ግባችን ብለን የምንወስደው አዳዲስ አምራቾችን መፍጠርና የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች ማቅረብ ነው፣ በራሳቸውም ይሁን በእኛ ጥረት ከዚህ በፊት ወደ ሥራ ገብተው የነበሩትን ያሉባቸውን ችግሮች የመለየት፣ የምርታማነታቸውን ደረጃ የማሳደግና የሰው ኃይል የመቅጠር ብቃታቸውን የመጨመር ሥራ ነው።
በሌላ በኩልም ምንም እንኳን አገሪቱ ያልተረጋጋች ቢሆንም ለአምራች ዘርፉ ማሽነሪ በብድር እንዲወስድ በማድረግ߹ ሼዶች በማዘጋጀትና ክህሎቱ ያላቸውን ወጣቶች ወስዶ ወደ ምርት በማስገባት ለምርቱ የሚያስፈልገውን ግብዓት በማቅረብ ላይ ነን፡፡ ከዚህ አንጻር የተሰራው ሥራ ለእኔ በቂና በችግርም ውስጥ ሆነን መስራት እንደምንችል ያረጋገጥንበት ዓመት ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ምን ያህል ለመስራት አቅዳችሁ ነበር? ምን ያህሉንስ አሳካችሁ?
አቶ አስፋው፦ በዓመቱ ሰባት ሺ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም አቅደን ያሳካነው ሁለት ሺ700 ያህሉን ነው። በተመሳሳይም በሥራ ላይ የነበሩ ሁለት ሺ 400 ኢንዱስትሪዎችን ለማጠናከር አቅደን ሁለት ሺ 119 ያህሉን አጠናክረናል። እነዚህን ሁለቱን ደምረን ስንመለከት ልንፈጥር ካቀድናቸው 141ሺ አዳዲስ የሥራ እድሎች መካከል አዲስ በተቋቋሙት 25ሺ፣ በነባሮቹ ደግሞ 31ሺ ዜጎች ሥራ አግኝተዋል። ይህ የሥራ እድል ከሌሎቹ የሚለየው ቋሚ በመሆኑ ነው። ከእቅድ አንጻር ስናየው ግን 40 በመቶ ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን ለምሳሌ ማሽነሪ በብድር ወስዶ ተክሎ ‹‹ይህንን ብሰራ ችግር አይገጥመኝም›› ብሎ የሚገባው ሰው መጠን ዝቅተኛ ከመሆኑ አንፃር ዓመቱ ከዚህም በታች ውጤት ሊመዘገብበት ይችል ነበር፤ ሆኖም በመንግሥትም የካፒታል ሊዝ ፋይናንሶችንና ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በሚገኙ ድጋፎች በመጠቀም ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፦ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ ያለው የሥራ እድል ፈጠራ ከዚህም በላይ ዝቅተኛ እንደሆነ መረጃው አለንና ሪፖርቱ ትክክል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?
አቶ አስፋው፦ አይ ወሬ እኮ አይደለም። አሁን ላይ 56 ሺ የሥራ እድል ተፈጥሯል እያልን ነው፣ ያቀድነው 141ሺ ነበር፣ይህንን ስናይ 40 በመቶ ነው፣የተከናወነው ዝቅተኛ ነው፣ይህ ማለት ደግሞ ምንም የማይሸሸግ ሀቅ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እኔ ጋር ያለው መረጃ ግን ከዚህ በታች እንደሆነ ነው የሚያሳየው?
አቶ አስፋው፦ እንግዲህ አንድ ነገር እንዲረጋገጥ የምፈልገው ይህ መረጃም ተሟልቶ ባለመምጣቱ እንጂ ሙሉ ቢሆን ኖሮ ከዚህም በላይ የተፈጠሩ የሥራ እድሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያሳያል።
አዲስ ዘመን፦ ለዚህ እርግጠኛነትዎ ወይም አልተሟላም ብለው ላሉት ነገር ማስረጃ ማቅረብ ይችላሉ?
አቶ አስፋው፦ ወረዳዎችና ዞኖች፤ ዞኖችና ክልሎች የተሳሰሩ አይደሉም። በዚህም ምክንያት ታች የተሰራውን ሥራ ተቀባብሎ እኛ ጋር የማድረስ ክፍተት ነበር። ሄደንም ስናይ ሥራውን የሚሰሩት ሰዎች እያሉ እንኳን ሪፖርቱ በትክክል አይመጣም። እኔም ዝም ብዬ አይደለም የማወራው፣እጄ ላይ የመጣውን መረጃ እያየሁ ነው።
ለምሳሌ ኦሮሚያን ብንወስድ በቆዳ ስፋት ትልቅ ቢሆንም የመጣልን ሪፖርት ግን ዝቅተኛ ነው፣ይህንን ይዘን ነው የምንናገረው ከስፋቱ አንጻር ትንሽ ነው ወይም ብዙ ነው ብለን የምንጨምረውም የምንቀንሰውም ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፦ አዲስ አበባ ከተማ ላይስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ አስፋው፦ ዝቅተኛ ነው። ከተማው ላይ አንጻራዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ቢኖርም አፈጻጸሙ ግን ዝቅተኛ ነው። ማሽነሪ ወስዶ፣ ሼድ አግኝቶ፣ መብራት ሳይቆራረጥበት ተጠቅሞ ወደ ሥራ ለመግባት በጣም አስቸጋሪ ነው። ችግሮቹን ተቋቁሞም ለራሱ እንዲሁም ለሌሎች የሥራ እድል ፈጥሮ የሚሰራን አካል ማግኘትም እንደዚሁ ከባድ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያሉት አምራቾቻችን በሚፈለገው ደረጃ ላይ ናቸው ወይ? አዳዲሶቹስ ወደ ሥራ እየገቡ ነው ወይ? ብለን ብንጠይቅ … አይደሉም።
አዲስ ዘመን፦ እቅድና አፈጻጸሙን በቁጥር ማየት ይቻላል?
አቶ አስፋው፦ እቅዱ በጣም ትልቅ ነበር፤ ለምሳሌ አዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም፣ ነባሮቹን በማጠናከርና የሥራ እድል በመፍጠር በኩል ታቅዶ የነበረው 17ሺ ነበር፤ አፈጻጸሙ ግን ስድስት ሺ 500 መቶ አካባቢ ነው። ይህ የሚያሳየው በሥራ እድል ፈጠራ ላይ መጓዝ የተቻለው 40 በመቶ ብቻ መሆኑን ነው። ስለዚህ አገሪቱ የነበረችበት ሁኔታ በሁሉም አካባቢዎች ላይ ተጽዕኖ ነበረው።
አዲስ ዘመን፦ ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን ምክንያቱ የአገሪቱ የሰላም ችግር ብቻ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?
አቶ አስፋው፦ ሰው መቼም የሚገበያየው ሰላም ሲኖር ነው አይደል? ታዲያ የሰላም ጉዳይ’ማ ወሳኝ ነው። በሌላ በኩልም በየወረዳው ያለው አመራር ትኩረት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑም አፈፃፀሙ የተፈለገውንና የታቀደውን ያህል እንዳይሄድ አድርጎታል።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ወጣቶችን መልምዬ ወደ ሥራ አስገባለሁ ቢልም በሼድ አቅርቦት፣ ውሃ መብራትና ስልክ የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን በማመቻቸት በኩል ደግሞ ቅሬታዎች ይነሱበታልና በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ አስፋው፦ ይህ በጣም ትክክል ነው። በአዲስ አበባ ላይ እንኳን ችግሩን እንፍታ ብለን ያሰብነውን የክላስተር ልማት እውን ማድረግ አልቻልንም። ይህ የክላስተር ልማት የበርካታ ዜጎችን የማምረቻ ቦታ ችግርን የሚፈታ ቢሆንም በቦታው ላይ ያሉትን ሰዎች ለማስነሳት ሲሞከር የካሳ ክፍያው ችግር ገጥሞታል። ይህንን የሚወስን አካል ጠፍቶ ሥራው ቆሟል።
በሌሎችም ክልሎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ላይ የካፒታል እጥረት ስለነበር አንድ ህንጻ እንኳን ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ከዚህ አንጻር ክልሎች በበጀታቸውም ይሁን በሌላ ገንዘብ ሼዶቹን ሰርተው ለተጠቃሚው የማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ቀደም ብለው የተሰሩትንም በተለያየ መንገድ ሥራ ላይ ሳያውሉ የቀሩትን ለይተን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት ተደርጓል። ዞሮ ዞሮ በሼድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በጥሬ እቃና በፋይናንስ አቅርቦት ላይ አሁንም በሚፈለገው ደረጃ እየተሄደ አይደለም። በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚገቡት አምራቾች የተለየ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ምክንያቱም ውጣ ውረዱ እንደ ንግድ ወይም አገልግሎት ዘርፎች ቀላል ባለመሆኑ። ይህንን የተረዳ አመራር፣ ፈጻሚና የፋይናንስ ተቋማት መኖር ሲችል ብቻ ነው ከግብርና ቀጥሎ የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለኢንዱስትሪው መዋቅር ተቀባይ የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ዘርፉን በዚህ ልክ የተረዱ አመራርና የፋይናንስ ተቋማት የሉም ማለት ነው?
አቶ አስፋው፦ የፋይናንስ ተቋማት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቅድሚያ እንሰጣለን ከማለት በዘለለ በተግባር መደገፍ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል። እነሱን ሊያበረታቱ የሚችሉ አዳዲስ አሰራሮችንም መንደፍ ይጠይቃል። ሼድና የኤሌክትሪክ ኃይል ቅድሚያ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንሰጣለን ቢባልም፣ በተባለው ልክ ዘርፉ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? ቅድሚያ ማግኘት ያለበት ለምንድን ነው? የሚለውን በትክክል ተረድቶ ያንን
ሊያግዝ የሚችል አሰራር መዘርጋት ላይ ክፍተት አለ።
አገራችን ብዙ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሃብት ያላት ናት፡፡ እነዚህን አቀናጅቶ መስራትና ማምረት ተችሎ ለህዝቡ እንኳን ቢቀርብ ገበያው ሰፊ ነው። በዚሁ ልክ የማደግ እድላችንም ትልቅ ነበር የሚሆነው። ይህንን ለማድረግ ግን የአስተሳሰብ አንድነትን በሁሉም አካባቢ ላይ ማምጣት የሚቀረን ሥራ ነው።
ለምሳሌ በጤና ሚኒስቴር ሥር የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት የሚሰጡና ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ ህብረተሰቡን ስለ ጤናው አጠባበቅ ግንዛቤን የሚፈጥሩ ባለሙያዎች አሉ። በተመሳሳይ በግብርና ኤክስቴንሹኑም በኩል ባለሙያዎች በእያንዳንዱ አርሶ አደር ማሳ ላይ በመሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ይሰጣሉ፤ የተመለከቱትን ችግር ደግሞ እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረስ በመላክ መፍትሔ ያሰጣሉ።
ወደ ኢንዱስትሪው ስንመጣ ግን አሰራሩ ገና መስመር አልያዘም፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ኢንዱስትሪው ቀን በቀን የሚገጥመውን ችግር እየለየ መፍትሔውንም ጎን ለጎን እያስቀመጠ የሚሄድ፣ እውቀት ያለውና በእያንዳንዱ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገባና ችግሩንም እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ድረስ አምጥቶ መፍትሔ የሚያሰጥ ሂደት ገና አልተገነባም። ሆኖም ኢንዱስትሪዎቻችንን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስና ከግብርና ወጥተንም ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር የምንፈልግ ከሆነ ይህንን መሰረት መጣል አለብን።
በጠቅላላው በማኑፋክቸሪግ ዘርፉ ላይ ያለው የአመራሩም ሆነ የተቀረው ህብረተሰብ ግንዛቤ በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም። ከመናገር ባለፈ የተሰራ ሥራ ባለመኖሩ እኛ ማምረት ስንችል በርካታ ምርቶች ከውጭ ይገባሉ፤ከዚህ ልንወጣ የምንችለው ደግሞ በሁሉም ደረጃ የሚገኝ ፈጻሚና አመራር ለኢንዱስትሪው ያለው እይታ ያደገ ሲሆን ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአመራሩና በፈጻሚው በኩል ክፍተቶች አሉ፣ ሆኖም ኤጀንሲው ጥቃቅንና አነስተኛ ብሎ ሼድ የሰጣቸው አካላት ዛሬ ላይ ከመካከለኛም አልፈው ባለሀብት ደረጃ ቢደርሱም የያዙትን ሼድ ለተተኪው አላስረከቡምና እናንተስ ለምንድን ነው ኃላፊነታችሁን መወጣት ያልቻላችሁት?
አቶ አስፋው፦ እዚህ ላይም ጥንቃቄ ይጠይቃል። ለምሳሌ ለአምስት ዓመት በሼድ ውስጥ እንዲሰሩ ተብለው የገቡ ነገር ግን ሀብት አፍርተው ወደሚቀጥለው ደረጃም ተሸጋግረው ሌላ ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲለቁ ተደርጓል። በየዓመቱም ሞዴል ተብለው የሚለዩት እነሱ ናቸው። ሆኖም በወረዳዎቻችንና በከተሞቻችን ላይ ያለው ሁኔታ ወጥ ባለመሆኑ ስርዓት ባለው መንገድ በትክክል እየተመራ አይደለም። ይህ ደግሞ አብዛኞቹ ሀብት እንኳን ፈጥረው ጥቃቅን ሆነው መኖርን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል። ይህ እንዲስተካከልም በየጊዜው ውይይት ይደረጋል፣ግን መሆን ባለበት ልክ ውጤት አልመጣም ።
አዲስ ዘመን፦ መሆን ባለበት ልክ ውጤት እንዲመጣ ማድረግ የእናንተ ኃላፊነት አልነበረም?
አቶ አስፋው፦ ኢንተርፕራይዞቹ በተለይ ሒሳብ አያያዛቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለባቸው። በየቀኑ የሰሩትንና ለገበያ ያቀረቡትን በትክክል መዝግበው አይዙም። ይህ ባለመሆኑ ደግሞ ‹‹በዓመት ምን ደረጃ ላይ ደረሱ›› የሚለውን እነሱም አያውቁትም፤እኛም የጠራ መረጃ ስለሌለን ሁኔታው እየተፈታተነን ነው። ምናልባት ችግሩን ለመፍታት አዳዲስና ዘመናዊ አካሄዶችን ማስቀመጥ ይጠይቃል። አንድ ሰው ሲሸጥም ሲገዛም መረጃውን መዝግቦ ከያዘ ሥራውን በስንት ጀመረ? አሁን ምን ላይ ደረሰ? የሚለውን በትክክል ለማወቅ ያግዛል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ እስካሁን አልተፈጠረም ።
በሌላ በኩል ተቋሙ ትኩረት አድርጎ ነው የሚሰራው በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ ላይ ባሉትና በነባሮቹ ላይ ብቻ ነው። ከዚህ ተቋም ተገንጥሎ የወጣ የሥራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ የሚባል ተቋም አለ። በከተሞች ደግሞ አነስተኛና ጥቃቅን ተብሎ የተደራጀ ተቋም አለ፤ ከዚህ አንፃር ጀማሪ ለሆኑት ሼድ የሚሰጠውና የሚከታተለው ሌላ ነው፤ እኛ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በዚህ ደረጃ ላይ መሳተፍ አቁመናል። እኛ ተሳትፎ የምናደርገው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ብቻ ለገቡትና በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ ላሉት አምራቾች ነው። በመሆኑም ሌሎቹን ሊከታተል የሚገባው ሌላ አካል ነው።
አዲስ ዘመን፦ እናንተ በምትከታተሏቸውስ ላይ ያለውን ችግርን ፈታችኋል?
አቶ አስፋው፦ ችግሩን ውጫዊ እያደረግኩ አይደለም፤ በእኛ ስር ያሉትም የማደግና የመስፋፋት ጥያቄን ያቀርባሉ፣የተሻለ ሼድ ይፈልጋሉ፣ ይህንን ለመመለስ ደግሞ በየክልሉ የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን የሚል ተቋቁሞ ሼዶቹን ተረክቦ ለአነስተኛ ለመካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ እያስተናገደ ነው። ይህም ቢሆን ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ተፈትተዋል ማለት አይደለም። እዚህ ላይ እኛ ታች ወርደን ኮርፖሬሽኑ የተሰጠውን ስልጣን ተጋፍተን ልቀቅ አትልቀቅ የሚል ሥራ አንሰራም፣ እኛ የምንሰራው ማኑፋክቸሪን ዘርፍ ላይ መግባት አዋጭ ነው የሚለውን የማስተዋወቅ ሥራ ነው ።
አዲስ ዘመን፦ የዓለም ባንክ ሰባት ቢሊዮን ብር ገደማ ለመሳሪያ ሊዝ አቅርቦት በሚል ድጋፍ ቢያደርግላችሁም እስከ አሁን የተጠቀማችሁት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብሩን ብቻ ነው፣ ገንዘቡን የሚጠቀምበት ጠፍቶ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት?
አቶ አስፋው፦ የዓለም ባንክ የሰጠው ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንጂ ለእኛ አይደለም። በመሆኑም ሥራውም የእርሱ ነው። ባንኩ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለዚህ ዓመት ይዣለሁ ካለ ሊጠየቅ የሚገባው እርሱ ነው። ሌላው ሊታወቅ የሚገባው ደግሞ የዓለም ባንክ ለልማት ባንክ የሰጠው ገንዘብ ሰባት ቢሊዮን ሳይሆን ሶስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው በሥራ ላይ ውሏል ።
ዞሮ ዞሮ አጠቃቀሙ ለምን ዝቅተኛ ሆነ ለሚለው አንደኛው ቢሮክራሲው ነው። ሌላው አገሪቱ የነበረችበት ሁኔታ ነው። ዋናው ደግሞ ገንዘቡን ተጠቅሞ ማሽን ተወስዶ ሲኬድ ሼድ ያስፈልጋል፤ ይህ ባለመሆኑ ደግሞ ገንዘቡን መጠቀም አልተቻለም።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ምን ሰራ?
አቶ አስፋው፦ የውስጥና የውጭ ብለን የለየናቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ። የውጭ ያልናቸው ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ያለው የአቅርቦት ድጋፍን በተመለከተ የምንሰራቸው ሥራዎች ሲሆኑ በዚህ ዙሪያ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ ጥረት እናደርጋለን። እስከ አሁን ባደረግነው የጋራ ጥረትም ውጤት ያመጡም ያላመጡም አሉ።
የውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ናቸው የምንላቸውን በየዓመቱ እንለያለን፤ በልየታው መሰረት ደግሞ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን። ከእኛ አቅም በላይ ሆነው በሌሎች ሊታዩ የሚገባቸውን ደግሞ በሚመለከታቸው አካላት ታይተው መፍትሔ እንዲሰጣቸው የማድረግ አካሄዶችም አሉ።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ በተለይም ዝውውርን በተመለከተ ከህግ ውጪ ይሰራል የሚባል ነገር አለና እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ አስፋው፦ ይህ ስህተት ነው፣ ዝውውር ህጉን በተከተለና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚከናወን ነው።
አዲስ ዘመን፦ እንደውም ቅሬታ የተነሳው በተለይ በምክትል ዳይሬክተርነት ቦታ ላይ በሚመጡት ሰዎች ዙሪያ ላይ ነውና የእነርሱ አመጣጥ ህግን የተከተለ ነው?
አቶ አስፋው፦ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ተሿሚዎች ናቸው፤ ተሿሚ ደግሞ በዝምድና አልያም በሌላ መንገድ ሊመጣ አይችልም፤ መንግሥት አውቆት አሰራሮችን ተከትሎና ለቦታው ብቁ መሆኑ ተረጋግጦ ነው የሚላከው። ይህ በእውነቱ በየትኛውም ሁኔታ ሊቀርብ የሚችል ችግር አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ ከጨረታ ጋር በተያያዘ ተቋሙ የገባበት ችግር እንዴትና ለምን ተፈጠረ ?
አቶ አስፋው፦ ተቋሙ እንደ ማንኛውም መስሪያ ቤት ጨረታን በህግና በስርዓት የሚመራ ቢሆንም በአሰራር ሂደቱ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ደግሞ ይኖራሉ፤ በጨረታ ሂደት ውስጥ ትክክለኛ ያልሆኑ አካሄዶች ይከሰታሉ፤ አንዳንዴም ደግሞ አካሄዱን ተከትሎ የሚደርሱ ጥቆማዎች አይጠፉም ። በዚህ ሁኔታ እየሄደ ያለን ጨረታ ደግሞ እንዲቆም የሚደረግበት አግባብ ይፈጠራል ።
በዚህ ጊዜ ደግሞ ጨረታው ላይ የገባው ሰውና ተቋሙ ሊካሰሱ ጉዳያቸውም ወደ ፍርድ ቤት የሚሄድበት አግባብ ይፈጠራል ማለት ነው። ፍርድ ቤት ደግሞ የራሱን እይታ አይቶ ብይን ይሰጣል ። እኛም ያጋጠመን ይኸው ነው።
ጉዳዩም ተቋሙ ያወጣውን ጨረታ አንድ ግለሰብ አሸነፈ፤ ሆኖም እኔ በግሌ ሳየው ተጫራቹ ሂደቱን አላሟላም ብዬ ውድቅ እንዲሆን አደረኩ፤ሆኖም ወደ ህግ ሲሄድ ያሟላል ተብሎ በተቋሙ ላይ ተፈረደ። አሁንም ቢሆን የእኔ እምነት ተጫራቹ ጨረታውን ለማሸነፍ አያሟላም የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፦ ግን እኮ ፍርድ ቤቱ ‹አሟልቷል›› ብሎ ፈረደለት፤ እርሶ አላሟላም የሚሉት ከምን አንጻር ነው?
አቶ አስፋው፦ እኔ አላሟላም ያልኩት ለምሳሌ አንቺ ጥያቄ ማቅረብ ሲገባሽ ሌላ ሰው አንቺን ተክቶ ቢያቀርብና ቢያልፍ ይህ ሂደት የተሟላ አልነበረም ማለት ነው። በጨረታ ሂደቱ ላይ የተከሰተው ይህ ነው። እንዲህ ዓይነት በአቋራጭ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን አጥርቶ መሄድ ደግሞ እኛንም ከተጠያቂነት የመንግሥት ገንዘብንም ከብክነት የሚያድን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ የተከተልኩት መንገድ እኔን ከተጠያቂነት የመንግሥት ገንዘብንም ከብክነት የሚያድን ነው አሉ እንጂ አሁንም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተቋሙ ብዙ ገንዘብ ተቀጥቷል፡፡ ይህ ያሰቡትን አሳክቶልዎታል ማለት ይቻላል?
አቶ አስፋው፦ እኔ አሁንም ቢሆን ጉዳዩ ህጉን ተከትሎ ያልመጣ በመሆኑ አላመንኩበትም፡፡ የህግ ሰዎቹ ደግሞ የሚያዩበት እይታ ይኖራቸዋል፡፡ ውሳኔውን በማሳለፍ ገንዘቡን እንድንከፍል ሆኗል። ያም ቢሆን ግን እኔ እስከመጨረሻው ድረስ ፍቃደኛ አልነበርኩም ግን የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ከዛ በላይ ማጓተት መስሪያ ቤቱን ለጉዳት የሚጥል በመሆኑ ከፍለናል።
አዲስ ዘመን፦ ገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ በፍርድ ቤት ውሳኔ ለተከፈለው ገንዘብ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂ በማድረግ እንደውም ገንዘቡን መክፈል ያለባችሁ እናንተ መሆናችሁን በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿልና ምን ይላሉ?
አቶ አስፋው፦ በጉዳዩ ላይም ገና እየተወያየን ነው፤ የመጨረሻ ውሳኔ ላይም አልደረስንም። የእኔ እምነት ሂደቱን በደንብ ማየት አለባቸው፤በዚህ ሂደት ውስጥ በትክክል ጥፋተኛ የሆነው አካል ደግሞ መጠየቅ አለበት የሚል ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህንን የማጥራት ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል። አሁን ለጊዜው ደብዳቤ ጽፏል፤እኛ ግን አልተቀበልነውም፤ እንደገና በህግ ባለሙያዎችም እንዲታይ እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አመሰግናለሁ
አቶ አስፋው፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011
እፀገነት አክሊሉ