
በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ላይ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል። አሁን ደግሞ የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ አቶ አልማው መንግስቴ። እኛም ተቋሙ በመሰረተ ልማት ዝርጋታው ላይ እያበረከተ ባለው አስተዋጽኦና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ አድርገንላቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ ማስተባበሪያ ኤጀንሲው መቼ ተቋቋመ? አላማውስ ምንድን ነበር?
አቶ አልማው፦ በአገሪቱ ውስጥ የሚሠሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የሚያስተባብራቸው ስለሌለ አንዱ የሚሠራውን ሌላው እያፈረሰ በመንግሥት ሀብት ላይ ከፍተኛ ብክነት ይፈጠራል:: የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችም በተለያዩ ምክንያቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳያልቁ ይሆናል፤ ተጠቃሚው ህብረተሰብም በወቅቱ አልቆለት መጠቀም ሲገባው እንዳይጠቀም መሆኑም የመልካም አስተዳደር ችግር አድርጎ ያነሳል። ይህንን መነሻ በማድረግ ኤጀንሲው እነዚህን በተበታተነ መንገድ የሚሠሩ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትን ወደ አንድ አምጥቶ ለማስተባበርና የጋራ እቅድ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተቋቋመ ነው።
ከዚህ አንጻርም ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት። አንደኛው የመሰረተ ልማት አቅራቢዎች ማስተር ፕላን ስለሌላቸው አንድ አገራዊ ማስተር ፕላን እንዲኖራቸው መሥራት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በተለያየ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ምክንያት ነዋሪዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ይነሳሉ፤ የእርሻ መሬታቸው ይወሰዳል፤ በእዚህ ጊዜ ደግሞ ተገቢውን ካሳ ማግኘት ሲኖርባቸው አይፈጸምላቸውም፡፡ በመሆኑም ኤጀንሲው የካሳ ቀመርና የነጠላ ዋጋ በማዘጋጀት ችግሩን ለመቅረፍ ይሠራል።
ኤጀንሲው በ2006 ዓ.ም በአዋጅ ቢቋቋምም ወደ ሥራ የገባው በ2009 ዓ.ም ነው፤ ለሦስት ዓመታት የዘገየበት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ብዙም መረጃው የለኝም።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በሙሉ አቅሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ተወጥቷል?
አቶ አልማው፦ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሠርቷል ማለት አይቻልም። መጀመሪያ የተመደቡት አመራር ሥራ ለቀቁ፤ ከዚያ በኋላ ተቋሙ ለብዙ ጊዜያት ያለ መሪ ቆይቷል፤ በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተቋሙ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ገብቷል ማለት አይቻልም። ለማንኛውም ግን የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ በሙሉ አቅሙ ሠርቶ ቢሆን ኖሮ ምን ነበር የሚጠበቅበት?
አቶ አልማው፦ ከተቋሙ ይጠበቅ የነበረው አንድ አገራዊ የቅንጅት ማስተርፕላን ተዘጋጅቶ ሁሉም መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት በዚህ መሰረት እንዲመሩ ማድረግ ነበር፤ እስከ አሁን ድረስ ይህንን ማድረግ አልተቻለም። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ተቋሙ ስሙ በራሱ እንደሚያመለክተው የመሰረተ ልማቶች ማስተናበሪያ ኤጀንሲ መሆኑ ነው፤ ነገር ግን ነባራዊ ሁኔታውን ስናይ ከባቡር በስተቀር ተቋማቱ የየራሳቸው ማስተር ፕላን የላቸውም። የመንገዶች ባለስልጣንን ማስተር ፕላን ብሎ ለመውሰድ ከባድ ቢሆንም መሰረቱ ግን አለው። ሌሎቹ ምንም ማስተር ፕላን የላቸውም። ስለዚህ የሌለን ነገር ከየት አምጥተን እናቀናጀው? አሁን እየተደራደርን ያለነው እነዚህ አካላት የራሳቸው የሆነ ማስተር ፕላን እንዲኖራቸው ነው። መብራት ኃይል የራሱን ማስተር ፕላን እየጀመረ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አገራዊ ማስተር ፕላን የለም:: ስለዚህ ተቋሙ ምንም ሥራ የለውም ማለት ነው?
አቶ አልማው፦ ማስተር ፕላን የለም ብለን ዝም ብለን አልተቀመጥንም። በ2011 በጀት ዓመት ተቋማቱን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የጋራ እቅድ እንዲያቅዱ አድርገናል። ከማስተር ፕላኑ በመለስም በዚህ አካሄድ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ችለዋል። ግን ማስተር ፕላኑ መዘጋጀት ነበረበት።
አዲስ ዘመን፦ ማስተር ፕላኑ ግን እንደዚህ መሰረታዊ ከሆነ ተቋማቱን ከማግባባት ባለፈ ኤጀንሲው ማስገደድ አይችልም?
አቶ አልማው፦ ኤጀንሲው በአዋጅ ነው የተቋቋመው፤ ማስፈጸሚያ ደንብ ያስፈልገዋል። ግን እስከ አሁን አዘጋጅተን የሰጠነው ደንብ ሊጸድቅ አልቻለም። ደንቡ ቢኖር ማስገደድ ይቻል ነበር። ነገር ግን ተቋማቱ ደንቡን በቀላሉ ሊያዘጋጁት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ማስተር ፕላኑ የተሟላ መረጃ ያስፈልገዋል፤ በየትኛውም ተቋም አሁን ላይ ያለው አመራርም ሆነ ባለሙያ የተሟላ መረጃ የለውም፡፡ ለምሳሌ ድሮ የቴሌ የመሬት ውስጥ መስመር የት እንዳለ የሚያሳውቅ መረጃ የለም፡፡ ሌሎቹም ተመሳሳይ ናቸው። በመሆኑም ሥራውን ለመሥራት የተደራጀ ጥናት ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነው ጊዜ የሰጠናቸው። ነገር ግን ደንቡ ከጸደቀ ወደ ማስገደዱ መግባታችን አይቀርም። እስከዚያው ድረስ ግን ኤጀንሲው ለማስተር ፕላኑ ሥራ መነሻ የሚሆን ፕሮጀክት በራሱ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፦ እየተዘጋጀ ያለው የጋራ እቅድስ ችግሮችን እየፈታ ነው ?
አቶ አልማው፦ አዋጃችን ከመሰረተ ልማት አቅራቢዎች ሥራቸውን ማከናወን ያለባቸው የመንገድ ማስተር ፕላንን ተከትለው መሆን እንዳለበት ያዛል። ከዚህ አንጻር የጋራ አቅዱ ሲዘጋጅ የመንገዶች ባለስልጣን በ2011 ዓ.ም የሚሠራቸውን ለይቶ ዝርዝራቸውን በመውሰድ መንገዶቹ በሚያልፉበት አካባቢ ቴሌ፣ መብራት … ምን አላቸው? የሚለው ጉዳይ ይለይና ሁሉም ያሏቸውን ንብረቶች በምን ያህል ጊዜ አንስተው ሊጨርሱ እንደሚችሉ በመገመት ነው እቅዱ የተዘጋጀው፡፡ በ2011 ዓ.ም ተሠርቶበትም የተሻለ ውጤት ተገኝቷል። ለቀጣዩ ዓመት ደግሞ ይህንን እቅድ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማቀድ ችግሮችን በተሻለ መልኩ ለመፍታት ይታሰባል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ግን አንድ የተቀናጀ አገራዊ ማስተር ፕላን መኖር ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የጋራ እቅዱ በ2011 ዓ.ም የተሻለ ውጤት እንዳመጣ ቢናገሩም ዛሬም ድረስ ቅንጅት የጎደለው ቁፋሮ እየተካሄደ እንዳለ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ አልማው፦ እናንተ አብዛኛውን ነገር የምታዩት አዲስ አበባ ላይ ነው፤ ሆኖም አዲስ አበባ ከእኛ ኃላፊነት ውጪ ነው፤ ምክንያቱም የራሱ ባለቤት ስላለው። የቴክኒክ ጉዳዩ በቢሮው የሚሰራው ነው፡፡እኛ ከአዲስ አበባ የመሰረተ ልማት ቅንጅት ቢሮ ጋር ግንኙነት አለን፡፡ ስለዚህ አለመግባባት እየተፈጠረ ያለው የሚቆፈሩ መንገዶች ወይም ሌላ የመሰረተ ልማት ችግር ሲታይ ‹‹ ኤጀንሲው የት አለ?›› ይባላል፡፡ ግን እኛ አያገባንም።
አዋጃችን ላይ ሲቀመጥም ተቋሙ የፌዴራል የተባለው በፌዴራል በጀት የሚሠሩ መሰረተ ልማቶችን መቆጣጠር ስለሆነ ነው። የአዲስ አበባ መሰረተ ልማት የሚሠራው በከተማዋ በጀት ነው።
በፌዴራል መንግሥት በጀት የሚሠሩ መሰረተ ልማቶች አብዛኞቹ ገጠር ላይ ነው ያሉት፡፡ እነሱን በተገቢው መንገድ እየተከታተልን ቅንጅታዊ ሥራው እንዲሳለጥም እየሠራን እንገኛለን። ለምሳሌ መንገድ እየተሠራ መብራት ኃይል ምሰሶውን ባለማንሳቱ መንገዱ ከሦስት ወራት በላይ የሚቆምበት አጋጣሚ ይፈጠራል፣ ይህንን ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት የእኛ ነው።
ሌላው በተለይም በመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ እያጋጠመ ያለው ችግር የተጋነነ ካሳ መጠየቅ ሲሆን ይህም ሥራው እንዲጓተት እያደረገ በመሆኑ ኤጀንሲው በአምስት ክልልች መድረኮችን በማዘጋጀትና ከአመራሮች ጋር በመነጋገር ህብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ችሏል።
በዚህም ብዙ በካሣ ክፍያ ምክንያት ቆመው የነበሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲጀመሩ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም አሁንም ህዝቡ ካለው የመሰረተ ልማት ፍላጎትና ተጀምረው ከዘገዩ ፕሮጀክቶች አንጻር ሲታይ ግን ኤጀንሲው በሚገባው ልክ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ብሎ መውሰድ አይቻልም።
አዲስ ዘመን፦ ኃላፊነቱን በሚፈለገው ደረጃ ላለመወጣቱ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?
አቶ አልማው፦ ዋናው ምክንያት ኤጀንሲው ተቆጣጣሪ ተቋም አለመሆኑ ሲሆን ይህም
እጅና እግራችንን አስሮ አስቀምጦናል፤ ሊቆጣጠርበትና ሊያስገድድበት የሚችልበት ምንም አግባብ የለውም፤ ለምሳሌ መንገድ እየተሠራ
መብራት ኃይል ምሰሶውን አላነሳም ቢል የምናስገድድበት አግባብ የለም። ሆኖም የመብራት ኃይልም ሆነ የእኛ ተቋም የመንግሥት የሥራ
ኃላፊዎች ስለሆንን
ቁጭ ብለን ተነጋግርን ችግሮቹን ለይተንና ተግባብተን ሥራዎች እንዲቀጥሉ ከማድረግ አንጻር ያለው ነገር የሚበረታታ ነው። ነገር ግን ማስገደጃ መንገድ ያለመኖርና የተቀናጀ ማስተር ፕላን አለመዘጋጀት ሥራውን ያልሠራን አካል ለመጠየቅ አስቸጋሪ አድርገውታል።
ሌላውና ትልቅ ችግር የሆነብን የካሣ ክፍያን በተመለከተ በተለይ ወረዳ ላይ ገማች ኮሚቴ ተብለው የሚቀመጡ አካላት መንገዶች ባለስልጣን የሚከፍለው ካሣ የመንግሥት ገንዘብ ስለማይመስላቸው የተጋነነ ክፍያን መጠየቅ ይስተዋላል፤ ይህንን ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ችግር ለመፍታት ደግሞ በአምስት ክልልች ላይ በመንቀሳቀስና የግንዛቤ መፍጠሪያ መንገዶችን በማመቻቸት ለውጦች እየመጡ ነው፤በቀጣይ ዓመትም የተጠናከረ ሥራ ይሠራበታል።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው የተሰጠውን ሥራ ለመሥራት የሚያበቃ አደረጃጀት አለው?
አቶ አልማው፦ ኤጀንሲው በአደረጃጀት በሀብትም ሆነ በስልጣን በዚህ መልኩ አልነበረም መደራጀት የነበረበት፡፡ ስኬታማ የሆነ የመሰረተ ልማት ሥራ ይሠራ ከተባለ ተቋሙ ከዚህ በላይ ከፍ ማለት ያስፈልገውም ነበር። አሁን ያለብን ችግር የመሰረተ ልማት ተቋማቱ ተጠሪነት ወጥ አለመሆን ሲሆን አንዳንዶች ለትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ሌሎቹ ደግሞ ለውሃና ኢነርጂ እንዲሁም እኛ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መሆኑ ነው።
ለምሳሌ እኛን የሚቆጣጠረን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የጋራ ሥራ አብረናቸው የምንሠራቸውን ተቋማት ስለማያገኛቸው በጋራ አይገመግምም፤ ይህ በከፍተኛ ሁኔታ በሥራው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
አዲስ ዘመን፦ ታዲያ እንዴት ቢደራጅ ይሻል ነበር?
አቶ አልማው፦ መደራጀት የነበረበት እነዚህን ተቋማት በአንድ ጠርንፎ በሚይዝ አንድ ትልቅ አካል ነበር። ሌላው እኔ ተቋሙን ያገኘሁት በሀብት፣ በሰው ኃይል የተዳከመ ሆኖ ነው። አሮጌ መኪና ከመንገዶች ባለስልጣን ተሰብስቦ ተሰጥቶት ነው ሥራ የሚሠራው፡፡ ሥራው የመስክ ቢሆንም መስክ ለመውጣት የሚያስችል ምንም ምቹ ሁኔታም የለም። በባለሙያ በኩልም ቢሆን እዚህ ቤት መምጣት የነበረበት በጣም ልምድ ያለው ከኮንትራክተሮች ጋር ተነጋግሮ ማሳመን የሚችል ቢሆንም ያለው አደረጃጀቱ ግን በዚህ ልክ የተጠና አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ የተቋሙ በዚህ ደረጃ ደካማ መሆን ሥራውን በምን ያህል መጠን ጎትቶታል?
አቶ አልማው፦ ለምሳሌ የመንገዶች ባለስልጣን የሚሠራቸው መንገዶች የዲዛይን ችግር ካለባቸው እንዲያስተካክል፣ ካሣ በወቅቱ እንዲከፍልና ሌሎች በሥራው ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን እንዲሞላ እናደርጋለን፤ግን ከመኪና ጀምሮ የተለያዩ የሥራ መሳሪያዎችን የምንወስደው ደግሞ ከእሱ ነው፤ስለዚህ የእነሱ ጥገኛ ነን ማለት ነው። በሌላ በኩል ተቋሙ ተቆጣጣሪ ተቋም አለመሆኑ ማስገደጃ ነገሮች እንዳይኖሩት ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ውጤታማ መሆን አልቻለም። ይህ ደግሞ ከመጀመሪያውም አደረጃጀቱ ላይ ከመበላሸቱም ባሻገር ለእኛ አገር በዓይነቱ አዲስ በመሆኑም ኤጀንሲው ከመቋቋሙ በፊት በደንብ መታሰብ ነበረበት።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ተቋሙ ከነችግሮቹ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ አልማው፦ ተቋሙ ገና ሦስት ዓመቱ ነው፣ በአቅም ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ሆኖም በይነ መረብን በመጠቀም የደቡብ ኮሪያና የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮዎች እንዲቀመሩ ተደርጓል፡፡ እነሱ እያንዳንዱን የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራቸውን የሚሠሩት በዓለም አቀፍ አማካሪዎች ያሠሩትን አገራዊ ማስተር ፕላን ይዘው ነው፡፡ እኛ ደግሞ ማስተር ፕላን እንኳን የለንም፡፡ ከዚህ አንጻር ራሳችንን ማወዳደር ከባድ ነው የሚሆነው፤እኛ ያለንበትን ስናየው ለማወዳደር እንኳን የሚከብድ ቦታ ላይ ነን።
በሌላ በኩልም መሰረተ ልማቶቻችን በጣም በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሆነውም አንዱ የሠራውን ሌላው የሚያፈርስበት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በወቅቱ የማይጠናቀቁበት፣ ከፍተኛ የሀብት ብክነት የሚስተዋልበት ነው። በአጠቃላይ እየተሠራ ያለውን ሥራ ገባ ብሎ ላየው በጣም እራስ ምታት ነው። ግን አንድ ቀን እነሱ የደረሱበት ደረጃ እንደርሳለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፦ እነሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከማሰብ በዘለለ ማን ምን ይሥራ?
አቶ አልማው፦ በእኛ በኩል በቀጣዩ ዓመት ከተሳካልን መሰረታዊ ለሆነው አገራዊ ማስተር ፕላን አንድ መሰረት እንጥላለን ብለን አስበናል። በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት አንድ አገራዊ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ይኖረናል የሚል ሃሳብ አለን። እዛ ላይ እስከሚደረስ ግን መንገድ ሲገነባ የእግረኛ መንገድ ምን ይምሰል? የመብራትና የስልክ እንዲሁም ሌሎች መስመሮች (ኬብሎች) እንዴት እንቀባበል? የሚሉና ሌሎች ነገሮችን ለመሥራት የሚያስችል የስታንዳርድ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነን።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ተቋም ባይኖር ኖሮ ምን ይከሰት ነበር ?
አቶ አልማው፦ ተቋሙ ባይኖር ኖሮ በርካታ የሚቆሙና የሚዘጉ ፕሮጀክቶች ይኖሩ ነበር። አሁን ያለው የህብረተሰቡ የመሰረተ ልማት ፍላጎትና ጥያቄ ከዚህ ቀደሙ በነበረው ልክ አይደለም፡፡ በመላው አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ አሳይቷል። በመሆኑም መንግሥት ይህንን ተረድቶ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እየለየ እየሠራ ነው። ልክ እንደ መንገድ ሁሉ መብራትና ቴሌም ግንባታ ይፈልጋሉ፡፡ ባለፈው ዓመት እንኳን በትክክል ከተከታተለናቸው 75 ፕሮጀክቶች መካከል የ69ኙ የቅንጅትና የካሣ ጥያቄዎች ምላሽ አግኘተዋል።
እስከ አሁን አቅቶን የቀረው በጣም ውስብስብ የሆነው የድሬዳዋ መልካ ጀብዱ ፕሮጀክት ብቻ ነው። ከዚህ አንጻር አሁን ላይ የትኞቹም የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ማንኛውም ችግር ሲገጥማቸው በቀጥታ ደብዳቤ የሚጽፉት ለእኛ ነው። በዚህም ተቋሙ በመኖሩ በርካታ ችግሮች ተፈትተዋል፤አሁንም የሚነሱ ችግሮችን በአግባቡና በልኩ እየፈታን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ይህንን ቢሉም በተለያየ ጊዜ ግን ‹‹ተቋሙ ሊፈርስ ነው … ሊበተን ነው›› የሚሉ መረጃዎች ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
አቶ አልማው፦ ሊፈርስ ነው ሊበተን ነው የሚለው መረጃ እኔ ጋር አልደረሰም። ሆኖም ባለፈው ዓመት በተፈጠረው የመንግሥት አዲስ አደረጃጀት ምክንያት መስሪያ ቤቶች ሲቀነሱና ኤጀንሲዎች ሲዋሃዱ ‹‹ከማን ጋር እንቀናጅ ይሆን?›› በሚል በሁሉም ተቋማት ሠራተኞች ላይ እንደሚፈጠረው ዓይነት ስጋት በእኛ ሠራተኞች ላይም ተፈጥሮ ነበር። ከዚህ ውጪ ግን ተቋሙ ሊፈርስም የሚችልበት ምክንያት የለም፤ መፍረስ የሚገባውም አይደለም። እንዲያውም መጠናከርና ከፍ ማለት አለበት። መንግሥት በመሰረተ ልማት ዙሪያ ያሉ የቅንጅት ችግሮችን በዘላቂነት የመፍታት እቅድ ካለው ተቋሙን ማጠናከርና አቅሙን ማሳደግ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፦ አገራዊ ለውጡ (ሪፎርም) በእናንተ ተቋም ላይ የፈጠረው እንደምታ ምን ይመስላል?
አቶ አልማው፦ አገራዊ ለውጡ እንደ ማንኛውም ተቋም በእኛም ላይም አዎንታዊ ተጽዕኖ አለው፤ በፊት ከነበረው አሠራር ወጣ ብለው ከሠራተኛውም ሞራል አንጻር ከአመራሩም የመምራት አቅምና ሞራል ጋር ስናየው አበረታች ነው። በዚህ መንገድ ኤጀንሲው ቀጥ ብሎ ቆሞ የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት መወጣት አለበት ብሎ ዕድል መስጠቱ በራሱ ለተቋሙ ትልቅ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ እነዚህን የመሰረተ ልማት ተቋማት አቀናጅቶ በመምራት የተረፈውና ወደፊት የሚድነው የአገር ሀብት እንዴት ይገለጻል?
አቶ አልማው፦ ይህን መግለጽ ከባድ ነው። ባለፈው ዓመት አንድ ጥናት ጀምረን አልጨረስነውም። እሱ አልቆ ቢሆን ኖሮ ይህን የምናወራውን ነገር ተጨባጭ ያደርገው ነበር፤ በቅንጅት እጦት ምክንያት ለሚከሰቱ የመሰረተ ልማት መጓተቶች ምን ያህል ገንዘብና ጊዜ መንግሥት ይከስራል የሚለውን ጉዳይ ለመለየት ወደፊት ጥናቶች ተጠንተው ተጨባጭ ውጤቶችን እናወጣለን ብለን እናስባለን።
ግን በየትኛውም ሁኔታ አንዱ የሠራውን ሌላው ካፈረሰው የገንዘብ ብክነት ይፈጥራል፤ ሁኔታውን ለማስተካከል ደግሞ ሌላ የጊዜ ብክነት ይከሰታልና እነዚህ ችግሮች እንዳይኖሩ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፤ አንዱ የሠራውን ሌላው እንዳያፈርስና ተናበው እንዲሠሩ ማድረግ ዋናው የኤጀንሲው ተግባር በመሆኑ በዚህ ልክ ይንቀሳቀሳል። በዚህ ደግሞ የሀብትና የጊዜ ብክነትን ማዳን ይቻላል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፦ እስከ አሁን ማዳን የተቻለውን የሀብትና የጊዜ በመጠን ማወቅ አይቻልም ማለት ነው?
አቶ አልማው፦ እሱን ማወቅ ከባድ ነው። የግድ ጥናት ያስፈልገዋል። ዝም ብሎ መናገር አይቻልም። እዚህ ላይ ግን ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስጠኗቸው ጥናቶች ቢኖሩም የቆዩ በመሆናቸው እንደ መረጃ መጠቀም ከባድ ነው። እኛ አሁን ያሰብነው እ.አ.አ ከ2014 ወዲህ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ ምን ያህል ሀብት ባክኗል የሚለውን ለማስጠናት ነው፤ ከተሳካልንም እስከሚቀጥለው ዓመት እናጠናቅቀዋለን።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ በአመራርነትዎ በአገሪቱ ያሉ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትን ቅንጅታዊ አሠራር እንዴት ያዩታል?
አቶ አልማው፦ በእኛ አገር ላይ ያለው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ቅንጅታዊ አሠራር በጣም ደካማ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ተቋማቱ አንድ የጋራ ማስተር ፕላን ስለሌላቸው ነው። ሁሉም ተቋማት የሚያስቡት ራሳቸው ያስቀመጡትን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስለማሳካት ነው፤በተረፈ ‹‹እኔ ስሠራ ሌላው ላይ ምን ችግር አደርሳለሁ? ሀብት ይባክናል? ንብረት ይወድማል? እንቅስቃሴ ይስተጓጎላል? …›› ለሚሉት ጉዳዮች ትኩረት አይሰጥም። የዚህ ተቋም ዋናው ዓላማም ይህንን ደካማ የቅንጅት አሠራር ወደተሻለ ማምጣት ነው። በተለይ በከተሞች አካባቢ ሰፊ የሆነ ችግር እየተስተዋለ ቢሆንም ለማስተካከል ግን ሁለት ዓይነት አደረጃጀት ነው ያለው፡፡ አንዳንዶቹ ላይ በፌዴራል በጀት የሚሠሩ ፕሮጀክቶች አሉ እነሱን እኛ እንከታተላቸዋለን፤ በክልል በጀት የሚሠሩትን ደግሞ አንከታተላቸውም፡፡ አሁን ከክልል መንግሥታት ጋር ተነጋግረን የፌዴራልና የክልል ፕሮጀክቶች እንዲናበቡ ማድረግ ነው ያለብን፤ ሆኖም እነዚህ ነገሮች እየተጋጩ ነው።
አዲስ አበባ ላይ የሚታየውም ሁኔታ ተመሳሳይ ከመሆኑም በላይ የከፋ የቅንጅት ችግር አለ። ይህንን እየተናበቡ መሥራት የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ ያለው የችግሩ መጠን ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ አልማው፦ አሁን አዲስ አበባ ከተማ የወሰደው ዕርምጃ ጥሩ ይመስለኛል። ባለፈው ዓመት ጉዳዩን የሚከታተል ባለስልጣን መስሪያ ቤት አቋቁሟል፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ተቋሙ ማስተባበር ሳይሆን የሚሠራው ቁጥጥር ነው። ተቋሙ ምናልባት አሁን ላይ በሰው ኃይልና በግብዓት አልተጠናከረም፤የልምድ ማነስም ስላለበት የቁጥጥር ሥራውን ለመጀመር ትንሽ ጊዜ ይወስድበት ይሆናል እንጂ አጀማመሩ በጣም ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በከተማዋ ያለው ችግር መጠነ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እስከሚደራጅና እስኪጠናከር በእናንተ በኩል የሚሠራ ሥራ የለም?
አቶ አልማው፦ አብረን ለመሥራት የጋራ እቅድ አቅደን ነበር፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስብስብ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በእኛ በኩልም ተለይተዋል፤ ለምሳሌ ሲኤምሲ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ አንድ እየተሠራ ያለ ድልድይ ሥራው ከተቋረጠ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፤በቃሊቲ አካባቢም ሥራው ለረጅም ጊዜ የቆየ ፕሮጀክት አለ፤ እነዚህንና መሰል ውስብስብ ችግር ያለባቸውን ፕሮጀክቶች ለይተን በመያዝና ባለሙያዎቻችንን በአራት ምድብ በመክፈል ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች ጋር አጣምረን እንዲሠሩ አድርገናል። በዚህ ሥራ ያን ያህል አመርቂ ውጤት መጥቷል ማለት ባይቻልም ጅምሩ ግን ጥሩ ነው። በሂደትም መስሪያ ቤቱ የቁጥጥር ኃላፊነት የተሰጠው ስለሆነ በመሰረተ ልማት በኩል ያለውን ችግር የማስተካከል ዕድሉ በጣም ሰፊ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የ 2012 ዓ.ም እቅዳችሁ ምንን ታሳቢ ያደረገ ነው?
አቶ አልምው፦ በበጀት ዓመቱ ሁለት ዓይነት እቅዶችን አዘጋጅተናል፤ አንደኛው የተቋሙ የራሱ ሲሆን ሌላው ደግሞ የእኛ ተቋም እያስተባበራቸው ካሉ ሰባቱ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀው ነው። ወደ ሥራ ለማስገባትም መጀመሪያ ከተቋማት ኃላፊዎች ጋር ቁጭ ብሎ መወያየት ያስፈልጋል። እቅዱ በጣም ጥሩና በትክክል ከተሠራበትም ችግሮችን የሚቀርፍ ስለሆነ በቀጣይም በደንብ ተግባብቶ ለመሥራት እንወያያለን።
ሌላው ተቋሙ የሚያስፈልገውን የማስፈጸሚያ ደንብ ለማጸደቅ የሚሠራ ሥራ ሲሆን አሁን ላይ ጨርሰን ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሰጥተናል፡፡ እነሱም ዓይተው ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ በመላክ አስተያየት እስኪሰጥበት እየጠበቁ ነው፤ ይህ ከተጠናቀቀ በኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላክ የማጸደቅ ሥራ ይሠራል።
በቀጣይ ዓመት በመላው ክልል የሚከናወኑ 84 ፕሮጀክቶችን ለይተናል፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ በየትኛውም መንገድ እንዳይቆሙና ፍጥነታቸውም እንዳይቀንስ የማድረግ ሥራ ለመሥራትም ዝግጅታችንን አጠናቅቀናል። በተለይ ደንቡ ከጸደቀ ውጤታማ ሥራ እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፦ አመሰግናለሁ
አቶ አልምው፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 22/2011
እፀገነት አክሊሉ