ነስር (የአፍንጫ መድማት)
ዶክተር አለ በሁሉም የጤና ዘርፎች ላይ በብቁ ባለሙያዎች ለጤናዎ የሚበጅዎትን በቤትዎ ሆነው በደቂቃ 6 ብር ብቻ ወጭ እያገለገልዎት ይገኛል፡፡
በአፍንጫ ደም መፍሰስ (ነስር) የምንለው አስደንጋጭ የሆነ፤ነገር ግን በአብዛኛው ለከፋ አደጋ የማይዳርግ የሕመም ዓይነት ነው፡፡
ነስር በሁለት ዓይነት ይከፈላል፣
1) ከፍተኛው የአፍንጫችን ክፍል የሚመጣ ነስር (Anterior Nosebleeds)
• ይህ ዓይነቱ የነስር ዓይነት ከ90 በመቶ በላይ ለሚከሰት የነስር ዓይነት ምክንያት ነው፡፡ ከፍተኛው የአፍንጫችን ክፍል የሚመጣን ነስር በቀላሉ መቆጣጠር ወይንም ማቆም ይቻላል፡፡
2) ከኋለኛው የአፍንጫችን ክፍል የሚመጣ ነስር (Posterior Nosebleeds)
• ይህ ዓይነቱ የነስር ዓይነት በአብዛኛው በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን ከሌላኛው የተለየ ሕክምና የሚያስፈልገው እና ውስብስብ ነው፡፡
ነስርን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
• የደም ግፊት መጨመር ጋር በተያያዘ የሚመጣ ነስር
• በአፍንጫ ላይ ከውጭ የሚከሰት አደጋ ወይንም አፍንጫ በመጎርጎር ምክንያት
• በተለያዩ የሕመም ወይንም መድኃኒቶች ምክንያት ደም መርጋት አለመቻል
ነስርን እንዴት ማቆም ይቻላል?
• ከጭንቅላትዎ ጎንበስ ማለት (ጭንቅላትን ወደ ላይ ቀና ማድረግ የሚፈሰውን ደም ወደ ጉሮሮ ከማምጣት ባለፈ ጥቅም የለውም)
• ቀጥ ብለው መቀመጥ
• ሁለቱም የአፍንጫ ቀዳዳዎች በአውራ ጣትዎ እና በጠቋሚ ጣት ግጥም አድርጎ ለአስር ደቂቃ ይዞ ማቆየት
• በአፍ የሚመጣን ደም መትፋት
• ነስሩ ካቆመ በኋላ አፍንጫዎን አለመነካካት ናቸው፡፡
ነስር ከተከሰተ በኋላ ወደ ሐኪም መሄድ የሚያስፈልገው መቼ ነው?
• አፍንጫዎን ለ10 ደቂቃ ያህል ይዘው ቆይተው ነስሩ የሚያቆም ካልሆነ
• በአጭር ጊዜ ልዩነት በተደጋጋሚ የሚነስርዎ ከሆነ
• ራስ ማዞር ወይንም ራስዎን የሚስቱ ከመሰለዎት
• የልብ ምትዎ የሚጨምር ከሆነ እና ለመተንፈስ ከተቸገሩ
• ደም የሚያስመልስዎ ከሆነ
• በሰውነትዎ ላይ ሽፍታ ከኖረ
• ትኩሳት ካለዎት
• ከነስር ሌላ ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች መድማት የሚኖር ከሆነ
• በቀላሉ የመበለዝ ምልክቶች በሰውነትዎ ላይ ከተገኙ
• ደምን ለማቅጠን የሚጠቅሙ መድኃኒቶችን የሚወሰዱ ከሆነ
• የደም መርጋትን የሚያስተጓጉሉ ማንኛውንም ዓይነት ሕመም ካለዎት
• የኬሞቴራፒ ሕክምና በቅርቡ ወስደው ከነበረ
ነስርን እንዴት መከላከል ይቻላል?
• በአብዛኛው ነስር የሚከሰተው በቀዘቀዘ እና በደረቅ የአየር ንብረት ጊዜ ነው፡ ፡ ለነስር ተጋላጭ የሆኑ ከሆነ አፍንጫዎ እንዳይደርቅ ቫዝሊን (Petroleum jelly) በመጠቀም ማለስለስ ይችላል ::
• አፍንጫዎን በጣትዎ አለመነካካት
• የነስርዎ መንስዔ ከሌላ የጤና ችግር ጋር ተያያዥነት ካለው ሐኪምዎን ማማከር የሚሰጥዎን የጤና ምክር መተግበር
• ሲጋራ ማጨስ አፍንጫን በማድረቅ ለነስር ስለሚዳርግ ማስወገድ ናቸው፡፡
ምንጭ፡- ዶክተር አለ 8809 የፌስቡክ ገፅ:
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011