1. የእከክ በሽታ ምንድን ነው?
የእከክ በሽታ የላይኛውን የቆዳ ክፍል ሰርስረው በመግባት እዚያው እንቁላላቸውን እየጣሉ በሚራቡ በአይን የማይታዩ እከክ አምጪ ተባዮች አማካይነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡
2. የእከክ በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው ?
እጅግ የተለመዱት የእከክ በሽታ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው ፡፡
• ማሳከክ በተለይ በመኝታ ወቅት
• ነጠብጣብ መሰል የቆዳ ላይ ሽፍታዎች
• መግል የያዙ እብጠቶች እና የቆሰሉ የሰውነት ክፍሎች ናቸው ፡፡
አዛውንቶች እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆነ ሰዎች እከክ ቢይዛቸውም ላያሳክካቸው ይችላል፡፡
ሽፍታውና ማሳከኩ በማንኛውም የቆዳ ክፍል ሊከሰት ቢችልም በተለይ ግን በእጅ፣በጣቶች መካከል፣በጥፍሮች ዙሪያ፣ የሰዓት ማሰሪያ አካባቢ፣ የክርን መታጠፊያ፣ በጡት፣ በብብት፣ በወገብ ዙሪያ እና በብልት አካባቢ ሽፍታው የሚከሰትባቸው ዋነኞቹ የሰውነት ክፍሎች ናቸው ፡፡
የእከክ በሽታ በጊዜ ካልታከመ የቆዳ መቁሰልና ውስብስብ የሰውነት ውስጥ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሰውነት ላይ የተከሰተ ማንኛውም አይነት የቆዳ ችግር በጤና ባለሙያ ሊታይ ይገባል፡፡
3. የእከክ በሽታ መተላለፊያ መንገዶች ምንድን ናቸው?
የእከክ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በሚደረግ ቀጥተኛና ረዘም ላለ ጊዜ በሚቆይ የሰውነት ንክኪ አማካይነት ነው፡ ፡ በተጨማሪም የእከክ በሽታ የያዘውን ሰው ልብስ፣ ፎጣ፣ አልጋና የመሳሰሉትን ነገሮች በመጋራት ይተላለፋል
4. የእከክ በሽታ ህክምና ምንድን ነው?
የእከክ በሽታ መድኃኒት አለው፡፡ በሽታው ሰውነት በሚቀባ ወይም በአፍ በሚዋጥ መድኃኒት ማከም ይቻላል፡፡ በመሆኑም በአቅራቢያዎ ወደ ሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ የጤና ባለሙያን ያማክሩ፡፡
በባለሙያ የታዘዘው መድኃኒት ሰውነት የሚቀባ ከሆነ እንደሚከተለው ይቀቡ፣
ከአንገት እስከ እግር ጣት ድረስ በሁሉም የሰውነት ክፍል ላይ ቀብቶ በደንብ ማሸት፣
በተለይ የቆዳ መታጠፊያዎችን ልዩ ትኩረት በማድረግ መቀባት፣
ቅባቱ አይኖችን እንዳይነካ መጠንቀቅ፣
መድኃኒቱ እስከ 24 ሰዓት ድረስ ሰውነት ላይ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ መታጠብና ንፁህ ልብስ መልበስ፣
በባለሙያ የታዘዘው መድኃኒት የሚዋጥ ከሆነ ደግሞ፣
በጤና ባለሙያ የታዘዘለት ሰው ብቻ በአግባቡ እንዲወሰድ ማድረግ፣
በጤና ባለሙያ በታዘዘው መጠን ብቻ
መዋጥ፣
በጤና ባለሙያ በታዘዘው ቀናት ብዛት ብቻ መዋጥ፣
ለሌላ ሰው መስጠት ወይም ማካፈል አይቻልም፡፡
ሕክምና በሚወስድበት ወቅት የሚከተሉትን ያከናውኑ
በቂ ውሃ ባለበት አካባቢ ከሆነ
የተለበሱትን ልብሶች በሙሉ በፈላ ውሃና በሳሙና አጥቦ ፀሐይ ላይ ማስጣት፣
ጋቢ፣ነጠላ፣ አንሶላዎች፣ ብርድ ልብሶችን እና የሌሊት ልብሶችን በሙሉ በፈላ ውሃና ሳሙና አጥቦ ለ3 ቀናት ፀሐይ ላይ ማስጣት ያስፈልጋል፡፡
የውሃ እጥረት ባለበት አካባቢ ከሆነ
መድኃኒት ከመቀባትዎ ወይም ከመዋጥዎ በፊት የተለበሱት ልብሶች እንደገና ከመለበሳቸው በፊት እስከ 3 ቀን ድረስ ፀሐይ ላይ ማቆየት፣
ጋቢ፣ነጠላ፣አንሶላዎች ብርድ ልብሶች እና የሌሊት ልብሶች በሙሉ እንደገና ከመለበሳቸው በፊት እስከ 3 ቀን፣ ድረስ ፀሐይ ላይ ማቆየት ያስፈልጋል፣ ወይም ልብሶቹን ከ 3 ቀን ባላነሰ ጊዜ በፌስታል ቋጥሮ ለብቻ ማስቀመጥ፡፡
5. የእከክ በሽታ መከላከያ ዘዴዎች ምንድን ናቸው ?
የእከክ በሽታ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ለመከላከል የሚከተሉትን ዘዴዎች ይከተሉ። በሽታው ከያዘው ሰው ጋር ንክኪ አለማድረግ፣ ንክኪ ማድረጉ የግድ ከሆነ ንክኪ ከማድግ በፊትና በኋላ በቂ ውሃ፣ ካለ እጂን በውሃና በሳሙና መታጠብ፣ እንዲሁም በማከክ ቁስሉ እንዳይባባስ ጥፍሮችን አሳጥሮ መቁረጥ
በቂ ውሃ ካለ የግል ንፅህናን በሚገባ መጠበቅ ማለትም ሰውነትንና ፀጉርን መታጠብ እንዲሁም ልብስን በየጊዜው ማጠብ፣ እከክ ከያዘው ሰው ጋር የተራዘመ የሰውነት ንክኪ ያደረጉ ሰዎች ምልክቱ ባይታይባቸውም መታከም አለባቸው፣
በእከክ ዳግም መያዝን ለመከላከል ሁሉም ንክኪ ያላቸው ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ መታከም አለባቸው፣
ህክምና በተደረገ ከ2-4 ሳምንት በኋላ የማሳከክ ችግር ከቀጠለ ቶሎ በአቅራቢያዎ ወደ ሚገኘው የህክምና ተቋም በመሄድ የጤና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል፡፡
ምንጭ፡- የአማራ ጤና ጥበቃ ቢሮ የፌስቡክ ገጽ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011