በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ፈረንሳይ አቦ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በህዝባዊ ሠራዊት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ ከተኮለኮሉት መካከል ወይዘሮ አልማዝ ወርቁ አንዷናቸው። የአራት ዓመት ልጃቸውን ይዘው ለማስመዝገብ መገኘታቸውን ሲገልፁ፤ በግቢው የነበሩ አንድ ጎልማሳ “ቦታ የለም፤ ልጆቹን መዝግበን የት እናድርሳቸው?” የሚል ጥያቄ አዘል ምላሽ ተሰጣቸው።
“እባካችሁ ነፍሰጡር ነኝ። ልጄን ማስተማር የሚመቸኝ እዚህ ብቻ ነው። ከሌላ ቦታ ማመላለስ አልችልም።” ወይዘሮ አልማዝ ልመና ጀመሩ። “ለምን መካነ ህይወት አታስገቢያትም?” የሚል ጥያቄ አቀረቡ መላሹ ሰው ፤ “ ግቢ ውስጥ ያሉት ልጆች የሚማሩት እዚሁ ነው። ተባበሩኝ” ሰውየው አቀርቅረው ”ሁሉም የራሱ ምክንያት አለው። እኛ ግራ ተጋብተናል። ርዕሰ መምህሩ መልስ ይሰጥሻል።” አሉ። ወይዘሮዋ ጠረቆ ከሚባል መንደር መምጣታቸውን ከህዝባዊ ሠራዊት የቀረበ የመንግሥት ትምህርት ቤት እንደሌለ እና ምንም አማራጭ እንደማይኖራቸው ገለፁ።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብረሃም አጥናፉ ሲመጡ ወላጆች ወረሯቸው። “እኛ አንመዘግብም ማለት አንችልም። በአንድ ክፍል ምጣኔው 40 ተማሪ መሆን አለበት ቢባልም በእያንዳንዱ ክፍል ከ80 ተማሪ ያላነሰ ተመዝግቧል፡፡ በትምህርት ቤቱ ያለው የተማሪዎች ክፍል፤ የተማሪዎች ሽንት ቤት፤ የመመገቢያ ቦታም ሆነ ውሃ የመጠጫና የመታጠቢያ ቧንቧ፤ ሁሉም መጠቀሚያዎች ሊያስተናግዱ ከሚችሉት በላይ ተማሪ መዝግበናል፡፡ በተለይ በአፀደ ህፃናቱ አንድ ልጅ ጉንፋን፤ ቶንሲልም ሆነ ኩፍኝ ከያዘው ሁሉም ይታመማሉ፡፡ የአራት ዓመት ጀማሪ ተማሪዎች ተጨናንቀው ሊሰቃዩ እንደሚችሉ እስኪ ገምቱ፤” አሉ፡፡ በሁሉም ወላጆች ዘንድ የመከፋት ምልክት ታየ፡፡
እንደርዕሰ መምህሩ ገለፃ፤ ለጀማሪዎች የማሸለቢያ ክፍል አንድ ብቻ በመሆኑ የሚያርፉት በተራ ነው፡፡ የመዋዕለ ህፃናት ደረጃ 2 እና 3 ተማሪዎች የሚያርፉት በዚያው ክፍል ውስጥ በመቀመጫቸው ላይ ነው፡፡ የሚመገቡት እዚያው በሚማሩበት ወንበር ላይ ነው፡፡ ከፍ ሲል ላይብረሪው ማስተናገድ የሚችለው 90 ተማሪዎችን ብቻ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ ያለው የተማሪ ቁጥር ግን ሁለት ሺህ 68 ደርሷል፡፡ በቢሮ ውስጥ ሠራተኞች የሚሰሩት ተደራርበው ነው፡፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የእንግሊዘኛ መጽሐፍ እጥረት አለ፡፡ ሁለት ላብራቶሪ ቢያስፈልግም ያለው አንድ ላብራቶሪ ብቻ ነው፡፡ ካፍቴሪያው እና የተማሪዎች መመገቢያ የቆርቆሮ አዳራሹ ፈርሶ ባለአራት ፎቅ ህንፃ እንዲገነባ ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚያስፈፅም ጠፍቷል፡፡
ጊዜያዊ የወላጆችን ጫጫታ ለመቀነስ ሲባል ብቻ የመጣውን መዝግቡ ከማለት ውጪ ምንም አይነት መፍትሄ እየተሰጠ አይደለም፡፡ ወደፊት ትምህርት ቤቱ ሥራ ሲጀምር ዞሮ የሚያየውና ያለበትን ችግር የሚረዳለት አይኖርም፡፡ አሁን ግን ከአቅሙ በላይ እንዲመዘግብ እየተገደደ ነው፡፡ በየዓመቱ በየደረጃው የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም ትልቁ ችግር መዝግቡ ከማለት በዘለለ ክፍል እየተገነባ አለመሆኑ ነው ይላሉ፡፡
አራት ኪሎ እና ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በተገላቢጦሽ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተመዝጋቢ ተማሪዎች መጥፋታቸው እየተገለፀ ነው፡፡ በርግጥ ነዋሪዎች በመልሶ ማልማት የተነሱ ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹ የተሻለ አፈፃፀም ቢኖራቸውም፤ በግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ የተማረረው ወላጅ የትራንስፖርት ወጪውን ችሎ በመንግሥት ትምህርት ቤቶቹ ያስተምር ነበር፡፡ አንድም ችግሩን የፈጠረው ትምህርት ቤቶች ተመጣጣኝ አቅም ስለሌላቸው በውስን ትምህርት ቤቶች ላይ ጫና እየተፈጠረ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡
ሌላዋ ከግል ትምህርት ቤት ልጃቸውን አስወጥተው በህዝባዊ ሰራዊት ለማስመዝገብ የተገኙት ወይዘሮ ፍቅርተ ተሾመም የርዕሰ መምህሩን ሃሳብ ይጋራሉ፡ ፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በፊት የሚያስተምሩት በግል ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ክፍያው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ አራት ኪሎ አካባቢ በመንግሥት ትምህርት ቤት ልጃቸውን አስገቡ፡፡ ሆኖም ልጃቸው ቀደም ሲል የምታውቀውን በሙሉ ረሳች፡፡ ትምህርት ቤቱ በርዳታ ድርጅት ስለተገነባ ግቢው እና የመማሪያ ክፍሎቹ ማራኪ ቢሆኑም ትምህርት አሰጣጣቸው ላይ ችግር አለ፡፡ በዚህ ሳቢያ መልቀቂያ ጠይቀው ወደ ህዝባዊ ሰራዊት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመምጣት ተገድደዋል፡፡ ሆኖም የተመዝጋቢው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ወረዳው መዝግቦ ዕጣ አውጥቶ ይመዝገቡ ካላቸው ውስጥ የእርሳቸው ልጅ አልተካተተችም፡፡ በዚህ ሳቢያ መቸገራቸውን ይገልፃሉ፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ምክትል ሥራ አስፈፃሚ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ደበበ ጉልማ እንደሚናገሩት፤ በርግጥ ህዝባዊ ሰራዊት በየካ ክፍለከተማ ካሉ 14 ወረዳዎች ከ37 ትምህርት ቤት ውስጥ በአፈፃፀሙ አንደኛ የወጣ ትምህርት ቤት ነው፡ ፡ የሠራተኞቹ ትጋት በጣም ጥሩ ነው፡፡ በተጨማሪ በቅርብ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ከአንቆርጫ፤ ከአካኮ፤ ከወይራ ሰፈር እና ከሌሎች ወረዳዎች ከወረዳ 1 እና ከወረዳ 10 የሚመጣው ሰው ቁጥር ቀላል አይደለም፡ ፡ በአፈፃፀሙ እና መንገድ ዳር በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን በዚህ ትምህርት ቤት ማስመዝገብ በመፈለጋቸው ከትምህርት ቤቱ አቅም በላይ ተማሪዎች ለመመዝገብ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር መብት ስላላቸው ዕጣ በማውጣት ወረዳው የተወሰኑትን ትምህርት ቤቱ እንዲመዘግብ ወስኖ አስተላልፏል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ችግር ያለባቸው እና በልዩ ሁኔታ መታየት ያለባቸውንም ለማስተናገድ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተረፈ ሰፋ ያለ ቦታ ወዳለበት መካነ ህይወት ትምህርት ቤት እንዲመዘገቡ ተነግሯቸዋል፡፡ ሆኖም ወላጆች ፈቃደኛ አይደሉም፡፡
መካነ ህይወት ትምህርት ቤት በፊት በነበረው ሥዕሉ በደንብ አያስተምርም እያሉ ብዙዎቹ ልጆቻቸውን እዚያ ማስተማር አይፈልጉም፡፡ ሆኖም አሁን ተሻሽሏል፡፡ መንግሥትም በደንብ እየሰራለት ሲሆን፤ ሜድሮክም 40 ክፍሎችን እየገነባለት ነው፡ ፡ ነገር ግን፤ በመካነ ህይወትም ከፍተኛ የተማሪ ቁጥር በመጨመሩ ወደ ጉራራ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ ተጨማሪ ትምህርት ቤት እንዲገነባ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ከቃል ያለፈ ምላሽ አልተሰጠም ይላሉ፡፡ በህዝባዊ ሠራዊት ቅጥር ግቢ ራሱ የቆርቆሮ ግንባታዎችን አፍርሶ ፎቅ መስራት ቢቻል የተሻለ ቁጥር ያለው ተማሪ መቀበል ይቻል ነበር፤ ያም ሊሆን አልተቻለም ብለዋል፡፡
የመካነ ህይወት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህሩ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ በበኩላቸው፤ በእነርሱም ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛን ጨምሮ አንድ ሺ ሶስት መቶ ተማሪ መመዝገቡን ይናገራሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ አጥር እንኳን የሌለው ሆኖ ወልዶ መጣያ እየተባለ ስሙ ቢጠፋም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተሻለ እንዲሆን ጥረት አድርገው ፊደል ለይተው ማንበብ ሳይችሉ የሚያልፉ ልጆች እንዳይኖሩ፤ የግቢው ሁኔታ እንዲስተካከል ጥረት በማድረግ እና ከግል ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በቆርቆሮ ክፍል ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በምቹ ሁኔታ እንዲማሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራን፤ የትምህርት አመራርና ባለሙያዎች ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ሻንቆ በበኩላቸው፤ 488 ትምህርት ቤቶች ለተማሪ ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ የዕድሳትና የጥገና እንዲሁም የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ከ350 በላይ በሚሆኑ ፕሮጀክቶች በኮንዶሚኒየሞችና በሌሎችም አካባቢዎች አዳዲስ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ወደ ኋላ አይልም፡፡
በተጨማሪም፤ የግል ትምህርት ቤት ያሉትን ግብአቶች በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በማስገባት ህብረተሰቡ አማራጭ እንዲያገኝ በሚል ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ለውጥ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ ወላጆች ፊታቸውን ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት አዙረዋል፡፡ ሁሉም ህብረተሰብ ልጆቹን ትምህርት ቤት የማስመዝገብ መብት አለው፡፡ ዜጎች አትማሩም ተብለው አይከለከሉም ፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ዋጋ በመጨመራቸው ይህንን መቋቋም ያቃተው ወላጅ ልጆቹን የመንግሥት ትምህርት ቤት እያስገባ ነው ይላሉ፡፡
አያይዘውም፤ በአፈፃፀም ላይ ከተቀመጠው አቅጣጫ ውጪ የሚሰራ ሥራ መኖሩን በመጠቆሙ፤ የዕርምት እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ተሰጥቷል። በክፍል ጥበት ሳቢያ ህፃናት ቤት ቁጭ ማለት ስለሌለባቸው ትምህርት ቤቶች በግዴታ መመዝገብ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል ብለዋል፡፡
በመጀመሪያ የህብረተሰቡን የመማር ፍላጎት መመለስ፤ በቀጣይ ደግሞ ችግሩን ማቃለል ይገባል። ተማሪ ከተመዘገበ በኋላ ችግሩን ማቃለል ይቻላል። የመማር ማስተማሩን ሂደት በማያስተጓጉል መልኩ ይገነባል፡፡ ከዚህ ውጪ ጥራት ላይ ለሚጠቀሰው ጉዳይም ወላጆች የተሻለውን ትምህርት ቤት መርጠው መሄዳቸው ጥሩ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ለውጥ ማምጣት ባይቻልም፡፡ በቀጣይ በሂደት ሌሎችም ትምህርት ቤቶች ተቀራራቢ የትምህርት ጥራት አቅም እንዲኖራቸው ይሰራልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 17/2011
ምህረት ሞገስ