ዶክተር ኮንቴ ሙሳ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር
የተወለዱት በ1958 ዓ.ም በአፋር ክልል በምትገኝ ዱለቻ በተባለች ወረዳ በአሁን አጠራሯ ዞን ሦስት ውስጥ ነው፡፡ የወጣትነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በደርግ ዘመነ መንግሥት ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አዋሽ 7 ተምረው ሲያጠናቅቁ ወደ ድሬዳዋ በማቅናት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቀጥለዋል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉባት ድሬዳዋ ከተማንም የቋንቋ ገበያዬ ይሏታል::
ለዚህ አባባላቸው ምክንያቱ ደግሞ ሶማልኛ፣ አደሪኛ፣ አፋርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ አረቢኛና ፈረንሳይኛን ቅልጥፍ አድርገው መናገር መቻላቸው ነው:: ይህ ሁኔታ ደግሞ የተፈጠረው በሮተርዳምና አልያንስ ፍራንሴ በተባሉና ድሬዳዋ ባሉ ትምህርት ቤቶች ነው:: ለከፍተኛ ትምህርት የሄዱባት ስዊድን ደግሞ ስዊድንኛን የመናገር ዕድል ፈጥራላቸዋለች፡፡
የከፍተኛ ትምህርታቸውን በተመለከተም የመጀመሪያ ዲግሪያቸው በጤና ሳይንስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማህበረሰብ ጤና ሳይንስ፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸው ደግሞ በሽታዎችን የመከላከል ትምህርትን የተማሩ ሲሆን ሁሉንም ያጠናቀቁት ደግሞ ስዊድን አገር ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የታተሙ የጥናት ውጤቶች ላይም የተለያዩ ጽሑፎችን አሳትመዋል፤ ለስዊድን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፤ በደቡብ ሱዳን ላይ የዓለም ባንክ የጤና ኤክስፐርት በመሆን የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ገንብተዋል:: ኡጋንዳ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሕንድ፣ ሮተርዳም፣ ሆላንድ ደግሞ በመምህርነት ያገለገሉባቸው አገራት ናቸው:: ይህ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ልምድን እንዲቀምሩ እንዳገዛቸውም ነው የሚናገሩት:: የዛሬው የዕለተ ረቡዕ አዲስ ዘመን እንግዳችን የአፋር ሕዝብ ፓርቲም ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ናቸው፡፡
ባልደረባችን ፍቃዱ ሞላ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በድሬዳዋ ከተማ ባዘጋጀው አዲስ ወግ መርሃ ግብር ላይ አግኝቷቸው ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ከኢትዮጵያ መቼና በምን ምክንያት ወጡ?
ዶክተር ኮንቴ፦ ከአገር የወጣሁት በ1979 ዓ.ም ብሔራዊ ውትድርናን በመሸሽ ነው:: በወቅቱ እኛ በመጽሐፍ ክለባችን አማካይነት የኤርትራን ጥያቄ በጣም እንከታተል ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ፌዴሬሽኑ እንዴት እንደፈረሰ፣ ደርግም የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም የሚል ግንዛቤ ይዘን ነበር:: በሌላ በኩልም በወቅቱ ይደረግ የነበረው ጦርነት ትርጉም አልባና የትም የማያደርስ ነው የሚል አቋም ስለነበረን ጦርነቱን የመቃወም ሥራ ነበር የምንሰራው:: ከዚህ ውጪ ግን አንተ አፋር ነህ ወይም ሌላ እንዲሁም እንደ አሁኑ ዘመን «የማን ጎሳ ነህ» ተብሎ ጥያቄ አናውቅም ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፦ በእኛ ዘመን የማን ጎሳ ነህ ብሎ ጥያቄ አልነበረም ብለዋልና ያን ጊዜ ጥያቄው ለምን አልነበረም? አሁን ደግሞ ለምን ተስፋፋ?
ዶክተር ኮንቴ፦ ሂደቱ ይመስለኛል፡፡ ያን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ችግር የብሔር ሳይሆን የፖለቲካ አስተሳሰብ ነበር:: ከዚያ በኋላ የተለያዩ የነፃነት ግንባሮችም ነበሩ፡፡ ግን የእነሱ ሃሳብ በጦር ሜዳ እንጂ በከተማ ነዋሪው ላይ የሰረጸ አልነበረም፤ ለዚህም ይመስለኛል በወቅቱ የጎሳ ጉዳይ ያን ያህል አሳሳቢ ያልነበረው፡፡ በነገራችን ላይ ድሬዳዋ ላይ ስለ ጎሳ የሚያነሳ ሰው «ፋራ» ነበር የሚባለው::
አሁን ግን ሁሉም በጎሳው ተደራጅቶና አገራዊው ጉዳይ ተደብቆ የብሔር ጥያቄ የጎላበት ሆኗል፤ በዚህ አካሄድ ያደገው ወጣት ቁጥር ደግሞ ቀላል የሚባል አይደለም:: በክልል ስር ያደገና በአንድ ቋንቋ ታጥሮ የቀረ ወጣት በጣም ያሳዝናል:: በሌላው ክልል የእኔን ቋንቋ ካልተናገርክ መውጣት አለብህ የሚል አለ፡፡ እነዛ ደግሞ ተሰዳጆቹ ቋንቋውን መማርን እንደ ኢንቨስትመንት ስላላዩት ይሄዳሉ:: እንደዚህ ዓይነት ንትርክ ውስጥ መግባታችን ደግሞ በጣም ያሳዝናል::
አዲስ ዘመን፦ ድሬዳዋ የመቻቻልና የፍቅር ከተማ መሆኗ አብቅቶላታል የሚሉ አሉና በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር ኮንቴ፦ አልስማማም:: ምክንያቱም ጥሩ መሠረት አለ፤ በሌላ በኩልም አብዛኛው ሰው ይህንን ሃሳብ ይቀበላል የሚል ግምት የለኝም:: አንዳንዴ እነዚህን ነገሮች ወጣ ብሎ የመጋፈጥ ወኔ ላይኖር ይችላል:: ግን አሁን እየነፈሰ ያለው የተስፋ ንፋስ ላይ ድሬ የማታገግምበት ምክንያት የለም:: ይህንን ስል ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት አብሮ የመኖር ብቻ ሳይሆን የመዋለድም ነው በዚህ ምክንያት ደግሞ ለተቀረው የአገሪቱ ክፍል ማሳያ ልትሆን የምትችልም ናት ብዬ አስባለሁ::
ድሬዳዋ ተለወጠች ከተባለም ሰው አይደለም የተለወጠው፡፡ በአወቃቀሩና በአስተዳደሩ የፍትህ መጓደል እንጂ ሕዝቡ ጸባዩን አልቀየረም::
አዲስ ዘመን፦ የሃሳብ እንጂ የብሔር ጉዳይ ቀደም ባለው ጊዜ አይታወቅም ነበር ብለዋልና ግን በዚያን ወቅትም ቢሆን በብሔር ተደራጅተው የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ነበሩ፤ ከዚህ አንጻር የብሔር ጥያቄ አልነበረም ማለት ይቻላል?
ዶክተር ኮንቴ ፦ ያኔ እንግዲህ የብሔር ጥያቄ ጫካ ውስጥ ነበር:: እኛ እንደ ከተሜዎቹ ይህንን ሁኔታ የሚያራምድ የሚያሳውቀን አልነበረንም::
አዲስ ዘመን፦ እንደ ድሬዳዋ ሳይሆን እንደ አገር ነው የጠየቅሆት፤
ዶክተር ኮንቴ፦ በወቅቱ ያን ያህል ጠለቅ ያለ ግንዛቤ አልነበረኝም:: ይህም ቢሆን ግን የብሔር ጥያቄ እንደ ፖለቲካ መፍትሔ ይሆናል ብሎ ሃሳቡን የሚገልጽ ወይም የሚያሰርጽ ሰው አላጋጠመኝም::
አዲስ ዘመን፦ አርብቶ አደሩ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ላይ ውክልናን አግኝቷል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ኮንቴ፦ አይመስለኝም:: በጠረፍና በመካከል ያለው የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል የጎዳው አርብቶ አደሩን ነው:: ብዙ ጊዜ የምናወራው ስለግብርናውና አርሶ አደሩ ፕሮጀክቶች ነው፡፡ የአገሪቱ የሀብት ወይም ዓመታዊ እድገትም ሲለካም የሚቀርበው በዚያ ማሳያነት ነው::
ለምሳሌ አርብቶ አደሩ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው? ይህንን የሚያሳይ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እኛ ልጅ ሆነን ጠዋት ሬዲዮ ላይ ስለ ቡና፣ስለ ቆዳና ሌጦ ይወራ ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህንን እንኳን ያካተተ ነገር ያለ አይመስለኝም::
አሁን በመጣው ለውጥ መሠረት ለአርብቶ አደሩ ለኑሯቸው ተመጣጣኝ የሆነ የመሠረተ ልማት ከመዘርጋት ይልቅ እነሱን ወደ ከተማ ለማስፈርና ከተሜ ለማድረግ በመንደር የማሰባሰብ ሥራ ነው የሚሰራው:: እዚህ ላይ አፋር አካባቢ ያለውን ብንመለከት ለመንደር ማሰባሰቢያነት የተገነቡት አካባቢዎች ለም መሬታቸው ለከሰምና ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካነት መጠቀም ስለተፈለገ አማራጩ እነዚህን ሰዎች ከአካባቢያቸው አንስቶ ወደ ሌላ ማዞር ስለሆነ ነው በመንደር እንዲሰባሰቡ የተደረገው::
በሌላው ጎን ደግሞ እነዚህ ሰዎች በመንደር ማሰባሰብ የሚሰፍሩባቸው አካባቢዎች ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት በቅጡ ያልተሟላላቸው፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮቸም የሌሏቸው ከመሆኑም በላይ በርካታ ገንዘብ የተበዘበዘባቸው ናቸው:: በዚህ ምክንያት ደግሞ አርብቶ አደሩ የሚፈልገው ወይም የሚያስፈልገው ነገር ተሟልቶለት እየኖረ አይደለም::
አዲስ ዘመን፦ ችግሩ ግን አፈጻጸሙ ላይ ነው ወይንስ ሌላ?
ዶክተር ኮንቴ፦ አፈጻጸሙን ነው ማየት፤ በፖሊሲ ደረጃ ያን ያህል ችግር ያለ አይመስለኝም:: ግን በአካባቢው ያሉ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላት ለእነዚህ ሰዎች የሚወጣውን ፕሮጀክት አስመልክቶ የሚጠይቃቸው ስለሌለ ሀብቱን ኪሳቸውን ይሞሉበታል:: ስለዚህ የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው::
አዲስ ዘመን፦ ከላይ ሲያነሱ የመንደር ማሰባሰብ የተባለው የአርብቶ አደሩን ለም መሬት ለነከሰምና ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎች መተከያ ነው ብለዋልና እንደው እውነት እንደዛ ነው? ወይንስ መንግሥት እንደሚለው አንድ ላይ አሰባስቦ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ነው?
ዶክተር ኮንቴ፦ አዎ ሁለቱንም ነው:: በተለይም በአዋሽ ዳርቻ ላይ ያሉትን በማስነሳት ዳርቻውን ለመቆጣጠር ሲባል ለሰዎቹ ካሳም ብለው በመንደር መሰባሰብ የተነደፈው ያም ቢሆን ግን ብዙ ገንዘብ የተበላበት ፕሮጀክት ነው፡፡ እነዚያ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ወንዙም መምጣት አይችሉም፡፡ ምንም አማራጭ ያጡና በረሃ ላይ የተጣሉ ሆነዋል::
እስከ አሁን የእነሱን ድምጽ የሚያሰማ አልተገኘም:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንደኛው የመንግሥት ፖሊሲ ሲሆን ሌላው ደግሞ አመራሩ ራሱ የድርጊቱ ተባባሪ መሆኑ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ በዚያ አካባቢ የተነሱ ሰዎች የመሬት ካሳም ነበር፡፡ በዚህም እነርሱ ራሳቸው የሸንኮራ አገዳን አምርተው ለፋብሪካው በማቅረብ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት አካሄድም የነበረ ቢሆንም እርሱንም አፈር ነው የበላው::
አዲስ ዘመን፦ እስኪ ስለ ፓርቲዎ አመሠራረትና የትኛውን ክፍተት ለመሙላት እንደተቋቋመ ቢነግሩኝ?
ዶክተር ኮንቴ፦ ፓርቲው እ.ኤ.አ በ2006 ነው የተቋቋመው፡፡ አነሳሱም በማህበራዊ ፍትህ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ በአገሪቱ ነግሶ የነበረውን ጭቆና ታሳቢ ያደረገ ነው:: በወቅቱ ሰዎች ተገደሉ:: የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ታሰሩ በተለይም አፋር ውስጥ ለገዢው ፓርቲ ታማኝ አገልጋይ የሆኑ ብቻ እንዲቀጥሉ ከመደረጉም በላይ በተለይም በክልሉ የነበሩ 5 ፓርቲዎች ፈርሰው ከእነሱ ጋር ታግሎ የመጣው ብቻ እንዲያስተዳደር ተደርጓል፡፡
በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ ዓይነት ግፎች ተፈጽመዋል፤ የክልሉ እድገትም ሊደርስ የሚገባው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ ሙስና ተስፋፍቷል፤ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ጨምሮ የሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች በሙሉ ተገፈዋል፤ አነሳሳችንም ይህንን ለመፍታት ነው::
ከዚህ ውጪ ግን ሰፋ አድርገን ስናየው ፓርቲው በአፋር ስም ይቋቋም እንጂ ራዕዩ አገራዊ ነው:: በተቻለ መጠን ደግሞ ከሌሎች የመገንጠል አላማ ከሌላቸው ድርጅቶች ጋር ግንባር ፈጥረን በመስራትም ላይ ነን፡፡ ዓላማችንም ይኸው ነው:: እኛ መልካም አስተዳደርን ማምጣትና ፖሊሲን ማስተካከል እንጂ ሌላ ዓላማ የለንም::
አዲስ ዘመን፦ ለምሳሌ ከነማን ከነማን ጋር ሰርታችኋል?
ዶክተር ኮንቴ፦ ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦነግ)፣ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄን መስርተናል:: ከዚያም በፊት ከሌሎች ጋር ለመስራት ሞክረናል፡፡ አብዛኛውን ግን የመገንጠል አላማ ከሌላቸው ጋር ነው የሰራነው::
አዲስ ዘመን፦ አሁንስ ምን እየሰራችሁ ነው?
ዶክተር ኮንቴ፦ የፓርቲ እውቅና ለማግኘት አስፈላጊውን መረጃችንን አቅርበን አሁን ላይ እውቅናውን አግኝተናል:: ከውጭ ተጠርተው ከገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ቅድሚያ እውቅናን ከማግኘታችንም በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰብስብን የምንመራውም እኛ ነን::
በአፋር ክልልም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ቢሮዎችን ከፍተናል፡፡ ለሚቀጥለው ምርጫም ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግን ነው::
አዲስ ዘመን፦ ከሌሎች ጋር የመስራትና ወደፊት የመምጣት ዝግጁነት አላችሁ?
ዶክተር ኮንቴ፦ አዎ ይህማ የማይቀር ነው:: አሁን ባለው የተለጠጠ የፖለቲካ መድረክ ላይ ይህ ሁሉ የፓርቲ ጋጋታ ያስፈልጋል የሚል እምነትም የለንም:: በቅድሚያ በአፋር አካባቢ ያሉትን የተለያዩ ፓርቲዎች ሰብሰብ ማድረግና ከሌሎች አገራዊ ፓርቲዎች ጋር የጋራ የሆነ ግንባር መፍጠራችን የማይቀር ነው::
ግን መጀመሪያ ራሳችንን ማደራጀት ያስፈልገናል:: ምክንያቱም በምርጫ ቦርድ የተመዘገብነው እንደ
ክልል ፓርቲ እንጂ እንደ አገራዊ አይደለም፤ በመሆኑም እነዚህን ሁኔታዎች አስተካክለን ከሌሎች ጋር የመስራት ፍላጎታችን ከፍተኛ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ወደ ኋላ ልመልስዎና በአፋር ክልል የነበሩ አምስት ፓርቲዎች ወደ አንድ መምጣታቸው ችግሩ ምኑ ላይ ነው?
ዶክተር ኮንቴ፦ ችግሩ ታዛዥ፣ ታማኝና እንዲሁም በአንድ አካል ተጠፍጥፈው የተሰሩ መሆናቸው ነው:: ከአምስቱ ፓርቲዎች መካከል ከህወሓት ጋር ታግሎ የመጣውን አብዴፓን ብቻ በማስቀጠል ሌሎቹ በተለያየ ምክንያት እንዲዳከሙና እንዲጠፉ ተደርጓል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ ባለፉት 28 ዓመታት በአገሪቱ ካሉ የክልል ፕሬዚዳንቶች በሥልጣን ላይ ረጅም ዓመትን የቆየውም የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ይመስለኛል:: ሱማሌ እንኳን በተለያየ ጊዜ ቀይሯል:: ይህ የሆነውም ላስቀመጠው አካል ከሚገባው በላይ ታማኝ አገልጋይ ስለነበር ነው::
አዲስ ዘመን፦ አሁን ክልሉን ከሚመራው ፓርቲና ከክልሉ መንግሥት ጋር የእርስዎ ፓርቲ በምን መልኩ ነው ሊሰራ ያሰበው እስከ አሁንስ ግንኙነት ፈጥራችኋል?
ዶክተር ኮንቴ፦ አዎ እንገናኛለን፡፡ ግን እኛ የምንፈልገው ለውጥ ገና መሬት አልረገጠም፡፡ የክልሉ ፓርቲም ይህንን የማስተናገድ ፍላጎቱ ገና ነው:: ቢሆንም ግን በማንኛውም ነገር ተግባብቶና ተቀራርቦ መስራት የሚለው የእኛ ዓላማ ነው:: እዚህ ላይ አብረን መስራት ብንፈልግም አብዴፓ በተለያዩ የሥልጣን ሽኩቻዎችና የእርስ በእርስ ስምምነት ማጣት ምክንያት ሽባ ሆኖ ያለ በመሆኑ አሁን ላይ የክልሉ ሁኔታ አስጊ ደረጃ ላይ ነው::
አዲስ ዘመን፦ አርብቶ አደሩን «ክልል» የሚለው ተጽዕኖ አሳድሮበት ይሆን?
ዶክተር ኮንቴ፦ አዎ ይህ ክልል የሚለው ነገር በድንበር አካባቢ ለሚከሰቱ ችግሮች መንስኤ ሊሆኑ ይችላል:: ለምሳሌ በከሚሴ፣ በወሎና አፋር አካባቢ አዋሳኝ ቦታዎች ያለው ሁኔታ ማሳያ ነው:: ከዚህ ቀደም የአፋር አርብቶ አደር እንደፈለገ ይዘዋወር «በእኔ ክልል አትለፉ» የሚል ነገርም አይታይም ነበር አሁን ግን ይህ በመከሰቱ ችግሩ ከፍተኛ ሆኗል:: ከአፋርና ከኢሳ ጋር ያለው ግጭትም ከዚያ ጋር ነው የሚያያዘው:: ክልል የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ያውካል፡፡ በአንድ በኩል ያንን ማህበረሰብ የሚወክሉ አሉ፤ በተግባር ግን አሁን ያለው ሁኔታ አርብቶ አደሩን የሚደግፍ ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በተግባር ሲታይ ግን አርብቶ አደሩ ተገፍቷል:: ከዚህ አንጻር የክልሉ በተለይም የአርብቶ አደሩ ችግሮች ገና የተፈታ አይመስለኝም::
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ መሪ ነዎትና ወደ ኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ልውሰድዎ:: ምክንያቱም አፋር በኤርትራም በኢትዮጵያም አለና አሁን የተገኘው ሰላም በምን መልኩ ነው የሚጠቅመው?
ዶክተር ኮንቴ፦ ሰላም ለአፋር ሕዝብ በጣም ወሳኝ ነው:: በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ጦርነት ፍጻሜውን ያገኘው እ.ኤ.አ በ2000 ቢሆንም እርቀ ሰላሙ እስከተካሄደበት ወቅት ድረስ የአፋር ሕዝብ ሁለቱም በር ተዘግቶበት መንቀሳቀስ ሳይችል ቆይቷል:: በኤርትራና በጅቡቲ እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ በኩል የነበረው አለመግባባት በክልሉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫናን አሳድሮ ቆይቷል::
ስለሆነም ከዚህ ሰላም ከአፋር ሕዝብ በላይ የተጠቀመ የለም:: እኛ ደግሞ የምናምነው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ከነገሰ ሁኔታው ወደ ጅቡቲም ይሁን ወደ ኤርትራ መድረሱ አይቀርም በሚል ነው:: በመሆኑን አገሪቱም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነባት የማድረግ ሥራ መሰራትን ትኩረት እንሰጠዋለን::
አዲስ ዘመን፦ ፓርቲዎ ኤርትራ ውስጥ ካሉ የአፋር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አለው?
ዶክተር ኮንቴ፦ እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጭቆና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን መታገል ነው ዓላማችን:: ስለዚህ በአፋርነታችን ብንገናኝም የፖለቲካ ግንኙነታችን ግን ያን ያህል አይደለም፤ ምክንያቱም የቀይ ባህር አፋር ድርጀት የሚባለው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ ሲሆን እኛ ደግሞ በኤርትራ ስንታገል የቆየን ነን በዚህ መካከል ተገናኝተን ለመነጋገር አገር ውስጥ መግባት አንችልም ነበር::
በሌላ በኩልም የፖለቲካ ዓላማችን የተለያየ ነው:: እነሱ ኤርትራ ውስጥ የራሳቸውን ነፃነት ለማግኘት ይሰራሉ፤ እኛም ደግሞ የራሳችንን ዓላማ ይዘን እንንቀሳቀሳለን፡፡ የጅቡቲም ተመሳሳይ ነው:: ግን ብዙ ጊዜ የሚነሳ ነገር አለ አፋሮች «ታላቋ አፋር» ወይም «ስቴት ኦቨ ግሬት አፋር» ዓላማ አላቸው ይባላል:: ይህ ለማተራመስ የሚወራ ነው እንጂ አንድም የፖለቲካ ድርጅት በዚህ ዙሪያ ጥናት አድርጎ ድምዳሜ ላይ አልደረሰም::
ሁኔታው እኮ የሚቻልም አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ተቆርሶ ከኤርትራና ከጅቡቲም እንደዛው ተወስዶ ይህንን ለማድረግ ምን ዓይነት ኃይል ቢኖር ነው? ይህንን ጥያቄ ይዞ መዞር ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም መንሳት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ አንዳንዶች ደግሞ አሰብ የአፋር ነው የሚሉ አሉና በዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድን ነው?
ዶክተር ኮንቴ፦ ካለው እውነታ ከተነሳን አሰብ የአፋር ነው፡፡ ግን የየትኛው አፋር የሚለው ጥያቄ ይመጣል፤ እኛ እስከምናስታውሰው ድረስ አሰብ የኢትዮጵያ ግዛት የነበረ አሁን ደግሞ ኤርትራ ነፃ ወጥታ አሰብም የእርሷ ግዛት የሆነ ነው:: በመሆኑም እኛ የአሰብን ጥያቄ የምናየው በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ሰፍኖ አገራቱም የጋራ የሆነ ፕሮጀክት ቀርጸው የጋራ ነገር እንዲፈጠር ነው የምንፈልገው::
ይህ የአፋር ነው ምናምን የሚባለው ነገር የቅርብ እይታ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ እኛ የምናስበው ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሌ የጋራ ኢኮኖሚ በመፍጠር የአፍሪካ ቀንድን የኢኮኖሚ ሁኔታ መዘወር የሚችሉ ኃይሎች ናቸው:: እዚህ ላይ ፖርት ሱዳን፣ አሰብ፣ ጅቡቲ፣ በርበራ አሉ እነዚህ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸውን በመጠቀም በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አንድ አድርገው መኖር የሚችሉ ከመሆናቸው አንፃር የአሰብ ጥያቄ ለእኛ ተራና ራዕያችንን የሚያሳንስ ነው::
አዲስ ዘመን፦ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ግጭቶች እንዳይከሰቱ በፓርቲዎት ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ዶክተር ኮንቴ፦ በተለይ በአፋርና በኢሳ መካከል ያለው ግጭት የዛሬ 50 እና 60 ዓመት የውሃና የግጦሽ መሬት ነበር፡፡ አሁን ግን መልኩን ቀይሮ የግዛት ማስፋፋትና ኮንትሮባንድ ሆኗል:: ከዚህ አንጻር ከፌዴራል መንግሥት የሚጠበቁ ሥራዎች አሉ:: የወሰን ጥያቄውን ደግሞ በወሰን ኮሚሽን አማካይነት መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ወንድማማች ሕዝቦች በየጊዜው እየተጋደሉ መኖር የለባቸውም::
አዲስ ዘመን፦ አሁን የጸብ መነሻ የሆኑ ቦታዎች ግን ከተወሰነ ዓመት በፊት ለአፋር የተባሉ ናቸው? አሁን በሶማሌ በኩል እየተነሳ ያለው ያን ጊዜ የሰጠው አካል ውሳኔው ትክክል አይደለም የሚል ነው፡፡ አዲስ የመጣ አመራር ማፍረስ ይችላል ወይ?
ዶክተር ኮንቴ፦ ታሪካዊ ሁኔታው ሲታይ አፋር ከነበረበት አካባቢ በጣም ተገፍቷል:: ይህ መገፋቱ ደግሞ አሁን አስፋልት ላይ እንዲደርስ አድርጎታል:: ይህ ውሳኔ የተወሰነው ደግሞ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የነበሩ መረጃዎች ተሰባስበው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተጨምሮበት 1ሺ 700 ገጾች ጥናት ከታየ በኋላ ነው፡፡ አካባቢው የአፋር ምድር መሆኑ አያጠራጥርም:: ሆኖም አሁን የተወሰነ ሰፈራ ስለተደረገ እነሱ በልዩ ቀበሌ መብታቸው ተጠብቆ ይተዳደሩና ይኑሩ ነው የተባለው::
አሁን ትልቁ ችግር በአፋር ክልል ውስጥ የሚኖረው ኢሳ ብቻ አይደለም፡፡ ኦሮሞ አማራ እና ሌሎቸም አሉ፡፡ እነዚህስ ማህበረሰቦች ድምጽ አይሰማም ወይ? የሚለው ነገር ችግሩን ትንሽ ውስብስብ ያደርገዋል::
አዲስ ዘመን፦ ፓርቲዎ ችግሩን እንዴት ሊፈታው አስቧል?
ዶክተር ኮንቴ፦ በቅድሚያ የወሰኑ ጥያቄ ተግባራዊ መሆን አለበት እንላለን:: ከዚያ በኋላ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ወደ እርቀ ሰላም ፕሮጀክት እንሄዳለን:: ሌላው አርብቶ አደር ማህበረሰቡ የሚጋጭባቸውን ቦታዎች ምናልባትም ውሃ የሚያስፈልገው ከሆነ እርሱንና ሌሎች ሥራዎችን በመስራት ግጭት እንደቀንስ እናደርጋለን::
ከዚህ ቀደም የአፋርና የኢሳ የሰላም ኮሚቴ ብሎ መንግሥት በማቋቋሙ ብዙ ገንዘብ ሲበላ ቆይቷል:: አሁን ኢሳ የሶማሌ ክልል አንድ ጎሳ ሆኗል፡፡ አፋር ደግሞ ራሱን የቻለ ክልል ነው፡፡ ስለዚህ ችግሮች መፈታት ያለባቸው በሁለቱ አካላት ነው እንጂ በተወሰነ የሶማሌ ጎሳ አይደለም፡፡ ይህ የአፋርን ሚና ማሳነስ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ግን እኮ የውሳኔው ተቃውሞ የወጣው ከጎሳው ሳይሆን ከክልሉ ነው፣
ዶክተር ኮንቴ፦ አዎ ከክልሉ ነው:: አሁን ነገሮች ወደ ክልላዊ ሁኔታ ተቀይረዋል:: አሁን ላይ ሁለቱም ክልሎች ልዩ ኃይል እንዳሰማሩ ነው የምንሰማው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶበት መፍትሔ ማግኘት ካልቻለ ግጭቱ ከባድ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፦ ለኢትዮጵያ ብሔር ግንባታ የሚበጀው የትኛው ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ኮንቴ፦ የእኔ አመለካከት ማህበራዊ ፍትህ ከሰፈነ የብሔር ጥያቄ በሂደት ይከስማል የሚል ነው:: ምክንያቱም የብሔር ጥያቄው መነሻው የፍትህ እጦት፣ በቋንቋ አለመጻፍ፣ አካባቢን አለማስተዳደር ናቸው:: በእርግጥ የብሔር ጭቆና ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች ከዚህም በላይ ብዙ ትርክቶች አሏቸው::
ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ከተሰጠ የሰው ልጅ የብሔርን ካርድ ይዞ የሚንቀሳቀስበት ምንም ምክንያት የለውም:: ይህንን አጀንዳ ይዘው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች በአብዛኛው ሕዝብ መሸነፍ የሚችሉ ናቸው:: ስለዚህ የብሔር ጥያቄ በፌዴራል ሥርዓቱ ከተመለሰ አክራሪነቱ ከስሞ ብሔራዊነት ወደሚለው አስተሳሰብ መሄድ የሚቻል ይመስለኛል::
ሌላው ላለፉት 28 ዓመታት የተሰራበትን ትርክት እንዴት ነው ወደ አገራዊ ቅርጽ መቀየር የምንችለው የሚለው በራሱ ፈተና ነው:: በመሆኑም የብሔር ጥያቄ ጊዜ ይወስዳል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን ነው መፍትሔው ብለዋልና እርሱን ማስፈን የሚቻለው እንዴት ነው?
ዶክተር ኮንቴ፦ ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን የሚቻለው እያንዳንዱ ዜጋ ደህንነት እንዲሰማው ማድረግ ሲቻል ነው:: ስለዚህ ሰው እንደ ሰው መታየት አለበት እንጂ አንዱ እንደ አማራ ከታየ ሌላው እንደ ኦሮሞ የሚታይ ከሆነ አስተሳሰቡ ይምታታል:: በመሆኑም አፋር ያለው አማራ በብሔሩ ሳይሆን በሰውነቱ ከተከበረና እሱም ምቾት የሚሰማው ከሆነ ያን ጊዜ ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን ይቻላል::
አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ የእርስዎ ፓርቲ ሶሻል ዴሞክራሲ ነው የሚከተለው ማለት ነው?
ዶክተር ኮንቴ፦ አዎ እኛ ራዕያችን ሶሻል ዴሞክራሲ ነው:: የስዊድንን ሞዴል በመከተል ዌል ፌር ስቴት መመስረት ነው ሃሳባችን::
አዲስ ዘመን፦ ዌልፌር ስቴትና ሶሻል ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣት ነባራዊ ሁኔታው ምን ያህል ያመቻል?
ዶክተር ኮንቴ፦ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የሥርዓቱ ቁርሾ ከዚያ የተረፉት ቅሪቶች ናቸው:: እነዚህ ነገሮች ደግሞ ፍትሀዊ የሆነ የሀብትና የሥልጣን ስርጭት እንዳይሟሉ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ከተሟሉ በኋላ ነው ዌልፌር ስቴትና ሶሻል ዴሞክራሲን መገንባት የሚቻለው::
ዌልፌር ስቴትና ሶሻል ዴሞክራሲ ከተገነባ በኋላ ለሕዝቡ ነፃ ትምህርትና ጤና ይሟላል:: በዚህ የተነሳ ይህ ሃሳብ ገዢ ይህናል፤ አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ምን ያህል ያስኬዳል የሚለው በተግባር የሚታይ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፦ አስተሳሰቡ ታክስን ሰብስቦ ለሌላው ማካፈል ነው ይህንን ማድረግ የሚችል ኢኮኖሚ እንዴት መገንባት ይቻላል?
ዶክተር ኮንቴ፦ በእኛ ሃሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ዕድል የሚከፍት ገበያ ነው መፈጠር ያለበት፡፡ ለምሳሌ በሌላው አገር ማሽኖች ብዙ ሥራ ይሰራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለእኛ ጥሩ አይሆንም፤ ስለዚህ መፍትሔው ብዙ ሥራ አጦችን የሚያሳትፉ ፕሮጀክቶችን መቅረጽ ነው::
አሁን ያለው ታክስ በመንግሥት ሠራተኛ ላይ የተንጠለጠለ የግል ሴክተሩን የማይጠይቅ ነው ይህንን መቀየር ያስፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ጥገኝነት የተላቀቀ የሥራ ገበያ ያስፈልጋል:: ይህ ሲሆን ደግሞ ሰውም ታክስ ለምን እንደሚከፍል ያውቃል:: መንግሥትም ደግሞ የከፈላችሁት ታክስ በዚህ አካባቢ ይህ ነገር ተሰርቶበታል ብሎ ማስረዳትም ይችላል::
አዲስ ዘመን፦ ኢህአዴግ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ይላል፤ ይህ መንግሥት እስከ አሁን የመጣበት አካሄድ በእርስዎ እይታ ድክመትና ጥንካሬው ምንድን ነው?
ዶክተር ኮንቴ፦ ልማታዊ መንግሥት የሚለው ዝም ብሎ ባዶ ፕሮፓጋንዳ ነው:: ምክንያቱም ልማታዊ መንግሥት ምን አደረገ? ከዚህስ ተጠቃሚ የሆነው ማነው? ቢባል ሀብት ባለውና በሌለው መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ እንዲሄድ ከማድረግ ሌላ ያመጣው ልማት የለም::
ሕዝቡን ሳያስተባብሩ የግሉን ሴክተር አንቆ ይዞ ልማታዊ መባልም አይቻልም:: ሁሉንም ነገር በመንግሥት ቁጥጥር ስር አድርጎ የሚደረግ ልማት አሁን እንዳየነው ባዶ ካዝና ማስረከብ ነው ውጤቱ:: ስለዚህ ልማታዊ መንግሥት የሚባለው ነገር እስከ አሁን ድረስ ለፖለቲካ ፍጆታ እንጂ መሬት ጠብ ያለ ነገር የለውም::
በርግጥ ግንባታ ተሰርቷል:: መሠረተ ልማቱም እንደዚያው፣ ግን እነዚህ ነገሮች የተሰሩት በአገሪቷ ሀብት ነው ወይስ በብድርና እርዳታ ብንል አብዛኞቹ ለሚቀጥለው ትውልድ በሚተርፍ ብድር ነው:: ስለዚህ ልማታዊ መንግሥት እንደገና መከለስ አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ኮንቴ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 / 2011
እጸገነት አክሊሉ