አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ለአራት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል የ452ሺ194 ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡ ድጋፉም በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚከናወኑ የትምህርት፣ የጤናና የአረጋውያን ማዕከላት ግንባታና ማስፋፊያ ሥራዎች የሚውል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በድጋፍ ስምምነቱ ፊርማ ላይ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኬ ማትሱናጋ፣ ድጋፉ በሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን ለሚገኘው የሃሮ ሾቴ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ፣ በእነሞርና ኤነር ወረዳ ለሚገኘው የጉንችሬ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለሻሸመኔ ከተማ የምግባረ ሰናይ የአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ማዕከል መጠለያ ግንባታ እንዲሁም ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቁሳቁስ ማሟያ ድጋፍ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡ ድጋፉም ከጃፓን የማኅበራዊ ልማት ፕሮጀክት በኩል የተደረገ እርዳታ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የድጋፍ ስምምነቱን ከተፈራረሙት መካከል የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ አደም ከማል፣ የተደረገው ድጋፍ ለሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፣ ድጋፉ ጃፓን በኢትዮጵያ ልማት ላይ አሻራዋን የማስቀመጧ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የእነሞርና ኤነር ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስጋኑ ወልማርያም በበኩላቸው ‹‹ድጋፉ ጥራት ያለው የመማሪያ ክፍልና የማስተማሪያ ቁሳቁስ እንዲሟላ በማድረግ የተሻለ የመማር ማስተማር ስርዓት እንዲፈጠር ያስችላል›› ብለዋል፡፡
የጃፓን የማኅበራዊ ልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ400 በላይ በሚሆኑ ፕሮጀክቶች ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ተግባራትን አከናውኗል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2011
ሰለሞን በየነ