አዲስ አበባ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያና ኤርትራን የጋራ ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር የህግ ማዕቀፍ በአጭር ጊዜ እንደሚተገብር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴርና የሰላም ሚኒስቴር ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ100 ቀናት እቅድና አፈጻጸማቸውን አቅርበዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የ100 ቀናት ዕቅድና አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በድንበር፣ በንግድ፣ በታክስ ፣በኢሚግሬሽንና በሌሎችም ጉዳዮች የሁለቱን አገራት ጥቅም ያማከለ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ህግ የሚዳኝ የህግ ማዕቀፍ በድርድር እየሰራ ይገኛል፤ በቅርብ ጊዜም ይተገበራል፡፡
የህግ ማዕቀፉ የሁለቱን አገሮች ወድማማችነትና የህዝቦቹን መቀራረብ መነሻ በማድረግ በመግባባት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ አገራቱ ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ተለያይተው በቆዩባቸው ረጅም ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተፈጥረው የነበሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ ድርድሩ በተከታታይ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡ እስካሁን በተሰሩት ሥራዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ላይ ትኩረት ሲደረግ መቆየቱንም አመልክተዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ100 ቀናት ዕቅዱ መሰረት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በቀጣናው አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉ አንዱ ስኬት መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ወርቅነህ፤ ሶማሊያን ጨምሮ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር የተካሄደውን ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ በስደት ላይ የሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው እንዲጠበቅ በተደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ ተግባራትን ማከና ወኑን፤ ተቋሙን መልሶ ማደራጀቱም ለለውጥ ያደረገውን ዝግጅት እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሌላዓለም ገብረዮሐንስ በበኩ ላቸው የተቋሙን የመቶ ቀን ዕቅድና አፈጻጸም በተመለከተ እንደገለጹት፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መከተል፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የሀብት አስተዳደርና ግዥ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ፣ ሠራዊቱ ተረጋግቶ እንዲቆይ የሚያስችሉ የማትጊያ ስልቶችን በማጥናት የሪፎርሙ አካል ማድረግ እንዲሁም የመተካካት ሥርዓትን መዘርጋት ከቁልፍ ተግባራቱ መካከል እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በአሰራር ያልነበሩት የሂሳብ አያያዝ፣የንብረት ግዥና አስተዳደር መመሪያ እንዲሁም በፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ይቀርብበት የነበረውን የሂሳብ ኦዲት ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ የሚያግዝ አዋጅ የማሻሻል ሥራ ማከናወኑን አብራርተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሐት ካሚል በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የማደራጀት ሥራ ላይ መቆየቱንና ጎን ለጎንም በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ግርግር ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን በየደረጃው ካሉ አካላት፣ከሃማኖት አባቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት መወያየቱን አመልክተዋል፡፡
በተለይም ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር በተሰራው ሥራ ወደተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ በሚደረገው ውይይት ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ የተለያየ ሙያ በተለይ የቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ከክልልና የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ጋር በመወያየት በሰላም ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ በማድረግ፣ የሰላም እናቶችም በየክልሉ በመሄድ ስለሰላም እያበረከቱ ያለውን በጎ አስተዋጽኦ በአብነት አንስተዋል፡፡
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ከሚኒስትሮቹ ጋር በመናበብ እየሰሩ ሀገራዊ ተልዕኮን የመወጣት ተግባር እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ የ100 ቀናት እቅዶቻቸውን በተሻለ እንዲፈጽሙም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 6/2011
ለምለም መንግሥቱ