የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የሆኑት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) በ93 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈው ከ 2 አመት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር።
ተስፋዬ ሳህሉ በቀድሞው ባሌ ክፍለ አገር ከዱ በተሰኘ ስፍራ ከአቶ ሣህሉ ኤጀርሳ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ ሰኔ 20 ቀን 1916 ዓ.ም ተወለዱ። አምስት አመት ሲሞላቸው ትምህርት ይማሩ ዘንድ አባታቸው ወደ ጎባ ወሰዷቸው።ወላጆቻቸው በስራ ምክንያት በአንድ ቦታ ረግተው የሚቀመጡ አልነበሩምና በመጀመሪያ ወደ ጊነር በመቀጠል ወደ ጎሮ ከዚያም ወደ አርከሌ አቅንተው በመጨረሻ ተመልሰው ሐረር ገብተዋል።ከቤተሰባቸው ጋር ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ መንከራተታቸው አብቅቶ ፋታ ያገኙት ሐረር ከገቡ በኋላ ነበር።በሐረር የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡
14 ዓመት ሲሞላቸው ወላጅ አባታቸው አቶ መንበረ ወርቅ ኃይሉ ለተባሉ ግለሰብ በአደራ ሰጧቸው።በዚህ ጊዜ የወላጆቻቸውን ቤትና ያደጉበትን ቀዬ ለቀው ወደ አዲስ አበባ ተጓዙ።አዲስ አበባ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ገብተው መማር እንደጀመሩ ብዙም ሳይቆይ የማይጨው ጦርነት ተቀሰቀሰ።
ተስፋቸው የጨለመው ይሄኔ ነበር።እናት፣ አባታቸውና ዘመዶቻቸው በሙሉ በጦርነቱ አለቁ።በየተራ የሚመጣውን መርዶ እየሰሙ በሀዘን ተዋጡ።“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ከአባታቸው በአደራ የተቀበሏቸው ብቸኛ አሳዳጊያቸውን ፋሽስት ጣሊያን አዲስ አበባ ላይ ሰቀላቸው።በዚህ ወቅት ከጠላት ጋር ለመፋለም ልባቸው ቢነሳሳም በበረታ የእግር ህመም ሳቢያ ሆስፒታል ለመግባት ተገደዱ።
ትንሽ ማገገም ሲጀምሩ ኑሮን ለማሸነፍ የሀኪም ቤቱ ኃላፊ የሆነውን ጣሊያናዊ ጫማ ይጠርጉ ነበር።ህክምናቸውን ሲያጠናቅቁም ከጣሊያናዊው ጋር በመግባባት ቢሮ ማጽዳትና መርፌ መቀቀልን የመሰሉ ስራዎችን መስራት ጀመሩ።በኋላም ክትባት እስከመክተብ ደርሰው ነበር።በተጨማሪም ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ስለሚናገሩ ለህክምና የሚመጡ ሰዎችን በማስተርጎም ያገለግሉ ነበር።
የተማሩትን የህክምና ሙያ ያየ አንድ ጣሊያናዊ አትክልት ተራ አካባቢ ክሊኒክ ሲከፍት ይዟቸው ሄደ።ከቀጣሪያቸው ጋር ሲሰሩ ቆይተው ጣሊያናዊው ወደ አገሩ ሲሄድ ክሊኒክ ውስጥ ይታከም የነበረ ሌላ ጣሊያናዊ ከአትክልት ተራ አለፍ ብሎ “ሎምባርዲያ” የሚባል ሆቴል ውስጥ በአስተናጋጅነት ቀጥሯቸው በመስተንግዶ ሙያ አሰለጠናቸው።ይህ ጣሊያናዊም በህመም ምክንያት ወደ አገሩ ሲመለስ በወቅቱ እቴጌ እየተባለ በሚጠራ የአሁኑ ራስ ሆቴል አስቀጠራቸው፡፡
በእቴጌ ሆቴል የነበራቸውን ቆይታ ሲገልጹ፣ “ሆቴሉን ይመራ የነበረው ጣሊያናዊ ስልጡን በመሆኔና የወሰደኝ ጣሊያናዊ አደራ ስላለበት በጣም ይወደኝ ነበር።በዚህ ምክንያት የሆቴሉ የምግብ ክፍል ረዳት ኃላፊ አደረገኝ” ይላሉ።ነገር ግን በሆቴሉ ውስጥ የማይወዳቸው አንድ ሌላ ጣሊያናዊ ኃላፊ ነበር።አንድ ዕለት ምክንያት ፈልጎ ጥፊ ሲያቀምሳቸው በያዙት ትልቅ ጭልፋ አናቱን ፈንክተውት ብዙ ደም ስለፈሰሰው ትልቅ ረብሻ ሆነ፡፡ ፖሊስ ሲፈልጋቸው ሆቴሉን የሚመራው ጣሊያናዊ በርሜል ውስጥ ደብቋቸው በሌሊት ወደ ሐረር ሸኛቸው፡፡
ሐረር እንደደረሱም በዚያ ወዳለው እቴጌ ሆቴል ቅርንጫፍ አምርተው ለጀርመናዊ የሆቴሉ ኃላፊ በአዲስ አበባ በሚገኘው ሆቴል መስራታቸውን ተናግረው እንዲቀጥራቸው ጠየቁት። ጀርመናዊው አዲስ አበባ ደውሎ በእርግጥም በሆቴሉ መስራታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ቀጠራቸው።ስራ ጀምረው ትንሽ እንደቆዩ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቆ ወጣ። ሆቴሉንም ልዑል መኮንን ገዙትና “ራስ ሆቴል” አሉት። አባባ ተስፋዬም የምግብ ቤት ኃላፊ ሆነው ተሸሙ።መኳንንቱ ለእረፍትና መዝናናት ወደ ሆቴሉ ሲመጡ ፒያኖ ይጫወቱላቸው ነበር፡፡
በ1934 ዓ.ም. በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች ይሰባሰቡ የሚል ትዕዛዝ ከመንግስት ተላለፈ። በዚህ ጊዜ አባባ ተስፋዬም ከሐረር ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ይሄኔ ነው ወደ ኪነጥበቡ ዓለም ተጠቃልሎ የመግባት ዕድል የገጠማቸው።
በ1937 ዓ.ም የማዘጋጃ ቴአትር ቤት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ሲያሰባስብ አባባ ተስፋዬም ተካተው በወር 11 ብር እየተከፈላቸው የትወናውን ዓለም ተቀላቀሉ።በብዙ ቴአትሮች ላይ ከተሳተፉ በኋላ በ1948 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲከፈት በማዘጋጃ ቤት አብረዋቸው ሲሰሩ ከነበሩ ተዋንያን ጋር ወደ ብሔራዊ ቲያትር ተሸጋገሩ።በብሔራዊ ቴአትር ቆይታቸውም ከ 70 በላይ ቴአትሮችን ተጫውተዋል።
ሀሁ በስድስት ወር ፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ ኤዲፐስ ንጉስ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ ዳዊትና ኦርዮን፣ ኦቴሎ፣ አስቀያሚዋ ልጃገረድ፣ ስነ ስቅለት እና የአዛውንቶች ክበብ ከተወኑባቸው ተውኔቶች ጥቂቶቹ ናቸው። “ብጥልህሳ ? ነው ለካ ?” እና “ጠላ ሻጯ” የተሰኙ ተውኔቶችንም ደርሰዋል።
እውቁ ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ ስለ ተስፋዬ ሳህሉ የትወና ብቃት ሲናገር ፣ “ጋሽ ተስፋዬ ትራጄዲም ኮሜዲም ቴአትሮችን መጫወት ይችላል። ኮሜዲ በሚጫወትበት ጊዜ ዋና ችሎታው የገጸ ባሕሪውን ደም፣ ስጋና አጥንት ወስዶ የራሱ አድርጎ ይላበሰዋል።በዚህም የደራሲውን ስራ አጉልቶ ያወጣዋል፡፡” ብሎ ነበር፡፡
ራሳቸውም ለሙያቸው ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ ‹‹ኪነ ጥበብ አባቴ ነው፤ ንጉሤና አሳዳሪዬ ነው። እፈራዋለሁ።አከብረዋለሁ። የኪነ ጥበብ ባሪያ ነኝ። ከኪነ ጥበብ የምለየው ስሞት ብቻ ነው›› ይላሉ።
ሴቶች ወደ መድረክ ለመምጣት ባለመድፈራቸው የሴት ተዋናይት ባልነበሩበት ወቅት በጎንደሬው ገ/ማሪያም፣ ቴዎድሮስ፣ አፋጀሽኝ፣ መቀነቷን ትፍታ፣ ጠላ ሻጯ እና የጠጅ ቤት አሳላፊ ቴአትሮች ላይ የሴት ገፀ ባህሪያትን ወክለው ተጭውተዋል።ሴት ሆነው ሲጫወቱም ገፀ ቅባቸውን የሚሠሩት ራሳቸው ነበሩ። በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ለ36 ዓመታት ያገለገሉት አባባ ተስፋዬ በ1973 ዓ.ም በጡረታ ተገልለዋል።
ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኘ ፕሮግራም እንዲኖር ሃሳቡን አቅርበዋል።ተቀባይነት ሲያገኙም የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተዋወቃቸውን የቴሌቪዥን ዝግጅት ህዳር 1 ቀን 1957 ዓ.ም. ’’ጤና ይስጥልኝ ልጆች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች! እንደምናችሁ ልጆች !” ብለው ጀምረው ለ42 ዓመታት ልጆችን በማዝናናት ፣ በመምከርና በተረት በማስተማር የሚታወቀውን ተወዳጅ ዝግጅታቸውን አቅርበዋል፡፡
አባባ ተስፋዬ ኢትዮጵያ “የሊግ ኦፍ ኔሽን” አባል በመሆኗ ደቡብ ኮሪያ በተወረረችበት ወቅት በቀረበላት ጥሪ የክቡር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ አባል በመሆን ሁለት ጊዜ ኮርያ ዘምተው የሃምሳ አለቃነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
ተስፋዬ ሳህሉ ተዋናይ፣ ድምጻዊ፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች፣ የልጆች ተረት መጽሐፍ ደራሲ፣ የሆቴል ቤት ባለሙያ፣ ወታደር፣
ተረት ተናጋሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ የምትሃት ባለሙያና የመድረክ አስተዋዋቂ ነበሩ።
በድምጻዊነት ከሚታወቁባቸው ዘፈኖች ውስጥ “ዓለም እንደምን ነሽ? ደህና ሰነበትሽ ወይ” እና “ፀሐይ” ይጠቀሳሉ። በገና፣ ዋሽንት፣ ክራር፣ መሰንቆ፣ ፒያኖ፣ አኮርዲዮንና ትራምፔት የተሰኙትን የሙዚቃ መሳሪያዎች ይጫወቱ ነበር።ለህጻናት የሚያገለግሉ ተረቶችን በማዘጋጀትም አምስት የተረት መጻሕፍትን አበርክተዋል።
በትዳር ሕይወታቸውም ለ48 አመታት አብረው ከኖሩት ከባለቤታቸው ደብሪቱ አይታገድ ጋር ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። የበኩር ልጃቸው ቀድሟቸው ይህን ዓለም ቢሰናበትም አምስት የልጅ ልጆችን አይተዋል።
አባባ ተስፋዬ በኪነጥበብ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተለያዩ እውቅናዎችን አግኝተዋል።በ1991 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኪነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በቴአትር ዘርፍ ‹‹የሕይወት ዘመን›› ተሸላሚ አድርጓቸዋል።ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ህይወታቸው ከማለፉ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል።
ተስፋዬ ሳህሉ ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም በ93 አመታቸው ይህን ዓለም ተሰናብተው፤ ሥርዓተ ቀበራቸው ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።ገና በልጅነታቸው እናትና አባታቸውን ያጡት አባባ ተስፋዬ ሕይወት በብርቱ ብትፈትናቸውም ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጽናት በመቋቋም እንደ አልማዝ አንጸባርቀው አንቱ ለመባል በቅተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
የትናየት ፈሩ