የኃይማኖት አባትና የነፃነት አርበኛው ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች በጥይት ተደብድበው የተገደሉትና ሰማዕትነትን የተቀበሉት ከ83 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት፣ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነበር።በ1875 ዓ.ም በሰላሌ አውራጃ፣ ፍቼ አካባቢ የተወለዱት፣ ገና በለጋ ዕድሜያቸው በጥንታዊው የቤተ-ክርስቲያኗ ስርዓተ ትምህርት መሰረት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያጠናቀቁት፣ ቅኔን በጎጃም (ዋሸራ)፣ ዜማን በጎንደር የተማሩት፣ ወደ ወሎ ተሻግረው ወንበር ዘርግተው የመጽሐፍት ትርጓሜ ትምህርቶችን በብቃት ያስኬዱት የያኔው ኃይለማርያም የኋላው አቡነ ጴጥሮስ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው አስተምረዋል።የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንስሐ አባትም ነበሩ።
በ1921 ዓ.ም ከግብፅ እስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ቤተ-ክርስቲያን መዓረገ-ጵጵስና ተቀብለው ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሰሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ›› ተብለው በመንዝና ወሎ ሐገረ ስብከት ተሾሙ።
አቡነ ጴጥሮስ በመንዝና ወሎ ሐገረ ስብከት ከተሾሙ ከሰባት ዓመታት በኋላ፣ በ1928 ዓ.ም፣ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ የቆየችው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች።አቡነ ጴጥሮስም ወራሪው የኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ ሲመለከቱ ልባቸው በከፍተኛ የኀዘን ጦር ተወጋ።የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መከራ ለኀዘንና ለቁጭት ዳርጓቸው ይህንን ግፍ አይተው ማለፍ አልፈለጉም፤ ይልቁንም ከአርበኞች ጋር በመሰለፍ አርበኞችን ያበረታቱና ይደግፉ ጀመር፡፡
ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል የሚፈፅመውን ገደብ የለሽ ግፍ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ለማሳወቅ ባህር አቋርጠው ከሄዱ በኋላ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ኃይላቸውን አሰባስበው በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ሠራዊት ለመውጋት በወሰኑበት ወቅት አቡኑ የአርበኞቹን ኅብረት ለመባረክና ሞራላቸውን ለማጠንከር ወደ አዲስ አበባ ሄደው ነበር።
በወቅቱ በነበረው የመረጃ እጥረትና የቅንጅት ጉድለት ምክንያት የታሰበው ጥቃት ባይሳካም ‹‹የመጣሁበትን ሳልፈፅም ወደኋላ አልመለስም፤ ብችል በአዲስ አበባም ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት ሕዝቡን በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርገዋለሁ፤ ካልሆነም እዚሁ እሞታለሁ›› በማለት ሕዝቡ ለፋሺስት እንዳይገዛና አስተዳደሩንም እንዳይቀበል ያስተምሩ ጀመር።
ይሁን እንጂ ጠላት በመላ ከተማው ያሰማራቸው በርካታ ባንዳዎች አወኳቸው።በዚህም ምክንያት ጳጳሱ እንዳሰቡት ሊንቀሳቀሱ ባለመቻላቸው በወቅቱ የኢጣሊያ እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ኃይሉ እጃቸውን ሰጡ።ራስ ኃይሉም ለፋሺስቱ አስተዳደር የበላይ ለነበረው ለሮዶልፎ ግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸውና የፋሺስት ጦር ቤተ መንግሥት ውስጥ አስገብቶ አሠራቸው።
ከዚያም ጳጳሱ የኢጣሊያን ገናናነት አምነው እንዲሁም የንጉሥ ኢማኑኤልንና የቤኒቶ ሙሶሎኒን ገዢነት ተቀብለው በሐይማኖታዊ ተልዕኳቸው እንዲሰብኩ ተጠየቁ። እርሳቸው ግን ‹‹የኢጣሊያን ገዢነት የተቀበላችሁ ሁሉ አወግዛችኋለሁ! የኢጣሊያን ገዢነት ከተቀበለ እንኳን ሰው ምድሯ የተረ ገመች ትሁን!›› አሉ። እንዲፈፅሙ የተጠየቁትን ፍርጥም ብለው ‹‹እምቢ!›› ያሉት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡
ለፍርድ የተሰየ ሙት ሦስት ዳኞችም ጳጳሱ በጥይት ተደብ ድበው እንዲገደሉ ፈረዱ። ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም በጥይት ተደብድበው ተገደሉ። አቡነ ጴጥሮስ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክብርና ነፃነት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ለሐይማኖታቸውና ለኢትዮጵያ አገራቸው መስዋዕትነትን ተቀበሉ።
የእርሳቸው መስዋዕትነት የኢትዮጵያውያንን ጀግኖች እልህ አፋፋመው። የሰማዕቱን የአቡነ ጴጥሮስን ጀግንነትና ጽናት ስንቅ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንም በፅኑ ትግላቸው ፋሺስትን አንበርክከው የኢትዮጵያን ነፃነት አስመለሱ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
አንተነህ ቸሬ