የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በኦሮሚያ አርሲ ዞን አስጎሪ ወረዳ ነው የጀመሩት። ከዚያም በመተሐራ መርቲ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረዋል። ከዲፕሎማ ጀምሮም እስከ መጀመሪያ ዲግሪ ድረስ ያለውን የትምህርት ሂደትም በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ “ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ” ነው ያገኙት።
የሥራ ህይወታቸውን በመምህርነት ጀምረው በኦሮሚያ ዓቃቤ ሕግ የሕግ ባለሙያ፣ የምርመራና ክስ ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ በመሆን፤ ቀጥሎም የኢትዮጵያ ፓርላማ ጽህፈት ቤት ሃላፊና አንድ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን፣ የኦሮሚያ ሠራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ሃላፊ፣ በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤትና በኦሮሚያ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለ5 ዓመት ከሠሩ በኋላ የአዳማ ከተማ ከንቲባ በመሆን ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዲፒ/ ጽህፈት ቤት ሃላፊ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ገቢዎች ሚኒስቴርን በሃላፊነት የተረከቡት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የዛሬ የአዲስ ዘመን ዕለተ ዕሮብ የተጠየቅ ዓምድ እንግዳችን ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ቀደም ሲል በሥራ አጋጣሚ ገቢዎች ሚኒስቴርን ያውቁት ነበር? በሃላፊነት ከተመደቡ ኋላስ እንዴት አገኙት?
ወይዘሮ አዳነች፦ ገቢዎች ሚኒስቴርን እንደ ሩቅ ሰው ነው የማውቀው፤ የምሰማቸውና እንደ አንድ ሰው የምረዳቸው ነገሮች ነበሩ።ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገቢዎችና ጉምሩክን ይዞ የተደራጀ እንደመሆኑ መጠን እየሠራቸው ባሉ ሥራዎች ብዙ ልምድ ያለውና ብዙ ሠራተኛንም የያዘ ነው፤ እንዲሁም ደግሞ መለወጥ አለባቸው ተብለው ከተያዙ መሥሪያ ቤቶች አንዱና የተለያየ ቅሬታ የሚነሳበት እንደሆነም አውቃለሁ። ነጋዴውም በየመድረኩ ሁሌ የሚያነሳው መስሪያ ቤት ስለሆነ እንደ ውጭ ሰው ውጫዊ ገጽታውን ለማወቅ ብዙም ሩቅ አልነበርኩም።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ወደ ተቋሙ ተሹመው ሲመጡ በተለይም በገቢ አሰባሰቡ ላይ ያገኟቸው ችግሮች እንዴት ይገለፃሉ?
ወይዘሮ አዳነች፦ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ጥልቅ ተሐድሶ ያስፈልገኛል ብሎ በሚልበት ጊዜ አንደኛ ተቋማቱን ነው ያየው፤ ተቋማት ከአገልግሎት አሰጣጣቸው አንፃር በትክክል እየሠሩ ናቸው ወይ? ተፈላጊውንስ አገልግሎት መስጠት ከመቻልና ውጤት ከማምጣት አኳያ ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ምንድን ናቸው ? የሚለውን ነው።
በአገር ደረጃ የሚነሳው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በቀጥታ የሚገኘው ከግብርና ቀረጥ ጋር ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሥነ ምግባር ችግር በመስሪያ ቤቱ ላይ ይነሳል፤ አገልግሎት አሰጣጡ በጣም ውስብስብና ልክ ነጋዴውን ለመጉዳት፣ ለመቅጣት ወይም ለማስቸገር እንደተቀመጠ የሚረዱም ብዙ ነበሩ።
በአጠቃላይ መስሪያ ቤቱ የሰው ሃይል ስብጥሩ በብቃትና በተለያየ ሁኔታ ችግር አለበት ተብሎ የተለየ በመሆኑ ይህንን ለመቀነስ ለውጥ ለማድረግ ነው የተነሳነው።ወደ ለውጥ ከመግባታችን በፊትም በዋናነት በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ችግር ምንድን ነው? የሚለውን ለመረዳት ሞክሬያለሁ።
በእርግጥ መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የጥናትና የለውጥ ሥራዎችን ሠርቷል ፤ የጥናቶቹን ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን አይተናል ከዚህ አንፃር ወቅቱ በደረሰበት ደረጃ ልክ በአሠራር መፈታት ያለባቸውን መዘመን የሚገባቸው ሂደቶች ሕግና መመሪያዎችን በመለየት ወደሥራ ተገብቷል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጉምሩክ ጋር ጠቅላላ ወደ 10 ሺ ሠራተኞች የያዘ ከመሆኑ አንጻርም በዚህ ደረጃ ሠራተኛ ታጭቆ መሄዱ ሥራውን ሊጎዳው እንደሚችል ታይቷል።ሌላው የተቋሙ አሠራር ተዋዕረድ (የዕዝ ሰንሰለት) ይበዛበታል፤ ይንንም ማሳጠር ያስፈልግ ነበር።ከዚህ ቀደም በተቋሙ ምክትል የሌለው ዘርፍ አልነበረም፤ ይህንንም እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻል ጠይቋል። አስፈላጊ ሆነውም ደግሞ ያልተሄደበት አወቃቀር ነበር። ይህንንም የማስተካከል ሥራ አስፈልጓል።
ሌላው መስሪያ ቤቱን በቴክኖሎጂ ጊዜው የደረሰበት ደረጃ ላይ ለማድረስም ሰፊ ጥረቶች ተደርጓል።በአጠቃላይ በአሠራር፣ በአደረጃጀትና በሰው ሃይል ስምሪት ለውጥ ተደርጓል።በተለይ የሰው ሃይል ስምሪቱ ከምናደርገው ለውጥና ልናመጣ ካሰብነው ውጤት ጋር መሮጥ የሚችልና ብቃት ያለው የሰው ሃይል ማየት ነበረብን፤ እርሱንም አሳክተናል ።መስሪያ ቤቱን መልሰን አዋቀርነው፤ በአንድ በኩል አሠራር ላይ ራሱን የቻለ ቡድን እንዲኖርና የሰው ሃይሉን ከሙያው ከልምዱና ከብቃቱ አንፃር መልሶ የመደልደል ሥራም ተሠርቷል።
በቴክኖሎጂ በኩልም በለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ የጥናት ሥራ እንዲካሄድ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡ በቴክኖሎጂ የተደገፈና ተገልጋዩን የሚያረካ ለማድረግ ተሠርቷል።
አዲስ ዘመን፦ ይህ የተቋሙ ለውጥ በታሰበው ልክ ሄዷል? ያጋጠሙ ችግሮችስ ምንድን ነበሩ?
ወይዘሮ አዳነች፦ ለውጥ ሂደት ነው፤ በአንድ ጀምበር ሠርተን ወይም ለውጠን ውጤት የምናይበት አይደለም።ምክንያቱም ዓለም ተለዋዋጭ ነው፤ ዛሬ በጣም አስፈላጊ ናቸው ብለን የለወጥናቸውና የሠራናቸው ነገሮች ከአንድና ከሁለት ዓመት በኋላ ሌላ ለውጥ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።ስለዚህ በአንድ ጊዜ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ሳይሆን ለተያዘው ዓመት እንዲሁም ወደፊት ለሚመጣው መገንባት ላለበት ጥሩ ሥራ መሠረት ተፈጥሯል፤ ውጤታማ ሥራም ተከናውኗል ማለት ይቻላል።
በተለይም ሕጎቹን ካየን በአንድ ጊዜ የምንቀይራቸው አይደሉም፤ ገና ወደፊትም ማየት የሚጠይቁ ናቸው። ለምሳሌ የጉምሩክ አዋጅ። የተጨማሪ እሴት ታክስ።ኤክሳይስ ታክስና ሌሎችም ከመመሪያዎቹ ውጭ ትልልቅ ለውጦች መደረግ አለባቸው።
እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ለአገልግሎት ሰጪውምሆነ ፈላጊው ውስብሰብ የሆኑ ናቸው።ይህ የሆነው ደግሞ አንዳንዱ የተበታተነ ከመሆኑ አንፃር ሌላው ደግሞ ለአሠራር ክፍተት የሚያጋልጡ በመሆናቸው የዛሬን ችግር ከመፍታት ባለፈ ለነገም ጥሩ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ናቸው በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ሃይል ስምሪቱ አደረጃጀቱ ከመመሪያዎች ጋር ተያይዘው ያሉት ነገሮች ግን በተሰጡ ስልጠናዎችና በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ዛሬውኑ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉም ናቸው።
ለምሳሌ ያልተሰበሰበ ዕዳ ከፍተኛ ነበር፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ በዋና ኦዲተርም የተረጋገጠ ነው፤ ይህ ለምን ሆነ አሁንስ እንዴት ይሰብሰብ ? ሲባል ይህንን ሁኔታ ነጋዴው በተራዘመ ጊዜ መክፈል የሚችልበትን መንገድ መቀየስ አስፈልጓል።
ሌላው በወደብ ዕቃን የሚያስገቡ አስመጪዎች ዕቃቸውን ከደረቅ ወደብ አያነሱም። ይህንን ብክነት ለመቀነስ ምን ይደረግ ? ስንል ያገኘነው መላ ከስር ከስር ከሞጆ እናውጣ ነጋዴው ያላወጣው ገንዘብ ቸግሮት ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ የባንክ ዋስትና እያቀረቡ ቀረጥ ሳይከፍሉ ዕቃቸውን የሚያነሱበትን ሁኔታ አመቻቸን ነጋዴው ክፍያውን ሲያገኝ ለመንግሥት ሊያስገባ እኛም የባንክ ማስያዣቸውን ልንለቅ ተስማምተን በዚህ ሁኔታ ጥሩ ሥራዎች ሠርተናል።
በተመሳሰይ አገልግሎታችንን 24/7 በማለት የ24 ሰዓት አገልግሎት በሰባቱም ቀን በመጀመር ሠራተኞች በሽፍት በተለይም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ያሉ እንዲሠሩ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የገቢ አሰባሰብና የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ተከናውኗል።ከተሠራው የለውጥ ሥራ አንፃር ወዲያውኑ ለውጥ ያመጡ አሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ሌላው በተቋሙ ላይ የሚነሳው ችግር የቅሬታ አፈታት ጉዳይ ነው፤ ተገልጋዩም ተበድሎ ቅሬታ ቢያቀርብ የማይሰማበት የተቋሙ ውሳኔ ብቻ ተግባራዊ የሚሆንበት፤ አንዳንድ ጊዜም ውሳኔ ሳያገኙ የሚቀሩ ጉዳዮች የሚበዙበት አካሄድስ እንዴት ታየ ?
ወይዘሮ አዳነች፦ ከዚህ ቤት የተከማቸ ከ3 ሺ በላይ ቅሬታ ነበር፤ ይህንን የመጥረግና በወቅቱ የሚቀርቡትንም ደግሞ ቶሎ ብሎ ውሳኔ የመስጠት፣ በተሰጠው ውሳኔ የማይረካ ካለ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የሚሄድበትን አካሄድ ማመቻቸት እንጂ እዚህ መያዝ እንደሌለብን በማመን የሠራነው ሥራ ተሳክቶልናል።
አዲስ ዘመን፦ ቴክኖሎጂን ከማምጣት፣ ሕግን ከማርቀቅና ከማሻሻል ባለፈ ለተሻለ ውጤት የሚያበቃው በሰዎች ላይ የሚሠራ ሥራ ነው፤ በዚህ ላይ ያልዎት ሐሳብ ምንድን ነው?
ወይዘሮ አዳነች፦ ዋናው የለውጡ መሰረት ሰው ነው። ቴክኖሎጂውም እኮ ሰው ከተጠቀመው ነው ውጤታማ የሚሆነው፤ በሌላ በኩል ለውጦች ለጋራ አጀንዳችን፣ ጥቅማችን ነው ብሎ ማሰብንም ይጠይቃል፤ ስለዚህ አገር በጋራ እየገነባን ነው። ለዚያ ደግሞ ዋጋ ከፍዬም ለውጥ ከመጣ እሰየው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።እኛም ያደረግነው ሠራተኞቻችንን ወደዚያ የመውሰድ ሥራ ነው። በእርግጥ ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ሠራተኛ መልሶ ደልድሎ ወደ ሥራ ማስገባት በአገሪቱ የቢሮክራሲ አካሄድ ቀላል አልነበረም።ከዚያ አንፃር የተሠራው ሥራ ጥሩ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ታህሳስ ላይ ሥራው ተጠናቆ ድልድል ተደርጎ ካለቀ በኋላ ቀጥሎ ያሉ ወራቶች መለኪያዎች ናቸው፤ ከዚህ አንጻር ስናየው ደግሞ በነበሩት ወራቶች ውስጥ የተሰበሰበው ግብር ከዚህ ቀደም ተሰብስቦ የማያውቅ ነው የሆነው።
በምደባው ከቦታ ቦታ በመዘዋወሩ ያልተመቸው ሠራተኛ እንኳን ቢኖር ሥራውን እየሠራ ነው ቅሬታውን ሲያቀርብ የነበረው፤ ይህም ቢሆን ግን የበለጠ የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣት አለበት።በዚህ ደረጃ ያለውን ሥራ ዘንድሮ ጀማመርነው እንጂ በቀጣዩ ዓመት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፦ የእኛ አገር የግብር ሥርዓት ደሀው ላይ ጫና ያሳደረ፤ ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ባለሀብቶችና ነጋዴዎችን በሚገባ ያላየ ነው፤ እርስዎ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ አዳነች፦ ያሉት ጥናቶች የተባለውን በመጠኑም ቢሆን ያመላክታሉ፤ የመጀመሪያውና በትክክል ግብር የሚከፍለው የመንግሥት ሠራተኛው ወይንም ተቀጣሪው ነው።በሁለተኛ ደረጃ የግል ግብር ከፋዮች በተለይም በትንንሽ ሥራ ላይ የተሰማሩት ናቸው። ምሉዕ ነው ማለት ባይቻልም ጤናማ የሆነ የግብር አከፋፈል ሥርዓት ያለው እነዚህ አካላት ጋ ነው።
ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ትልልቅ ድርጅቶች ግን የሚቀጥሯቸውም ሠራተኞች ወይ ከእኛ ተቋም የወጡ ናቸው። አልያም ከገንዘብ ሚኒስቴር ከፍ ካለም ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ናቸው።በግብር አሰባሰቡ ላይ ላቅ ያለ እውቀት አላቸው ይህንን እውቀታቸውን ግን ለእኩይ ተግባር በማዋል ምስኪኑን ግብር ከፋይ ማጭበርበር የሚያስተምሩ በመሆናቸው ክፍተቶች ይስተዋላሉ።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ከሆነ ፍትሀዊ የግብር አከፋፈል ሥርዓት እንዴት ነው ሊመጣ የሚችለው?
ወይዘሮ አዳነች፦ የመጀመሪያው ማስተማር ነው፤ ይች አገር የጋራችን ናት ሌላ አገር የለንም፤ በሚሰበሰበው ግብር ነው እንደነ አሜሪካ ። ቻይናና ሌሎች የበለፀጉ አገሮች ለውጥ ልናመጣ የምንችለው፤ ፍትሐዊነት ማስፈን የምንችለው የታክስ ሕጉ መከበር ሲችል ነው፤ ይህም ራሱን በቻለ ሚኒስትር ዴኤታ የሚመራ ሆኗል፤ ሌላው የኢንተለጀንስና የምርመራ ሥራችንም እንዲሁ በዳይሬክተር ይመራሉ፤ በዚህ በኩል ዘንድሮ ወደ 189 አከፋፋይ ጅምላ ሻጮች ዕቃ አምጪ የምንላቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ያለ ደረሰኝና ያለ ህጋዊ የሽያጭ ሥርዓት ዕቃ በማከፋፈላቸው እርምጃ ተወስዷል።ድርጅቶቹን የሚወክሉ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው እንዲጠየቁ ሆኗል።ከዚህ ጋር ተያይዞም 11 ሚሊየን ብር የሚገመት አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲቀጡ ሆኗል።
የታክስ ሕግን ከማስከበር አንፃር የእኛ አገር ልል ነው፤ ሌሎች አገሮች ለአሠራርና ለአገልግሎት በጣም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። አጭበርብረው ሲገኙ ግን ምንም ምህረት የለም።እኛ ጋ ሕጉን ለማስከበር በምንሄድበት ወቅት ነጋዴውን እንዳዋከብን፣ እንዳስጨነቀን በማሰብ የገባውም ያልገባውም ዝም ብሎ አስተያየት ይሰጣል።ይህ ሁኔታ ለአገር አይጠቅምም።
የምንሰጠው አገልግሎት መሻሻል አለበት በቅንነት በፍትሐዊነትና በብቃት ማገልገል አለብን፤ ከዚያ በተረፈ ግን የህዝብ ገንዘብን ለመሰብሰብ ያወጣነውን ሕግ ለማስከበር ጠንከር ያለ ሥራ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፦ ግዥ ሲፈፅሙ ደረሰኝ የሚወስዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማበረታታት የሽልማት ዕቅድ ተይዞ ነበር፤ ለምን ሳይተገበር ቀረ?
ወይዘሮ አዳነች፦ በአገር አቀፍ ደረጃ ሕግን ጠብቆና በጊዜው ግዴታውን ለተወጣ ግብር ከፋይ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት በዚህ በሐምሌ ወር ተደርጓል ።በዚህ መልክ እያበረታታን ካልሄድን በስተቀር ችግሩ ውስብስብ ነው።በርካቶች ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ቢከብዳቸውም አብዛኞቹ ግን እየተወጡ በመሆኑ እነዚህን ማበረታታት አስፈላጊ ነው። እማይበረታቱ ከሆነ ግን ልዩነታቸውን ስለማያውቁት ሃላፊነታቸውን መወጣቱ ላይም መሳነፍ ይኖራል ።
ሌላው ደረሰኝ መቁረጥን ለማበረታታት ዕጣ የሚወጣበት ቴክኖሎጂ እንተገብራለን ብለን በሪፎርሙ ከያዝናቸው ዕቅዶች መካከል ይገኝበታል፤ ሆኖም በካሽ ሪጅስተር ማሽን ላይ የሚስተካከሉና ዕጣውም ታዓማኒ እንዲሆን የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት ሥራውን የበለጠ ግልፅ ስለሚያደርገው ይህንን የማዘጋጀት ሂደቱ ጊዜ ወስዷል።
አዲስ ዘመን፦ ያገለገሉ መኪኖች ከውጭ ሲገቡ የሚጠየቀው ቀረጥ ከፍተኛ መሆኑ ቅሬታ እያስነሳ ነው፤ በሌላ በኩል እንደ አማራጭ ለምን በአዳዲሶቹና በአገር ውስጥ በሚገጣጠሙት ላይ ቀረጡ አይቀነሰም የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፤
ወይዘሮ አዳነች፦ በአሮጌ መኪና ላይ ምንም ዓይነት የታክስ አጣጣል ማሻሻያ አልተደረገም፤ የተደረገው የእርጅና ቅናሽ ላይ ያለው አሠራር ግልፅነት የጎደለው ለወቀሳ የዳረገን በመሆኑ እንዴት ነው መሠራት ያለበት የሚለውን እያስጠናን ነበር፤ አንደኛ የእርጅና ቅናሹን በማሰብ በጣም አሮጌ የሆኑ መኪኖች እየገቡ አገሪቱን ልክ እንደ መጣያ መቁጠር ተጀምሯል፤ ይህ ደግሞ ከአየር ብክለት ከትራፊክ አደጋና መሰል ችግሮች ጋር በተያያዘ መሻሻል ያለበት ሆኖ ተገኝቷል ይህም በሂደት ላይ ነው።
ስለዚህ አሮጌ መኪና የሚያስገቡ ሰዎች የእርጅና ቅናሹ ለምን እንደ ቀድሞ በተለመደው መንገድ አልሄደም ነው እንጂ ከቀረጥና ታክስ አንፃር ምንም የተደረገ ማሻሻያ የለም።
ከፖሊሲ አቅጣጫችን አንፃር አገር ውስጥ መገጣጠም መበረታታት አለበት፤ ወደፊት የሚሻሻለው ሕግ ይህንን ለማበረታታት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።ጥራታቸው እንዲጨምር ቁጥጥር ተደርጎ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው እንዲያመርቱ ማበረታታት አለብን እንጂ በሌለን የውጭ ምንዛሪ ማስገባትን ብቻ ትኩረት አድርገን የምንሄድ ከሆነ ጎጂ ነው።
ሌሎች አገሮች አሮጌ መኪና ጭራሽ አገራቸው እንዳይገባ ይከለክላሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ በዓመት ይገድባሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ አሮጌዎቹ ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል ሁኔታው እንዳይበረታታ ያደርጋሉ።እኛ የቱን እንጠቀማለን የሚለውን ጥናቱ ተጠንቷል ወደ ሕግ ረቂቅ ሄዷል ያን ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ወራት በተለይም የውጭ ምንዛሪ ኮንትሮባንድን በከፍተኛ ሁኔታ ሲይዝ እንደነበር ተገልጿል አሁንስ?
ወይዘሮ አዳነች፦ ኮንትሮባንድ አልቆመም፤ ብዙ ሲሰራበት የቆየ የአገር ሀብት በጣም የጎዳ ሰዎችም የህጋዊነትን ያህል በጣም ተለማምደውት ስለነበር በቀላሉ ተስፋ ማስቆረጥ አልተቻለም።ነገር ግን የመያዝ አቅማችን ጨምሯል።አሁን ላይ ከኔትዎርክና ተመሳሳይ ችግሮች አንፃር ሁሉም እየተገለፀ አይደለም እንጂ መያዙ ከእኛ አልፎ ክልሎችም እያገዙን ነው።
ኮንትሮባንድን ከመያዝ አንፃር ያልረካንበትና ብዙ ችግር የሚስተዋልበት አንዱ ማዕድን ዘርፍ ነው። አገሪቱ ከወርቅ ታገኝ የነበረው ከፍተኛ ገቢ አሁን ላይ ቀንሷል።ይህም የውጭ ምንዛሪው ላይ ከፍተኛ ጫና ከማሳደሩም በላይ ወዴት እየሄድን ነው? የሚለውን በራሱ አሳሳቢ አድርጎታል።አሁን ላይ አንድ ለገደንቢ ነው ሥራውን ያቆመው ሌሎቹ ሁሉም ይሠራሉ ባህላዊውም እንደዚያው ስለዚህ እዚህ ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንዳለብን ያሳያል።
ሌላው የቁም ከብት ነው፤ የእኛን ከብቶች የጎረቤት አገራት ኤክስፖርት ያደርጋሉ።ይህንን ለመከላከል ሁሉም በሮቻችን ላይ ኬላ ማደራጀት ስለማንችል ህዝባችን ግን መለወጥ መቻል አለበት። እዚህ ላይ መንግሥትም የቁም ከብት የግብይት ሥርዓቱን በሚገባ አላበጀም በመሆኑም ትንሽ ግብዓት ተጨምሮ ኤክስፖርት የሚደረግበትንሥርዓት በፖሊሲው መሰረት ማመቻቸት ከማስፈለጉም በላይ በቁማቸው መውጣት ያለባቸውን ከብቶችም በሥነ ሥርዓት ተቀርጠው የሚወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል።የግብርና ምርቶች ላይም ተመሳሰይ ችግሮች ስለሚስተዋሉ ከዚህ አንፃር ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።
ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ሥራ ለመሥራትና ንቅናቄውን አገራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፤ በተለይም ችግሩ ኮንትሮባንድ የሚባልበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ለመከላከል የሚያስችል ሥራ መሠራት እንዳለበት መተማመን ላይ ተደርሷል።ገቢ ኮንትሮባንድ ላይ የተሻለ ለውጥ እንዳመጣን ሁሉ በዚያ ልክ ውጤታማ ለመሆን አንዱ የትኩረት አቅጣጫችን አድርገን ይዘነዋል።
አዲስ ዘመን፦ ኮንትሮባንድን በማጋለጥ ሂደት ላይ ጥቆማ የሚሰጡ ሰዎች በሚያገኙት ወሮታ ዙሪያ ቅሬታ ያነሳሉ፤ አንዳንዶቹም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሌሎች ናቸው የሚጠቀሙበት ይላሉ?
ወይዘሮ አዳነች፦ ኮንትሮባንድ በተጠቆመበት ጊዜ ወዲያውኑ የጠቋሚው ሰም ይመዘገባል፤ ጥቆማው ውጤታማ ከሆነ ደግሞ መዝገቡ ታይቶ ወሮታው ይከፈላል።እዚህ ላይ እንግዲህ አንዳንድ ጊዜ ጥቆማ መጥቶ መዝገቡ ላይ የሌለ ወይም ሌላ ሰው ተመዝግቦ ከሆነ በተለየ ሁኔታ ነጥሎ ማጣራት ያስፈልጋል።ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ወሮታው አይከፈለንም የሚሉ አካላት ገጥሞናል አሁን ግን ወሮታ አከፋፈሉ ግልፅነቱ እንዲጨምር ጥቆማንም ለማበረታታት በሚያስችል ሁኔታ ማሻሻያ ተሠርቷል።ከዛ በኋላ ጥሩ ሁኔታ እንዳለ በሪፖርት እየሰማንም ነው ።
አዲስ ዘመን፦ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለይም ከአዲስ ሠራተኛ ቅጥር እንዲሁም ነባሮቹን በመመደብ ላይ አድሎ እየተፈፀመ ነው የሚሉ ሐሳቦች አሉ፤
ወይዘሮ አዳነች፦ አድሎ የሚባል አልተፈፀመም። የአማራ ብሔር እየተገፋ ነው ብሎ የሚያስወራ ግሩፕ ነው የተፈጠረው።ሥራችንንና ተልዕኳችንን ትተን ማነው የተገፋው? የቱ ነው? እያልን መዘናጋትን እንድናመጣ የሚፈልግ አካል አለ።መሥሪያ ቤቱ ከገንዘብ ጋር የተገናኘ ብዙ ሥራ ይሠራል በውስጥም በውጭም እርምጃዎችን ይወስዳል።እዚህ ላይ ለአብነት ብናነሳ በመሥሪያ ቤቱ በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት መቶ ያህል ሠራተኞች ተቀጥተዋል።ብሔራቸውን አላውቅም፤ ቁምነገሩ እርሱ አይደለም፤ ተግባራቸውን ነው የምናየው ።ያለተልዕኳችን ተልዕኮ ሊሰጡን የሚፈልጉ አካላት ግን አሉ፤
በሌላ በኩል ገቢዎች በአሁኑ ወቅት ከውጭ ብዙ ሠራተኛ አልቀጠረም፤ ምክንያቱም ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ሠራተኞች የሞሉበት ተቋም ነው። ከውጤታማነት አንፃር ቦታ ቀያይሯል፤ ዳይሬክተር መሆን ሲችሉ ወደ ዳይሬክተርነት ያልመጡትን፣ ብቃት ያነሳቸውንና ያለአግባብ ቦታ የያዙትን በሚችሉት ቦታ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፤ በዚህ ልክ ባይሠራ ኖሮ የደረስንበት ውጤት ላይ መድረስ ባልቻልን ነበር።
ለዚህ ሁኔታ ብዙ ጆሮ መስጠትና አጀንዳም እያደረግን መሄድ አንፈልግም። ምክንያቱም ለአገር አይጠቅምም፤ ሠራተኞቻችንንም አይመጥንም፤ ከዚህ ይልቅ ምን ተሠርቶ ምን ውጤት መጣ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።ይህ መሥሪያ ቤት እየተቀየረ አገልግሎት አሰጣጡም ደንበኞችን እያረካ ነወይ ? በሥነ ምግባር በኩልም ለውጥ መጥቷል ወይ? የሚለውን ነው ማየት ያለብን።ለሥራው አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ዜጎችም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ እየሠሩ እያገዙ ነው፤ ዋናው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገው የእኛ ወጪ በአገር ውስጥ አቅማችን ላይ የተመሰረተ መሆኑና የታክስ ሥርዓቱም ፍትሐዊ እንዲሆን ማስቻል ነው።
ከውጭ በጣም በጠበበ ሁኔታ ለቸገረን ቦታ ብቻ ሠራተኞችን ቀጥረናል፤ አዲስ ጀማሪ የሆኑ 2 ሺ ያህል ባለሙያዎችንም ቀጥረናል።ይህንን ለየት የሚያደርገው የተጠቀምንበት የቅጥር ማስታወቂያ ሂደት ነው፤ የቅጥር ማስታወቂያው ተደራሽ መሆን አለበት ብለን በማሰብ በአንድ ጋዜጣ ሲተዋወቅ የነበረውን በማስፋት በሁሉም ክልሎች አውርደናል።ኮሚቴ በማቋቋምና ክልሎችም ተሳታፊ እንዲሆኑ በማስቻል መስፈርቱን የሚያሟሉ ሁሉ ተወዳድረው ተቀጥረዋል ሰልጥነውም ሥራቸውን ጀምረዋል።
ይህ ቤት የህዝብ እምነት የሚጎድለው ከሆነ ውጤቱ ምንም ነው የሚሆነው፤ በመሆኑም ሁሉም የሚተማመንበት ለማድረግ አሠራራችንን አብዛኛው ሰው እንዲያምንበት የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ወደፊትም ይሠራል።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ትልቅ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፤ በተለይም በሠራተኞቹ አካባቢ ሙስና የሚመስል ነገር የሚታይበትን ሰው በቀጥታ መቅጣት የሚችልበት መንገድም ተቀምጧል፤ ይህ ሁኔታ በሠራተኞች መካከል የፈጠረው ክፍተት የለምን?
ወይዘሮ አዳነች፦ በዚህ ዓመት መቶ ሠራተኞች ላይ እርምጃ የተወሰደው በዚህ አካሄድ ነው፤ የዲስፒሊን ግድፈት በማንኛውም መሥሪያ ቤት እንደሚሠራው ነው የሚሠራው፤ ሆኖም ሙስና ሲሆን ግን ምንም እርቅ የለውም፤ በቀጥታ የሥራ ስንብት ነው የምናደርገው፤ ይህ ከመሥሪያ ቤቱ ተጋላጭነት አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
አዲስ ዘመን፦ አሉባልታን።ሕገ ወጦችን። በተቋማችሁ ያሉ ሥነ ምግባር ግድፈቶችን ተቋቁማችሁ ለዚህ ውጤት የመብቃታችሁ ምስጢር ምንድን ነው?
ወይዘሮ አዳነች፦ በዋናነት ለእኔ ሥራችንን መውደድ ነው ትልቁ ሚስጥር፤ እኔ እዚህ መሥሪያ ቤት ከመጣሁ በኋላ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በሠራሁባቸው መሥሪያ ቤቶችም ሥራዬን በጣም ወድጄው ነው የምሠራው።ፍቅር ሲኖር ራስን መስጠት አለ፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ የሥራ ባልደረቦቼም ያያሉ ይነሳሳሉ።ሆኖም የምንናገረውን የማንኖረው ከሆነ የምንሰጠው አቅጣጫም የዛኑ ያህል ወርዶ ተግባራዊ አይሆንም።በተቻለ መጠን መጀመሪያ ራስ ላይ ነው ለውጥ ማምጣት ።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ለብቻ የሚሠራ ሥራ የለም፤ በር ላይ በጥበቃ ሥራ ከላይ ከተሰማሩት ጀምሮ ሁሉም የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ባሉበት የስራ ዘርፍ ሁሉ ለተቋሙ መለወጥ፣ ለግብር አሰባሰቡ መቀላጠፍና ውጤታማ መሆን አስተዋጽዎአቸው የጎላ ነው።ስለዚህ በሚመለከታቸው ነገር ላይ ማሳተፍ ጥቅም አለው ብዬ አስባለሁ፤ የምንወስነውን ነገር በማኔጅመንት በጋራ ነው የምናወጣው፤ ይህንን ሥሩ ተብሎ ዝም ብሎ የሚወረወር ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፦ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ አዳነች፦ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
እፀገነት አክሊሉ