በየክረምቱ ተተከሉ የሚባሉት ችግኞች ቁጥር የሚያሻቅብበትን ምክንያት በተመለከተ የተቀለደ ቀልድ ጀባ በማለት ፅሑፌን ልጀምር። በአንድ ክረምት በተካሄደ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ላይ አንድ ባለስልጣን ችግኙን የተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ በአፍጢሙ ደፍትው አፈር መመለስ ይጀምራሉ። ድርጊታቸውን የተመለከተ አንድ ጋዜጠኛ ጠጋ ብሎ “ክቡርነትዎ ይህ ችግኝ እንዲህ ተተክሎ እንዴት ይጸድቃል” ብሎ ይጠይቃቸዋል። ባለስልጣኑም በግልምጫ አንስተው ካፈረጡት በኋላ “በሪፖርት ይጸድቃል” ብለው እርፍ አሉ።
ባለፉት አስር ዓመታት በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች “ተተክለዋል”። ምን ያህሉ እንደጸደቁ ግን አይታወቅም። ዋናው ችግር ችግኝ ተከላው የድርጅት ተልዕኮ ተደርጎ ተወስዶ ከዕቅድ በላይ የማከናወን ሱስ በተጠናወታቸው ካድሬዎች ፊትአውራሪነት እንዲካሄድ መደረጉ ይመስለኛል።
ካድሬዎች ሆነ ብለው ሊያሳኩ ከሚችሉት መጠን ያነሰ አሊያም የገዘፈ ችግኝ ለመትከል ያቅዳሉ። ከዚያም የተለጠጠ ዕቅድ ያቀዱት “የማይቻለውን ችለን መቶ በመቶ አሳካን” ሲሉ ፤ ከአቅም በታች አቃጆቹ ደግሞ 10 ችግኞች ተክለው አንድ ሺ ብለው ሪፖርት በማድረግ “ከዕቅድ በላይ አሳካን” ይላሉ።
ቀድሞውንም ከአቅም በላይም ሆነ በታች ማቀድ ድክመት ነው። ነባራዊ ሁኔታን ፣ በእጅ ያለ ሀብትንና የማስፈጸም አቅምን ከግምት አስገብቶ ያቀደ አካል የመጨረሻ ግቡ እቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት ነው።
ከዕቅድ በላይ የማሳካት ሱሳችን አሁንም የለቀቀን አይመስለኝም።”የታቀደው እንዲህ ነው እኛ ግን በዚህን ያህል ቁጥር ብልጫ ያለው ችግኝ ለመትከል ተዘጋጅተናል” እየተባለ ከዚህም ከዚያም ስንሰማ የከረምነው ዲስኩር በቁጥር መገለጽ ጀምሯል።
345 ሺ ችግኞችን ለተከላ ያዘጋጀው የሱማሌ ክልል መስተዳድር እስከ ሐምሌ 21 ቀን ድረስ በተካሄደው ችግኝ ተከላ 360 ሺ “ተከልኩ” ማለቱ ሳይበቃው ሐምሌ 21 ቀን 847 ሺ 442 “ተክያለሁ” ብሎ ብዙዎችን አስፈግጓል። የአፋር ክልል መስተዳድርም ለክረምቱ 320 ሺ ችግኞችን ለተከላ አዘጋጅቶ እስከ ሐምሌ 21 ቀን ድረስ 110 ሺ ከተከለ በኋላ ሐምሌ 22 ቀን ብቻ 445 ሺ “ተከልኩ” ብሎ ሪፖርት አድርጓል።
ይፋ የተደረጉት መረጃዎች መጣረስ በአንድ ቀን 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ350 ሚሊየን በላይ “ተተከለ” መባሉን እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ናቸው። ተዘጋጀ የተባለው ችግኝና ተተከለ የሚባለው ጨርሶ አይመጣጠንም።
ባለፉት ዓመታት በእስክሪብቶ ወረቀት ላይ የተተከሉት ችግኞች ቁጥር ከሚሊኒየሙ ወዲህ ተተክለው ከጸደቁት በእጥፍ የሚበልጡ ይመስለኛል። የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግኞች እንደተተከሉ የመነገሩንን ያህል ውጤቱ አለመታየቱን አስመልክቶ በ ዲ ደብሊው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ እስከዛሬ በተተከሉት ችግኞች የአገሪቱ የደን ይዞታ መሻሻሉን ጠቅሰው “የሥራው አፈጻጸም ዘገባ ላይ እውነቱ ብቻ እንዲቀርብ መደረግ አለበት” ማለታቸው በሪፖርት የሚጸድቁ ችግኞች ለተጠባቂው ውጤት አለመገኘት ምክንያት መሆናቸውን ያመላክታል።
እንኳን የውሸት ሪፖርት ታክሎበት እስከአሁን ባለው ልማድ በአገራችን ከችግኝ ተከላ በኋላ የሚገኘው ውጤት በአማካኝ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ነው። ይህም ችግኙ ከተተከለ በኋላ ባሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ሲለካ እንጂ ከተጨማሪ ዓመታት በኋላ ቢፈተሽ ይበልጥ ሊቀንስ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ተዋጊ ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ሳይሆን ሲመለስ እንደሚወደሰው፤ ችግኞችን መትከልም ብቻውን እንደ ድል ሳይቆጠር ሲጸድቁ ብዙ ቢባል የተሻለ ውጤት ይገኛል። በየጊዜው ክትትል በማድረግም ከተተከለው ችግኝ ምን ያህሉ እንደጸደቀ ይፋ መደረግ አለበት። “200 ሚሊየን ችግኝ ተከላው ይህን ያህል ቀን ቀረው” እየተባለ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ፣ በዚህ አካባቢ ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ ተደረገ የሚል ዜና ዓመቱን ሙሉ መነገር ይኖርበታል።
አዲስ ከመትከል ባለፈም ያለውን የደን ይዞታ ማስጠበቅ ላይ በስፋት መሠራት አለበት! የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ብሄራዊ የደን ምዝገባ ክትትልና ልኬት አድርጎ ነበር። ልኬቱ እንዳመላከተው በዓመት 92 ሺህ ሄክታር ደን ይጨፈጨፋል። በምትኩ የሚተከለው ግን 19 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ደን ብቻ ነው። ይህም በየዓመቱ ሳይተካ የሚወድመው ደን 73 ሺህ ሄክታር እንደሚደርስ ያሳያል።
ተጨማሪ የእርሻ መሬትና የማገዶ ፍላጎቶች ደን የሚጨፈጨፍባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። መስኖን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ከእርሻ መስፋፋት ጋር የሚያያዝን የደን ጭፍጨፋ ለመቀነስ መሠራት አለበት። ምርጫ የሌላቸው የገጠር አካባቢዎች የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን እንዲጠቀሙና ከተፈጥሮ ደን ይልቅ በሰዎች የሚተከሉ ቶሎ የሚደርሱ ዛፎችን ለማገዶነት እንዳይገለገሉ የማድረግ ጥረት ያስፈልጋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በአርሲ 177 ችግኞችን በነቀለ ግለሰብ ላይ የስድስት ዓመት ጽኑ እስራት መወሰኑ ከሰዎች መፈናቀል ጋር እየተያያዘ በማህበራዊ ድረ ገጽ አቧራ ሲያስነሳ ሰንብቷል። አቧራ ካስነሱትም ከአቧራው ጋር ከተነሱትም አንዱ አይደለሁም። ነገር ግን የችግኞቹ ዋጋ ትኩረቴን ሳበው። በግለሰቡ የተነቀሉት ችግኞች 3 ሺህ 640 ብር ግምት እንዳላቸው በዜናው ተጠቅሷል። የችግኞቹ ጠቅላላ ዋጋ ለ177 ሲካፈል የሚገኘው የአንድ ችግኝ ዋጋ 20 ብር ከ 56 ሳንቲም ነው።
በክረምቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተከለውን 4 ቢሊየን ችግኝ በዚህ ሒሳብ ስናሰላው ለህዳሴው ግድብ ከመደብነው በጀት የሚስተካከል 82 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል። ችግኞቹን ቀጣይነት ባለው መንገድ መንከባከብ ካልቻልን ከፍተኛ መጠን ያለውን የድሃ አገር ሀብት በማባከን በድጋሚ ሪከርድ መስበራችን አይቀሬ ነው። በአንጻሩ ተከታትሎ እንዲጸድቅ ማድረጉ ላይ የመትከሉን ያህል ከበረታን፣ ይተከላሉ በተባሉት አራት ቢሊየን የዛፍ ችግኞች 400 ሺህ ሄክታር መሬት መሸፈን ይቻላል።
የመንግሥት ባለስልጣናት ክብረ በዓላት ላይ ንግግር ሲያደርጉ “የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው…” ብለው መጀመር ይቀናቸዋል። መሪዎችን መከተል ስለሚያስፈለግ እኔም ጽሑፌን በዚህ መንገድ እቋጫለሁ።
የዘንድሮውን ችግኝ ተከላ ልዩ የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተለያዩ አገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች ጋር በመሆን የቤተ መንግሥቱን መሬት ድንግልና በተደጋጋሚ ገስሰዋል። የአገራቸውን መንግሥት የሚወጉ ኃይሎች ብረት ጥለው ችግኝ አንስተዋል። ይህ ትልቅ ስኬት ቢሆንም ምናልባት ሰላማዊው ትግል ካላዋጣን በሚል ወደፊት የሚገቡበትን ጫካ እንዳያበጁ ክትትል ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
ኮሜዲያኖች ተሰባስበው ህብረተሰቡ ችግኝ እንዲተክል በዜማ የታጀበ ቅስቀሳ አድ ርገዋል። ችግኝ ተከላው ኤርትራና ግብፅ ድረስ ዘልቋል። ዜጎች ለዓመታት ከኖሩበት አካባቢ እንዲነቀሉ ምክንያት የሆኑ “አክቲቪስቶችም” መትከልን መለማመድ ጀምረዋል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በሚተክሏቸው ችግኞች ድንበር (ወሰን) እያሰመሩ አለመሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ተዋንያንም ሰብሰብ ብለው አገር አገር በሚሸት ማስታወቂያ ላይ ተሳትፈዋል። እንዲህ ላለ ዓላማ መሰባሰባቸው ያስመሰግናቸዋል። ነገር ግን ማስታወቂያው “ኢትዮጵያውያን ተክለን አንተውም … ተክለን አንረሳም … ሲጣመም አቃንተን … ሲደርቅ አረስርሰን … “ ማለቱ አልተዋጠልኝም።
ለምን ይዋሻል? ተክለን ትተናል ፤ ረስተናል ፤ ሲጣመም አላቃናንም፤ ሲደርቅ አላራስነውም … በማር የተለወሰ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲባል መሬት ላይ ያለው ሀቅ ተገላብጦ መቅረቡ ቅር ያሰኛል። እንደኔ በዚህ ወቅት መተላለፍ የነበረበት መልዕክት “ያልተከልነውን ተክለናል አንበል! የምንተክላቸው ችግኞች በሪፖርት ሳይሆን በተግባር እንዲጸድቁ ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ !” የሚል መሆን ነበረበት።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
የትናየት ፈሩ